በቋራ ያሉ የናይጄሪያ ዘላኖችና ‹ሸውሽዌ›
ክፍል ፪
በዚህ በርሃና ጫካ ብዙ ገራሚ ነገሮች አሉ፡፡ መንደሮች በድንገት በሚነሳ ቋያ ሙሉ በሙሉ ይድማሉ፡፡ በርሜልን ጨምሮ ብዙዎቹ የሰፈራ መንደሮች በበርሃ ቋያ በየጊዜው እየወደሙ እንደገና ይሰራሉ፡፡ የበርሃ ሰው ተስፋ አይቆርጥም፤ ነገ በቋያ ቤቱ እንደሚወድምበት እያወቀ እንደገና ይገነባል፤ ይቃጠልበታል፤ ይሰራል…
በየመንገዱ ጅራታቸው የውሻ ያክል የረዘመ በጎች በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ በጎች ‹ፈላታ› በመባል ይታወቃሉ፡፡ ፈላታዎች የናይጀሪያ ዘላኖች በጎች ናቸው፡፡ በጎቹ በዘላኖቹ ስም ፈላታ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ የናይጀሪያ ዘላኖች የሱዳንና የቻድን መሬት አልፈው ለምን ቋራ እንደከተሙ ለኔ ብዙ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ነገር ግን ቋረኞች እንደሚሉት በቋራ ጫካዎች ውስጥ ፈላታዎች ከብቶቻቸውንና በጎቻቸውን ያረባሉ፡፡ እርግጥ ነው አካባቢው የግጦሽ ሳርና ውኃ ችግር ስለሌለበት ለከበት አርቢዎች ምቹ ቦታ ነው፡፡ የፈላታ ከብቶች አውሬዎች ናቸው፡፡ አበሻ ካዩ አባርረው ይዋጋሉ፡፡ ብዙ ግዜ አበሻዎች ከዛፍ ካልወጡ በስተቀር አያመልጧቸውም፡፡ ነገር ግን አበሾች የፈለታዎችን ከብቶች በጥይት በመምታት እንደሚወስዱባቸው ሰምቻለሁ፡፡ የፈላታ በጎች ተራብተው በድፍን ቋራና መተማ በብዛት አሉ፡፡ መልካቸው ነጫጭ ሲሆን ጸጉር የላቸውም፡፡ ጅራታቸው ረጅም ነው፡፡ ሥጋቸው ቆንጆ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እርግጥ ነው የሔድኩበት ቀን አርብ በመሆኑ የበግ ሥጋ አልበላሁም፡፡
ወደ ጫካ አንድ ሰው ጂፒኤስ ሳይዝ ከሔደ የመጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ የመጣ የመንግሥት ተቀጣሪ ከሆነ መስክ ብቻውን መሔድ የለበትም ይላሉ፡፡ ወደ ጫካው ከሔደ በኋላ በርሃው ሕሊናውን ያነሆልለዋል፡፡ በበርሃ ሕሊናን የመሳት ሒደት ‹ሽውሽዌ› ይባላል፡፡ ሽውሽዌ የያዘው ሰው አቅሉን ስቶ ከመጓዝ ውጭ ወደየትና እንዴት እንደሚሔድ አያውቅም፡፡ በዚህ በርካታ ሰዎች ጠፍተው ቀርተዋል አሉ፡፡ ‹አሉ› የምለው ሰዎች በነገሩኝ መሠረት ስለምነግራችሁ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህች ሽሽዌ የምትባል ‹ነገር› አንዳች መለኮታዊ ነገር ይኑራት አይኑራት የሚታወቅ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ብዙ ሰዎች እንደ ሰይጣናዊ ሥራ የሚቆጥሩት አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የአየር ንብረቱ ሞቃታማ መሆን የሰውነታችን ሥነ ሕይወታዊ (ፊዚዎሎጅካል) ሥራ ስለሚያወከው አእምሯችን በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ያቅተዋል፡፡ በዚህም አቅጣጫ የመለየት ችግር ይገጥመናል የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን የትኛው ትክክል እንደሆነ የተሰራ ጥናት አላየሁም፡፡ አቅጣጫ ሲጠፋ በአካባቢው የሚኖሩት ጉምዞች አቅጣጫን ለማወቅ የሚሆናቸው የለም፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ አሉ፡፡ አንዲት ግብርና ተመድባ የመጣች ሴት ወደ ጫካው የገጠር አካባቢ ትሔዳለች፡፡ ብዙ እንደተጓዘችም ሽውሽዌ ትይዛታለች፡፡ ያኔ ወደየት እንደምትሔድ ሳታውቅ ብዙ ከገለጎ (የወረዳው ከተማ) ርቃ ሒዳለች፡፡ በዚህም ከፈላታዎች እጅ ትገባለች፡፡ እንደነገሩኝ ከሆነ ይህች ልጅ ፈላታዎችን አግብታ እርሷም ዘላን ሆና በመኖር ላይ ነች፡፡
ፈላታዎች ሴቶችን ጠልፈው ወይም ሽውሽዌ ከወሰደላቸው መቼም አይለቁም፡፡ በዚህ የተነሳ ይህች ሴት አንዳንዴ ለዘመዶቿ ደብዳቤ ከመጻፍ የዘለለ ከጫካ ውጭ ያለውን ዓለም በሽውሽዌ ከተጠለፈችበት ጊዜ ጀምሮ አይታው አታውቅም፡፡ ለማምለጥ ብትሞክር በፈላታዎች ጥቃት ስለሚደርስባት አስባም የምታውቅ አይመስልም፡፡ ፈላታዎች ብዙም ልብስ መልበስ የለመዱ አይደሉም፡፡ በሬዎቻቸውም ሆነ እነርሱ የማሽተት ኃይላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አደጋ ከመጣባቸው አሊያም አበሻ እየቀረባቸው መሆኑን ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት አውቀው ይርቃሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አእዋፍም የሚታዘዟቸው ይመስላል፡፡ ወደ እነርሱ እየቀረበ ያለው ሰው ይሁን ሌላ አንበሳ ሁሉንም አእዋፍ ሊነግሯቸው እንደሚችል የወሬ ምንጮቼ ያረጋግጣሉ፡፡
የአካባቢውን ማኅበረሰብ ወባ፣ እባብና ሽውሸዌ ያጠቁታል፡፡ መርዛማ የበርሃ እባብ አለ፡፡ በእጽ የሚከላከሉት ሰዎችም አሉ፡፡ እርግጥ እባብ የሚከላከሉበት እጽ ከሱዳን አስማተኞች የተገኘ ነው አሉ፡፡ አዲስ አበባ እባብ ስለሌለ ጥበቡን ማወቅ እንጅ እጹን አልፈለግኩትም፡፡ ስለዚህ ይዤ አልተመለስኩም፡፡ ጥበቡንም አልቀሰምኩም፡፡ ደሞስ መሥራት አለመሥራቱን ሳላረጋግጥ እንደኔ ዓይነት ቶማስ (ተጠራጣሪ) እንዴት ይዞ ይመጣል? ሽውሽዌ ብዙ ሰው ታጠቃለች፡፡ አንድ ጊዜም እንዲሁ ከቋራ ወረዳ ወደ ገጠር የተላኩ አምስት ያክል ባለሙያዎች በሽውሽዌ ይጠቃሉ፡፡ ሕሊናቸው ነሁልሎ የሚሔዱበትን አቅጣጫ ሳቱ፡፡ ሽውሽዌ የተጠቃ ሰው ያለ አቅጣጫው ኃይሉ እስከሚያልቅ ድረስ መጓዝ ነው፡፡ የእነዚህ ባለሙያዎች ኃይል አልቆ ኖሮ ወደቁ፡፡ ወዳጆቻቸው ለመፈለግ ሞከሩ፡፡ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለሌላ መስክ (ፊልድ) የተላኩ ሰዎች በርሃ ውስጥ ወዳድቀው በክረምት ዝናብ ሣር በቅሎባቸው ተገኘ አሉ፡፡ እንግዲህ ስለ ሸውሸዌና ፈላታ ናይጀሪያውያን ካላይ ያወጋሁት በሙሉ በቋረኞች በተነገረኝ መሠረት እንጅ ከፈለታ በግ ውጭ ያየሁት አንድም ነገር የለም፡፡ እርግጥ ነው ሁሉምን ለማየት አይቻለም፡፡ ደግሞም አደገኞች ናቸው፡፡ ሽውሽዌን ልይ ብል ተመልሦ ይህን ሪፖርት ማን ያስነብባችኋል? ዘላኖቹንም ማግኘት ሌላው ከባድ ነገር ነው፤ ደግሞም የሚመጡበት ወቅት አላቸው እንጅ ዓመቱን በሙሉ አይኖሩም፡፡ እባብ እንኳን በእውን በናሽናል ጂኦግራፊ ሳየውም ውቃቢየ አይወደው፡፡ በወባ ለመለከፍ አንድ ቀን ማደር ይጠበቅብኛል፡፡ ሁሉንም ግን አልሻም፡፡ የሔድኩባት ፒክ አፕ ወደ ሸኽዲ ትመለሳች፡፡
ጊዜ ቢኖረኝ ኖሮ ብዙ ነገር የሚታይ ነበር፡፡ ወደ ደጋማው የቋራ አካባቢ ቴዎድሮስ ከተማ የሚባል አለ፡፡ እዚያ የአጼ ቴዎድሮስ የልጅ ልጆችና ዘሮች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እነርሱን የማግኘት እቅድ ነበረኝ፡፡ ጊዜም ገንዘብም ስለተመናመነ ብሎም ቀጣይ ጉዞ ስላለብኝ ያን በርሃ ትቼው መመለስ ግድ ይላል፡፡ ወጣሁም፡፡ ሸኽዲ ከተማ ባጃጅ ውስጥ ያነበብኩት ጥቅስ ለአካባቢ ምቹ (ኢንቫሮንመንት ፍሬንድሊ) ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ‹የሰው ትርፍ የለውም› የሚል ጥቅስ እዚህ ቦታ አይታሰብም፡፡ ትርፍ አትጫን የሚል ሕግ የለምና፡፡ ባጃጅ ውስጥ ያለው ጥቅስ ‹ጊዜን አይቶ የማይከዳ ዕውነተኛ ጓደኛ የበርሃ ጥላ ነው› ይላል፡፡ ከዚህ የበለጠ ዕውነት በዚህ አካባቢ የለም፡፡ ቀን ላይ አይቸዋለሁና፡፡
አሁን እየመሸ ነው፡፡ ጀምበር መዘቅዘቅ ጀምራለች፡፡ ወደ ጎንደር የሚሔዱ መኪናዎችም ብዙ የሉም፡፡ ወደፊት 161 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅብኛል፡፡ ያገኘዋት ሚኒ ባስ በዚያ ሙቀት ሰው ጥቅጥቅ አድርጋ ሞላች፡፡ ጋቢና ነበርኩ፡፡ ጋቢና ሾፌሩን ሳይጨምር ሦስተኛ ሰው ታከለልን፡፡ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ ዝም ብሎ መጓዝ ነው፡፡ ገንዳ ውኃን አለፈን፤ ደረቅ አባይ፤ ነጋዴ ባህር፤ አርሴማ፣ ሰራባ፣ ጭልጋ…. ጎንደር ምሽት ሦስት ሠዓት ሲሆን፡፡ ነገ ቀጣይ ጉዞ አለ፡፡ ወደ አርማጭሆ፡፡
በላንድ ማርክ ሆቴል የተደረገው የወልቃይት ጉዳይ ስብሰባ
የአርማጭሆን ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ግን ትናንት በጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል ስለነበረው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ስብሰባ የታዘብኩት ማስቀመጥ እሻለሁ፡፡ ሐሙስ እለት ላንድ ማርክ ሆቴል ስደርስ የእቴጌ ምንትዋብ የስብሰባ አዳራሽ ሞልቶ መፈናፈኛ አልነበረውም፡፡ ውስጥ ገብቼ አንዳንድ ነገሮችን ሪከርድ ለማድረግ ብሞክርም መሹለኪያ መንገድ ጠፋ፡፡ ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ ውጭ ላይ ሆኖ በሞንታርቦው የሚነገረውን ማዳመጥ ነበር፡፡ ስብሰባውን የአዘጋጁት የጎንደርና የዳባት አገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ወልቃይት ቀድም ባሉት ጊዜያት የቆላ ወገራ አካል ሆኖ አውራጃው ዳባት ነበር፡፡ በዚህም ይመስላል የዳባት የአገር ሽማግሌዎች ከጎንደር ከተማ ጋር በመቀናጀት ስብሰባውን የአዘጋጁት፡፡ ኮሚቴዎቹ የደረሱበትና እየገጠማቸው ያለውን ነገር ሲያስረዱ ሕዝቡ ላይ የቁጭት፣ የንዴትና የተስፋ ስሜቶች ተደባልቀው ይነበቡ ነበር፡፡ በዚሁ ሰሞን በወልቃይት፣ በጠገዴና በኹመራ አካባቢዎች ለሠፈራ ከመጡት የትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ በመኪና እየተጫኑ እየመጡ ‹‹ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለንም፤ ጸረ ሰላም ኃይሎችን አንታገስም…›› ወዘተ የሚሉ የማወናበጃና የማስፈራሪያ መፈክሮች በሰፊው የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተዋቸው ሲስተናገዱ ሰንብተው ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ተወላጆች ነን ላሉት እንኳንስ ሰላማዊ ሰልፍ ሊፈቀድ ቀርቶ የቤት ውስጥ ስብሰባም ተከልክለዋል፤ አማርኛ ሙዚቃ እንዳያደምጡ ተደርገዋል፡፡ አልፎም ወደ አገራቸው ለመሔድ ኬላዎችን ተሸለክልከው ነው፡፡
የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ከሆኑት መካከል ኮሎኔል ደመቀ የሚባሉት ይህን አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹የእነርሱን ትግሬነት እኛ አልካድንም፤ እኛ የምንለው የእኛም አማራነት ይታወቅ ነው፡፡ አማራ የሆነ ሰው እንዴት በግዴታ ትግሬ ሊሆን ይችላል? በግዴታ እንዴት ማንነት ሊሰጠን ይችላል? እኛ እኮ በትግርኛ መርዶ ሰምተን በአማርኛ የምናለቅስ ነን፤ በትግርኛ የሰርግ ጥሪ ተላልፎልን በአማርኛ የምንዘፍን ሕዝብ ነን፡፡ ሕወሓት ጭቆና ወደ ጫካ አስወጣኝ ብሎ እኛ ላይ ያልፈጸመው በደል የለም፡፡ አማራ ነን ብሎ መናገር ምንድን ነው ጸረ ሰላም የሚያስብለው? ጠመንጃ መያዝ ለወልቃይት ሕዝብ ተራ በጣም ተራ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ይህ የሚጠቅም ነገር ስላልሆነ በሕገ መንግሥቱና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ጥያቄያችን እየቀርብን ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የወልቃይት ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለማውገዝ የግድ አማራ መሆን አይጠበቅም፡፡ ትግሬዎች ራሳቸው ሕወሓትን በቃህ ሊሉት ይገባል›› በማለት በሰፊው አብራሩ፡፡ አቶ አታላይ ዛፌ የተባሉም በወልቃይት ሕዝብ በተለይ ደግሞ በሱዳን ወታደሮች እየተወሰዱ ስላለቁት የአማራ ወጣቶች፣ በሕወሓት ባለሥልጣናት ስለተደፈሩት ሴቶችና ተማሪዎች፣ ግሕንብ የምድር እስር ቤት ውስጥ ስላለቁት ወልቃይቴዎች በሰፊው ሲዘረዝሩ አንዳንዶች ያለቅሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ያጨበጭቡ ነበር፡፡ ፍጹም ድብልቅልቅ ያለ ስሜት፤ በቃ ደስታና ሀዘን፣ ተስፋና ተስፋ መቁረጥ፣ የዋህነትና በቀል፣ የአንድነትና የልዩነት…. ስሜቶች በአንድ ሰው ገላ ላይ ሳይታዩ አልቀረም፡፡
አንድ ስሙን ሳልሰመው ያለፈኝ የወልቃይት ተወላጅ ሁለቱን ወንድሞቹን የሕወሓት የጸጥታ ቡድኖች ወስደው እንዴት አሰቃይተው እንደገደሉበት ምስክርነቱን ሊሰጥ ማይክራፎኑን (የድምጽ ማጉያውን) ተቀበለ፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ምንም እንኳ ግፉ የተፈጸመው ከዐሥር ዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም ድረስ በሐዘኑ ልቦናው እንደተሰበረ ነው፡፡ ሊናገር ሲል ትናገው መከፈት አልቻለም፡፡ በዐይኑ እንባ ፈሰሰ፡፡ ድምጹ ተቆራረጠ፡፡ ብዙ በጣም ብዙ በስብሰባው የነበሩ ሰዎች ዝም ብለው ማዳመጥ አልቻሉም፡፡ የሰዎች ኪስ ሲንኮሻኮሽ ይሰማል፡፡ ሶፍት ወይም ማኅረም ፍለጋ ነበር፡፡ የዛሬ ዐሥር ዓመት የተገደሉ ሰዎች ዛሬ መርዶአቸው የተረዳ መሠለኝ፡፡ ወንድ ልጅ ሲያለቅስ ማየት አልወድም፡፡ ቀረጻ ላይ ነበርኩ፡፡ እንባየ ተናነቀኝ፤ ታገልኩት፤ አልቻልኩም ፈሠሠ፡፡
ግለሰቡ ወንድሞቹን ከእናታቸው ነጥለው ወስደው አሰቃይተው ገድለውበታል፡፡ እርሱም አገር አለኝ ብሎ ተመልሶ አያውቅም፡፡ እንኳን ወልቃይት ሊሔድ ቀርቶ ጎንደር ኹመራ መውጫን ወለቃን አልፎ አያውቅም፡፡ በሐዘን የተሰበረ ልብ ይገርማል፡፡ በወልቃይት ሕዝብ ላይ ሕወሓት የፈጸመው ግፍ በቀላሉ ተነግሮ እንደማያልቅ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ሰዎች ተገድለው በአዲ ረመጥ ከተማ በመኪና ላይ ተጭነው ለሕዝብ መቀጣጫ እንዲሆኑ እንደ ደርግ የቀይ ሽብር ሰለባዎች በዚህ ዘመን የተፈጸመው ከወልቃይት ሕዝብ ውጭ የትም አይኖርም፡፡ አማራ በግዴታ ወደ ትግሬነት የተቀየረው ከወልቃይት ሕዝብ ውጭ በአገራችንም በዓለማችንም አይኖርም፡፡ እውነታው ይሔ ነው፡፡ ከሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እኛም ጋ መጥታችሁ ጉዳዩን አስረዱን የሚሉ ጥያቄዎች ብዙ ነበሩ፡፡
ጎንደር ስሔድ ምሽት ላይ ብዙ ጊዜ ወደ አጼ በካፋ የባህል ምሽት ማዝገሜን አልተውም፡፡ ጥሎብኝ የዚህ የባህል ምሽት እወደዋለሁ፡፡ የዛሬው አካሔዴ ግን ለመዝናናት እንዳልሆነ ብናገር ተአማኒነት ስለማይኖረው ብዙም ምክንያት ማቅረብ አልሻም፡፡ ብዙ ዜጎቻችን በርሃብ ጠኔ የሚበሉትን አጥተው እየተቸገሩ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህንንም አይቻለሁ፡፡ በሰፊው ወደፊት ስለምሔድበት አሁን አልቀላቅልም፡፡ ቀን ላይ በወልቃይቶች ላይ የደረሰውን ስሰማ በእውነቱ እድሜ ልኬን በሐዘን የምኖርም መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ጠንካራ ፍጥረት ነውና የሐዘን ብዛት አጥንቱን አይሰብረውም፤ የመደሰቻ ሕዋሳቱን አያደነዝዝም እንጅ ትንሽ ብቻ በቂ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ አዝማሪ ምን አለ ለማለት ነበር የገባሁት፡፡
ተንኮለኛው ጋዜጠኛ ተስፋየ ገብረ አብ አንድ ጊዜ ጎንደር ሒጄ ሰማሁት ያላቸውን የአዝማሪ ግጥሞች አስታወስኩ፡፡
ጎንደር አገር ጠፍቶ ሲፈለግ ሌሊት
ቀን ታዲሱ ጋራ ሲሔድ አየሁት፤
በረከት አገሩ ስለናፈቀው
ዳሸን አናት ሆኖ አስመራን አየሁ፡፡
እነዚህን ግጥሞች ጎንደር በሔድኩ ቁጥር አዝማሪ ለአዝማሪ ቤት እየዞርኩ ልሰማቸው ፈልጌ አልተሳካልኝም፡፡ ግን የጎንደር አዝማሪ ከእነዚህ በላይ የግጥም ቅኔዎች ማሽሞንሞን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ይህን ግጥም በሕሊናችሁ በማሲንቆ አጃቢነትና በመረዋ የቡርቧክስ አዝማሪ ድምጽ ስሙት (ቡርቧክስ ከጎንደር ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ያክል የሚርቅ ማክሰኝት የምትሰኝ ከተማ ወደ በለሳ መውጫ በኩል ያለ የገጠር ቀበሌ ሲሆን የበርካታ አዝማሪዎች ቀዬ ነው)፡፡
ኧረ አገሬ ጎንደር ሸንበቆው ማማሩ፣
አገሬ ወስከንቢት ሸንበቆው ማማሩ፤
ኧረ አገሬ ቋራ፣ መተማ አርማጭሆ ሸንበቆው ማማሩ
አገሬ ወልቃይት፣ ቃፍታና ኹመራ ሸንበቆው ማማሩ፣
ቆርጠው ቆርጠው ጣሉት ለም-አገር እያሉ!
አዝማሪው አገሩን በሸንበቆ መስሎ ለም ለም የሆነው ሁሉ ተቆርጦ አንድም ለሱዳን አሊያም ለታላቋ የትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ መወሰዱን በቁጭት ነው በቅኔ የሚገልጸው፡፡ የሆነው ሆኖ በዚያ ቀን አብዛኛው በበካፋ የባህል ቤት ሲዘፈን ያመሸው ስለወልቃይት ነው፡፡ አንድ ራሰ በራ ድምጸ መረዋ አዝማሪ አለ፡፡ የድምጹ ነገር ወፍ ከሰማይ ያወርዳል፤ ወይንም በአገራችን አባባል ነብር ይጠራል፡፡ የፋሲል ደመወዝን ‹‹አረሱት መተማ፣ አረሱት ኹመራን የውም የእኛን እጣ፣ እነርሱ ምን ያርጉ ከእኛ ሰው ሲታጣ›› ያለ ጊዜ የምድር ቤት ውስጥ ያለው አዳራሽ በጩኸት ተናወጠ፡፡ መቼም በጩኸት ከኢያሪኮ ከተማ ውጭ የፈረሰ ግንብ አልሰማሁም እንጅ ያን እለት የነበረው ጩኸት ከዚህ ላይ ለመግለጽ ቃላት መፈለግ ግድ ይለኛል፡፡
አዝማሪው ያዘምራል፡፡ እንዲህ በማለት
ኧረ አገሬ ጎንደር ሰሜን ጃናሞራ ወልቃይት ጠገዴ፣
ለራበው እንጀራ ለጠገበው ጓንዴ!
ወደ መድረክ ሰው ሁሉ መቶ ብር መወርወር ጀመረ፡፡ በዚያ ምሽት ቤቱን አይቶ የማያውቅ እንግዳ ሰው ቢገባ የቤቱ ሕግ መስሎት መቶ ብር እንደሚወረውር በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ፡፡ መድረክ አካበቢ ወደ አዝማሪው ስመለከት ውር ውር የሚሉ አረንጓዴ ቢራቢሮዎች ባለማሲንቆውን ሸፍነውታል፡፡ አዎ ቢራቢሮዎች አይደሉም፤ የባለ መቶ ብር ኖቶች እንጅ፡፡ ከዚህ ቤት ውስጥ የታመቀ ብሶት ፈንድቷል፡፡ የተጠራቀመ ቁጭት ፈሷል፡፡ ወጣቱ ደሙ ፈልቷል፡፡ ባርነትን በቃህ የሚል ይመስላል፡፡ ማንም ይህን የተናገረ የለም፤ እኔ ግን እያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ ያለውን ስሜት አንብቤዋለሁ፡፡ ሊመርጅ የገባው የደህነንቱም ሰው ስሜት ቢሆንም!!
እስኪ አንድ ሰው እስክስታ እየመታ ሲያነባ፣ ግማሽ ፊቱ የብርሃን ጸዳል ወርሶት ግማሹ ግን የዳመነ ሲሆን፣ ውስጡን በነገር ሞልቶ መተንፈስ አልችል ሲል፣ ሁለት ፍጹም ተቃራኒ ስሜቶች በአካላቱ ላይ ሲነበቡበት ያያችሁት ሰው አለ? ወይስ ይህ ስሜት ገጥሟችሁ ያውቃል? እኔ በዚያ ቤት ውስጥና በዚያ ሰዓት ያየሁት ግን ይህ ነው፡፡ ቤቱን ሁለት ፍጹም ተቃራኒ መናፍስት ወርሰውት አምሽተዋል፡፡
የሚቀጥል