“ኑ፣ እንግደለውና በጉድጓድ ውስጥ እንጣለው”

ማኅበረ ቅዱሳን mk

image

“ኑ፣ እንግደለውና በጉድጓድ ውስጥ እንጣለው” ዘፍ. 37፡20 አትም ኢሜይል

ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘውን በረከት ለማግኘት ብዙ የደከመውና የተጋደለው፣ ከዚህም የተነሣ “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፣ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና” የተባለለት ያዕቆብ አሥራ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፡፡ ዘፍ.. 32፡28 ከእነዚህም መካከል አንዱ ዮሴፍ ነበር፡፡ ዮሴፍ ከልጅነቱ ጀምሮ በአስተሳሰቡና በተግባሩ ሁሉ ከሌሎቹ የያዕቆብ ልጆች የተለየ ነበር፡፡

ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ሲጠብቅ ሳለ እንኳ ወንድሞቹ እንደ ልጅነታቸውና እንደ ዘመኑ ነባራዊ ሁኔታ ያደርጉት የነበረው ነገር አያስደስተውም ነበር፡፡ ሆኖም እርሱ ወንድሞቹን “ይህ ነገራችሁና ድርጊታችሁ መልካም አይደለም” ብሎ ቢነግራቸው ስላልሰሙት ለአባታቸው ተናገረ፡፡

ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ “ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ” የሚለን፡፡ 37፡2 ይህም ማለት አባታቸው የልጆቹን ያልታረመ ድርጊት ተረድቶ በጊዜው ይመክራቸውና ያስተካክላቸው ዘንድ ዮሴፍ ለአባታቸው ተናገረ ማለት ነው፡፡

ሆኖም አስተሳሰቡና ግብሩ የተበላሸ ሰው ስህተቱን ሲነግሩት አይወድምና በዚህ ሁኔታ የዮሴፍ ወንድሞች አልተደሰቱም፡፡ ይልቁንም ዮሴፍን እየጠሉት ሄዱ፤ እነርሱ የሚፈልጉት የዋዛ ፈዛዛ ነገራቸውንና የስህተት ድርጊታቸውን አብሮ የሚያሟሙቅላቸውና የሚያዳምቅላቸው ሰው ነበር እንጂ እነርሱን የማይመሳሰል ሰው አልነበረም፡፡ እንዲሁም ይመክራቸው ዘንድ በማሰብ ድርጊታቸውን ለአባታቸው ስለ ተናገረ ዮሴፍን የበለጠ እየጠሉት ሄዱ፡፡

አባቱ እስራኤል ግን ዮሴፍ እንደ ሌሎቹ ልጆቹ በሥጋ የወለደው ብቻ ሳይሆን መንፈሱና አስተሳሰቡ ሁሉ እንደ እርሱ ስለሆነ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ወደደው፤ “እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር” እንዲል፡፡ ዘፍ. 37፡3 ሆኖም ይህ የዮሴፍ በአባቱ ዘንድ መወደድ ወንድሞቹ በቅንዓትና በምቀኝነት ዓይን እንዲመለከቱትና የበለጠ እንዲጠሉት አደረጋቸው፤ “ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፣ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም፡፡” ዘፍ. 37፡4

በዚያውም ላይ ከልጅነቱ ጀምሮ የልጅነት ነገር ለማያታልለውና አስተሳሰቡና መንፈሱ ሁሉ ከልጆች የተለየ አርቆ አሳቢና አስተዋይ ለሆነው ለዮሴፍ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ በሕልም ገለጠለት፡፡ ዮሴፍም ደግና የዋህ እንጂ የተንኮልና የክፋት ሃሳብ መኖሩን የማያውቅ ቅን ብቻ ስለ ነበረ እነዚያን ሕልሞቹን ለወንድሞቹ እንደ ወረደ ነገራቸው፡፡

“እርሱም አላቸው፡- እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፣ እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና እነሆም የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፣ የእናንተም ነዶዎች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ። ወንድሞቹም፡- በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛን ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት።” ዘፍ. 37፡6-8

ዮሴፍ እንደ ገና ሌላ ሕልምን አለመ፡፡ ያንን ሕልሙንም አሁንም ለወንድሞቹም ነገራቸው፡-

“ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፣ ለወንድሞቹም ነገራቸው፡፡ እንዲህም አለ፦ እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፡፡ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ። ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፣ አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፦ ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን? ወንድሞቹም ቀኑበት፣ አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር።” ዘፍ. 37፡9-11

እነዚህ እግዚአብሔር ለዮሴፍ የገለጠለት ሁለቱ ሕልሞች ከብዙ ጊዜያት በኋላ እግዚአብሔር ያደርገው ዘንድ ያለውን ነገር የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡ የወንድሞቹ ነዶዎች በዙሪያው ከብበው ለእርሱ ነዶ መስገዳቸው በእህል ምክንያት ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጥተው የሚሰግዱለት መሆኑንና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተፈጸሙትን ነገሮች አስቀድሞ የሚያሳዩ አመላካቾች ነበሩ፡፡ የፀሐይ የጨረቃና የአሥራ አንዱ ከዋክብት ለእርሱ መስገድም እንዲሁ፡፡

ሆኖም የዮሴፍ ግላዊ ሰብእና፣ ከዚህ የተነሣ በአባቱ ዘንድም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ መሆኑና ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የሚያሳይ ሕልሞ የተገለጠለት መሆኑ በወንድሞቹ ዘንድ አልተወደደለትም፡፡ ይልቁንም ዮሴፍ አድጎ በሕልም የተነገረውና ይነግሥብናል ብለው የፈሩት ነገር ደርሶባቸው ላለማየት ሲሉ እርሱን ለማጥፋት ቆርጠው ተነሡ፡፡

ለዚህም አባቱ ዮሴፍን እነርሱ በግ ወደሚጠብቁበት ቦታ ስንቃቸውን ይዞ እንዲሄድና እንዲጠይቃቸው በላከው ጊዜ በዚያ በምድረ በዳ ከእጃቸው የሚያድነው ሌላ ማንም ሰው ስላልነበረ ያን አጋጣሚ ተጠቅመው ሊያጠፉት በቁርጥ ወሰኑ፡፡ እርሱ በየዋህ ልቡናው እነርሱ ያሉበትን ቦታ በብዙ ድካም ፈልጎ ወደዚያ ሲደርስና ስንቃቸውን ተሸክሞላቸው ሲመጣ እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተሰብስበው ተነጋገሩ፡፡

ዘጠኙ ወንድሞቹ በሙሉ (ቢኒያም አልነበረም፣ ሮቤል ከእነርሱ ሃሳብ ጋር አልተስማማም፣ ሌላው ራሱ ዮሴፍ ነው) አንድ ሆነው እርሱን ለመግደል ወሰኑ፤ “እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፣ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ።” ዘፍ. 37፡18 ስለዚህ የዮሴፍ ወንድሞች የስብሰባ ውሳኔ (የአቋም መግለጫ) “ዮሴፍን እንግደለው” የሚል ነበር፡፡

ዮሴፍን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የወሰኑት የራሱ የዮሴፍ ወንድሞች የተከተሏቸው ዋና ዋና ስልቶች የሚከተሉት ነበሩ፡-

1. አንደኛው ስልት – የዮሴፍን ግብር አክፋፍቶ መሣልና ዮሴፍ ሞት የሚገባው ወንጀለኛ እንደሆነ አድርጎ መናገር ነበር፡፡ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሕልም እነርሱ ግን እንደ መክሰሻ ተጠቀሙበት፡፡ “ያ ሕልመኛ መጣ” እያሉ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሕልም መናገሩን ወንጀል አስመስለው ስሙን ማጥፋትንና ግብሩን ማክፋፋትን ሥራዬ ብለው ተያያዙት፡፡

ለእነርሱ የሚያስበው ቅኑ ዮሴፍ ከብዙ ፍለጋ በኋላ ካሉበት ቦታ ሲደርስና ወንድሞቼን አገኘኋቸው ብሎ ደስ እያለው ሳለ እነርሱ ግን ዮሴፍን ክፉ ሰው እንደ ሆነ እያስመሰሉ አንዱ ለሌላው መናገር ጀመሩ፡፡ እንዲህም ተባባሉ፡- “አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። አሁንም ኑ፣ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፣ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን።” ዘፍ. 37፡19-29

በዚህ ዓለም ሲፈጸሙ ስለ ኖሩ ነገሮች ከታሪክ እንደምንማረው ሰዎች ሊያጠፏቸው የሚፈልጓቸውን ሰዎች አስቀድመው የሚያጠፉት ስማቸውንና ግብራቸውን ነው፡፡ በመጀመሪያ የሰብእና ግድያ (Character assasination) ይፈጽሙባቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሰብእናቸውና ማንነታቸው ጥላሸት ተቀብቶ ወንጀለኛ መስለው እንዲታዩ ተደርገው የተሣሉትን ሰዎች የፈለጉትን ማድረግ ቀላል ነው፡፡

ዮሴፍን የመሰለውን የልጅ አዋቂ ሰው፣ እግዚአብሔር የገለጠለትን ነገር ስለ ተናገራቸውና ገና ለገና ወደ ፊት በእኛ ላይ ይሠለጥንብን ይሆናል ብለው ስለ ፈሩ ሕይወቱን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቆርጠው ተነሡ፡፡ የራሱ ወንድሞች የሆኑት ሰዎች ስለ ክፉ ግብራቸው የሚወቅሳቸው ሰው ሳይኖር እንዳሻቸው መሆን ይችሉ ዘንድ የዮሴፍን ስም ማጥፋት የመጀመሪያው ተግባራቸው ነበር፡፡ በነውራቸው ሊወቀሱና ሊገሠጹ ይገባቸው የነበሩት ሰዎች ለእነርሱ በማሰብ ስህተታቸውን እንዲያርሙ የነገራቸውን ዮሴፍን ወንጀለኛ አስመስለው ሣሉት፡፡

“ከእኛ ሊበልጥ ነው፣ ሊገዛን ነው” በሚለው ደካማ የቅንዓትና የስጋት አስተሳሰባቸው ምክንያት እግዚአብሔር ስለ ዘላቂው ሁኔታ በዮሴፍ የገለጠውን ታላቅ ነገር ለማጥፋት ተነሡ፡፡ ለዚህ ነበር “ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት” ብሎ ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን፡፡ ዘፍ. 37፡23 ይህን ያደረጉትም ዮሴፍን ክብር የማይገባው፣ የውርደት ሰው፣ የሞት ሰው ነው ለማለት ነበር፡፡

የእነዚህ ልጆች የሆኑት አይሁድ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን “ወንጀለኛ ስለሆነ የሞት ሰው ነው፣ ሞት ይገባዋል” ለማለት በዕለተ ዓርብ ልብሱን ገፍፈው ከለሜዳ ያለበሱት ለዚህ ነበር፡፡ “ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት” እንዲል፡፡ ማቴ. 27፡28

2. ሁለተኛው ስልት ደግሞ – ዮሴፍን ለማዳን ይፈልግ የነበረውን ብቸኛውን ሰው ሮቤልን ማስመረርና ከእነርሱ መካከል እንዲወጣ ማድረግ ነበር፡፡

ከዮሴፍ ወንድሞች መካከል ለዮሴፍ መልካም ሃሳብ የነበረውና ከክፉዎች ወንድሞቹ እጅ ሊታደገው ይፈልግ የነበረው ሮቤል ብቻ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሮቤልን ሁኔታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-

“ሮቤልም ይህን ሰማ፣ ከእጃቸውም አዳነው፤ እንዲህም አለ፦ ሕይወቱን አናጥፋ፡፡ ሮቤል፣ ደም አታፍስሱ፣ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፣ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው።” ዘፍ. 37፡21-22

ሆኖም የዮሴፍ ጠላት ሆነው ከተነሡት የራሱ ወንድሞች ብዙ ኾነው (ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ዛብሎን፣ ይሳኮር፣ ዳን፣ ጋድ፣ አሴር፣ ንፍታሌም – ዘጠኙ በአንድ ላይ) በዮሴፍ ላይ መጮኽ የተነሣ ሮቤል እንዲገለልና ብቻውን እንዲቆም ሆነ፡፡ ከእነርሱ ዮሴፍን የመወንጀልና “እንግደለው” ከሚለው ጩኸታቸው የተነሣም ሮቤል ተማርሮና ተሰላችቶ ከእነርሱ መካከል እንዲወጣና ዘወር እንዲል አደረጉት፡፡

ሮቤል ወንድሞቹ በዮሴፍ ላይ በሚያሰሙት “ያ ሕልመኛ፣ ኑ እንግደለው፣ ወዘተ” የሚሉ የማያባሩ የጥላቻ ጩኸቶች የተነሣ ተማርሮና ተሰላችቶ ከእነርሱ መካከል ወጣ ሲልላቸው ደግሞ ያችን የሚፈልጓትን “መልካም” አጋጣሚ ተጠቅመው ዮሴፍን ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች ሸጡት፡፡ እነዚያ ነጋዴዎች ደግሞ ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በአጠቃላይ በዓለም ሲሆኑ ከነበሩት ድርጊቶች ታሪክ የምንረዳው ይህን የመሰሉ ስልቶች ጥቅም ላይ ሲውሉና እንዲህ ያሉ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ መኖራቸውን ነው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ አገረ ስብከት አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የቀረበው መነሻ ሃሳብና ከአንዳንድ ተሳታፊዎች የተሰጡት አስተያየቶች የዮሴፍ ወንድሞች በዮሴፍ ላይ የነበራቸውን ጥላቻና እርሱን ለማጥፋት ያመቻቸው ዘንድ “ያ ሕልመኛ መጣ” እያሉ የጮኹበትን ጩኸት ከሦስት ሺህ በላይ ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን እንድናስታውስ አድርጎናል፡፡

የአንዳንድ አድባራትንና ገዳማትን እልቅና (አለቅነት) ቦታው የሚጠይቀው መንፈሳዊነትና ትምህርት ሳይኖራቸው በተለያዩ መንገዶች የያዙት እነዚህ ግለሰቦች ምእመናን ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው አንጀታቸውን አስረው ለቤተ ክርስቲያኔ አገልግሎት ያስፈልጋል ብለው በሚሰጡት አሥራትና አስተዋጽኦ መበልጸጋቸው ሳያንስ ይኸው ሁኔታ ያለ ምንም ተቃውሞና ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ በዚህ የዝርፊያ መብታቸው ላይ የሚነሣባቸውን ማንኛውንም ግለሰብም ሆነ አካል እንደ ዮሴፍ ሊያጠፉት ቁርጠኞች ናቸው፡፡
ከሁሉ አስቀድመን በትሕትና ማሳሰብ የምንፈልገው ይህ ጽሑፍ የሚመለከተው ተከሳሹ እንኳ ቀርቦ እንዲያስረዳ አንዳች እድል ባልተሰጠበትና አሳዛኝ በሆነው የክስ ስብሰባ ላይ የተናገሩትን ሰዎችና የእነርሱንም ሃሳባቸውንና ግብራቸውን ብቻ እንጂ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሌሎች አባቶችን የሚመለከት አይደለም፡፡ በስብሰባው ላይ አንዳንዶቹ ተናጋሪዎች ሲናገሩ ኃፍረትና ሐዘን እየተሰማቸው ፊታቸውን ሲሸፍኑና ሲያዝኑ የነበሩ ብዙ አባቶች የነበሩ መሆናቸው ግልጽ ነውና፡፡

መልእክት ማስተላለፍ የፈለግነውም የተነገረው ነገር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም መሆኑ ሳይለይ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደንታ ቢስ በመሆን ከውንጀላ አንጻር በቀረበው ሃሳብ ላይ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ህልውና ከልብ የሚያስቡና የሚሠሩ አባቶችና ምእመናን የማኅበሩን አገልግሎት በእጅጉ የተረዱና ከጎኑ የቆሙ ናቸው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ማለትም የእነዚህ አባቶችና ምእመናን የጋራ የአገልግሎት ማኅበር እንጂ ሌላ ማንም ማለት አይደለም፡፡ ይህም መስከረም 29 ቀን በአዲስ አበባ አገረ ስብከት በተካሄደው ስብሰባ ላይ እና ሰሞኑን ከጥቅምት 5 ጀምሮ በተካሄደው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በሰፊው እየተንጸባረቀ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በዓመታዊው የሰበክ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የመጡት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች

በየአገረ ስብከታቸው ማኅበረ ቅዱሳን ከእነርሱ ጋር በመተባበር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሠራቸውን ሥራዎችና ያደረገላቸውን ድጋፎች በሰፊው ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ማኅበረ ቅዱሳን የሠራቸውን ሥራዎች ሲያቀርቡ ከጉባኤው አባላት ይደረግላቸው የነበረው ጭብጨባና ድጋፍም በእጅጉ ልዩ ነበር፡፡ ይህም ከሳሾቹን ማንነታቸው እንዲታወቅባቸና ብቻቸውን ተነጥለው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመኑን የዋጀ አሠራር ማስፈለጉ ታምኖበት በባለ ሞያዎች አማካይነት እንዲጠናና እንዲዘጋጅ ተደርጎ ለትግበራ ሂደት ላይ ሳለ እነዚሁ አሁን ካለው ለዘራፊዎች ምቹ የሆነ አሠራርና አጠቃላይ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆኑ አካላት ባደረጉት ነውረኛ ተቃውሞና ግፊት ምክንያት እስካሁን በሥራ ላይ እንዳይውል አድርገውታል፡፡

እነዚሁ በቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ዘረፋ የከበሩት ግለሰቦችና የውስጥና የውጭ አጋሮቻቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በባለ ሞያዎች ያስጠናውንና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ በምልዐተ ጉባኤው ተመልክቶ በእጅጉ ያመሰገነውን የአሠራር ሥርዓት ለመቃወም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተፈቅዶላቸው ስብሰባዎችን ማድረጋቸውም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

አሁንም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ለማደም መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ. ም. የተጠራውን ስብስባ በፍታውራሪነት ያስተባበሩት እነዚሁ አካላት ከመሰሎቻቸው ጋር መሆኑን አንደኛው ተናጋሪ “እንጀራው ይቅርብን፣ ሥራው ይቅርብን ብለው ቆርጠው ተነሥተው ከዚህ አቋም ያደረሱት ሁለት ወንድሞቻችንን (በስም ጠቅሰዋቸዋል) አመስግኗቸው” በማለት ገልጸውታል፡፡

በእነዚህ አሳፋሪ ስብሰባዎቻቸው ላይም በዋናነት ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ዋና አጥፊ ኃይል እያደረጉ ጥላሸት ሲቀቡና ሲፎክሩ ነበር፡፡ የዚህ አንዱ ምክንያትም አዲሱን አሠራር ያጠናው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ብለው ስላሰቡ ነው፡፡ ይህ የአሠራር ሥርዓት ተግባር ላይ ከዋለ የለመዱትን ባለቤት የሌለው የሚመስለውን ገንዘብ እንዳሻቸው መዝረፍ ስለሚያስቸግራቸው አስቀድመው ከፊት እየቆሙ መንገድ በመዝጋት ላይ ይገኛሉ፣ እስካሁንም ሃይ ባይ አላገኙም፡፡

እንዲያውም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባሉት መዋቅሮች ችግሩ ሰርጎ በመግባት በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ላይ መሰናክል እየፈጠረ መምጣቱ የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ ያውቁብናል፣ ከመዝረፍ መብታችን ያሰናክሉናል የሚሏቸውን ሁሉ ለማጥፋትና ለመክሰስ መድረኩ ለእነርሱ የተሰጠ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል የሚያውቀው የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በቅርብ ጊዜ እስካሁን በሥራ ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሂሳብ አሠራር ሥርዓት ኋላ ቀርና ለቁጥጥርም ሆነ በአጠቃላይ ለአሠራር ከማያመቸው ከነጠላ የሒሳብ አሠራር ሥርዓት (Single Entry Accounting System) ተላቅቆ ለአሠራርም ሆነ ለቁጥጥር ወደሚያመቸውና ዘመናዊ ወደ ሆነው ወደ ሁለትዮሽ የሒሳብ አሠራር ሥርዓት (Double Entry Accounting system) እንዲለወጥ ወስኗል፡፡ ይህ ዜና ለቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ ልጆች መልካም ዜና ቢሆንም ለዘራፊዎቹ ግን መርዶ ነው፡፡ አሁንም ይህን የወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ስማቸውን ማጥፋቱን ተያይዘውታል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በግልጽ የታየውም ይኸው ነው፡፡

እንደዚሁም “ጉሮሯችን ላይ ይቆምብናል፣ ዝርፊያችንን ያስቀርብናል” ብለው የሚፈሩትን ማኅበረ ቅዱሳንን የዮሴፍ ወንድሞች “ያ ሕልመኛ መጣ፣ ኑ እንግደለውና በአንድ ጉዳጓድ ውስጥ እንጣለው” እንዳሉት እነርሱም ማኅበረ ቅዱሳንን ስሙን ጥላሸት በመቀባትና ወንጀለኛ አስመስሎ በማቅረብ “ኑ እንግደለው” እያሉ ነው፡፡ በስብሰባው ላይ የሚገርሙ ብዙ የፈጠራ ክሶች ተሰንዝረዋል፡፡

በእውነቱ ትዝ ካሏቸው ክፉ የመክሰሻ ቃላት የቆጠቡት ያለ አይመሰልም፡፡ “ገንዘቡን ፖለቲካ እየሠራበት ነው፣ መንግሥት እየተጠቃበት ነው፣ ምእመናን እየተበታተኑበት ነው፣ ፈጣሪ የለም ይላሉ፣ የካህናት ፈጣሪዎች እኛ ነን ይላሉ፣ የጳጳሳት ፈጣሪዎች እኛ ነን ይላሉ፣ እነርሱ ካሉ እኛ ነገ የለንም፣ ምእመናኑን ዘረኛ አድርገውታል፣ በብሔር በመንደር እንዲከፋፈል አድርገውታል፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከማበላሸት ውጭ የሠራው ጠቃሚ ነገር የለም፣ አሜሪካ ሌላ ሦስተኛ ሲኖዶስ ሊያቋቁም ነው፣ የማኅበሩ አባላት እያንዳንዳቸው በግላቸው አራት አራት ፎቅ አላቸው፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን ያዳክማል፣ አሥራት በኩራትን ለራሱ ይወስዳል፣ ማኅበሩ አሸባሪ ነው፣ አክራሪ ነው፣ ወዘተ” የሚሉ ዘመኑ ያመጣቸውን ቅጽሎች በመጠቀም ውንጀላዎችን ያቀረቡት ለዚህ ነው፡፡

ማኅበሩ ቶሎ ጠፍቶ ለማየት ከመቸኮላቸው የተነሣም “ቁራጭ ደብዳቤ ይበቃዋል፣ የማኅበረ ቅዱሳንን ነገር እስከ ጫፍ አድርሱልን፣ እስካሁን ቢዘገይም ይህ ነገር ቶሎ መጥፋት ያለበት ጉዳይ ነው፣ በቶሎ ቁረጡት . . .” እያሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እንዲያውም አንደኛው የራሳቸውን ምኞት ይሁን አይዞህ ያላቸው ሰው ወይም አካል የነገራቸውን ይዘው፣ “ከመጨረሻው ደርሰናል” ብለዋል፡፡

ክፉዎቹ የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍን አባቱ የሰጠውን ልብሱን እንደ ገፈፉትና ሊሞት የሚገባው ነው እያሉ እንደ ጮኹት እነዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ ከሰጠው ተግባርና ኃላፊነት፣ እንዲሁም ግብሩ ከሚመሰክረው ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ስም በመስጠት የማኅበሩን ማንነትና ተግባር ሌላ መልክ ለመስጠት አጋጣሚውን አሟጥጠው ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ ነገሩ “ገበያ ቢያመቻት እናቷን ሸጠቻት” እንደ ተባለው ዓይነት ሆኗል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተጀመረው የዚህ ዘመቻ ሌላው ገጽታ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሰርገው የገቡ የተሐድሶ መናፍቃንና ውጫዊ አጋሮቻቸው ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮና እምነት ያላቸው የተሐድሶ አራማጆች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመቆጣጠርና ፕሮቴስታንት ለማድረግ ውስጧ ገብተው መዋቅሯን ተጠቅመው ወዳሰቡት ግብ ለመድረስ መሥራት ከጀመሩ ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ ይህም ራሳቸው ተሐድሶዎቹ በይፋ በሚጽፏቸው መጻሕፍት፣ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎችና በከፈቷቸው ብሎጎች እየገለጹት ያለ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

እነዚህ አካላት እኩይ የሆነ ሰይጣናዊ ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስ መሰናክል ይሆንብናል ብለው የሚፈሩት ማኅበረ ቅዱሳንን መሆኑን በተለያዩ ጊዜያትና መንገዶች ራሳቸው ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ያሉ ጌቶቻቸውና ተልእኮውን የሰጧቸው ላኪዎቻቸውም ለክርስቲያኖች መብት እንቆማለን በሚሉ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና ተቋማት ስምና ሽፋን በሚያወጧቸው ሪፖርቶች በኢትዮጵያ ውስጥ “ክርስቲያኖችን የሚያሳድደው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” እያሉ በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ አስርገው ላስገቧቸው ሰዎች የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም እነዚህ የተሐድሶ አራማጅ ኃይሎች ቤተ ክርስቲያኒቱን በማዳከምና ተቋማቷን በመቆጣጠር ፕሮቴስታንት ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳንን “አሸባሪ፣ አሳዳጅ፣ አክራሪ” እያሉ ስሙን በማጥፋትና ከቻሉም በማንኛውም መንገድ ህልውናው እንዲያከትም በማድረግ ያለ ማንም ከልካይና መሰናክል ዓላማቸውን ከዳር ለማድረስ ይሠራሉ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከእምነቷና ከአስተምህሮዋ ተቃራኒ የሆነ ነገር እየናኘ ያለው ተሐድሶ አጀንዳ ሊሆን ሲገባው ጉዳዩ ተገልብጦ እነዚህን ጸረ ቤተ ክርስቲያን የሆኑ አካላትን በተመለከተ ምእመኑ ማንነታቸውን እንዲያውቅና ራሱንና ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠብቅ፣ እንዲሁም ተገቢውን ውሳኔ ለመወሰን ይረዳቸው ዘንድ አስፈላጊውን መረጃ ለቤተ ክርስቲያን አባቶች በማቅረብ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት የድርሻውን እያደረገ ያለውን ማኅበረ ቅዱሳንን መክሰስ መሆኑ የሚገርም፣ የሚያሳዝንም ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ ተሰግስገው ቤተ ክርስቲያንን ወዴት እየወሰዷት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህ አካሄድ የሚያሳየው ተሐድሶዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ዘልቀው ገብተው ጉዳዮችን ለራሳቸው በሚያመቻቸው መንገድ ጠምዝዘውና ሌላ መልክ ሰጥተው ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሯቸውን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማስፋፋት የጀመሩትን ዘመቻ ዳር ለማድረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ የራሳቸውን እምነት ማራመድ መብታቸው ነው፡፡ ሆኖም የራሳቸውን እምነት በኦርቶዶክሳውያን ላይ ለመጫን የሚያደርጉት ተግባር ግን በምንም መንገድ ተቀባይነት የለውም፣ ሊኖረውም አይችልም፡፡
አርዮሳውያን በአራተኛው መቶ ዓመት የተለያዩ ባለ ሥልጣናትንና ስልቶችን በመጠቀም ኦርቶዶክሳውያን አባቶችንና ምእመናንን እያሳደዱ አርዮሳዊ ኑፋቄያቸውን ሲዘሩና ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ሲያውኩ የነበረበት ዘመን እንዳይደገም አባቶችና ምእመናን ሁኔታዎችን በጥልቀት ማሰብና መገንዘብ የግድ የሚልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት ያልተለያዩ በነበሩባቸው በእነዚያ ዘመናት የተፈጸመው አሁን መንግሥትና ሃይማኖት በተለያዩበት ዘመን ይሆናል ብለን ባናስብም መንግሥትም ከወዲሁ ልብ ሊለው እንደሚገባ ማሳሰብ ግን ጉዳት ያለው አይመስለንም፡፡

እነዚህ አካላት በስብሰባው ላይ “ማኅበረ ቅዱሳን ሰዎችን ተሐድሶ ይላል፣ መናፍቅ ይላል፣ የእኛን አባቶች ይነቅፋል፣ ሰዎችን ይከስሳል . . .” እያሉ ሲከስሱ ተደምጠዋል፡፡ በመጀመሪያ እነርሱ እንዲህ ሲሉ ምን እያደረጉ ነው? እየከሰሱ አይደለምን? ታዲያ ለእነርሱ ሲሆን ትክክል፣ ለማኅበረ ቅዱሳን ሲሆን ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው? ሁለተኛ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ ያላወገዘውን ወይም ደግሞ ራሳቸው ለይቶላቸው “ተሐድሶ ነን” ብለው በይፋ የገለጡ ሰዎችን ካልሆነ በስተቀር ማንንም ሰው በመጽሔትም ሆነ በጋዜጣ “መናፍቅ ነው፣ ተሐድሶ ነው” ብሎ አውጥቶ አያውቅም፡፡

በሦስተኛ ደግሞ አንድ ሰው እምነቱና አስተምህሮው ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወጣና ተሐድሶ መሆኑን ራሱ በቃሉ እየተናገረና በግብሩ እየመሰከረ እያለ ይህን ሰው “ተሐድሶ ነው አትበሉ” ማለት መናፍቃን ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዳሻው ይፈንጩባት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ ከሚሉ ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይህ በእግዚአብሔርም ዘንድ ሆነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስጠይቃል፡፡ መቸም መች ተቀባይነት ሊኖረውም አይችልም፤ ጉዳዩ የሃይማኖት ጉዳይ ነውና!

በዚሁ ጥቅምት 27 ቀን፣ 2007 ዓ. ም. በአዲስ አበባ አገረ ስብከት አዳራሽ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመክሰስና ብሎም ለመስቀል በመቋመጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከተናገሩት ተናጋሪዎች መካከል አንደኛው እንዲህ ነበር ያሉት፡- “የጥንት አባቶች የተለያዩት በሃይማኖት እኮ አይደለም፣ ውሸት እኮ ነው፡፡ የተለያዩት በገንዘብ እኮ ነው፣ በሥልጣን እኮ ነው፡፡” ይህን ስንሰማ በአንድ በኩል ማኅበረ ቅዱሳንን የወቀሱበት የእውቀት ችግር እነርሱም ላይ ምን ያህል በጥልቀት መኖሩን ሲያሳብቅባቸው በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሰዎች ጉዳያቸው ሃይማኖት ሳይሆን ገንዘብና ገንዘብ ብቻ መሆኑን በግልጽ ያሳየናል፡፡

ለመሆኑ ቅዱስ አትናቴዎስና አርዮስ የተጣሉት ለገንዘብ ነበር? ለሥልጣን ነበር? ሠለስቱ ምእት በዚያ ዘመን በነበረው አስቸጋሪ የመጓጓዣ ሁኔታ ከየአገረ ስብከታቸው ተጉዘው ኒቅያ ተገናኝተው አርዮስን ከነ ተከታዮቹ ያወገዙት ለሥልጣንና ለገንዘብ ነበርን? እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮትና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እና ሌሎቹም አንድ መቶ ሃምሳው አባቶቻችን በቁስጥንጥንያ ተሰብስበው ከመቅዶንዮስና ከአቡሊናርዮስ ተከታዮች እንዲሁም ከተለያዩ መናፍቃን ጋር የተከራከሩትና አልመለስ ያሉትን አውግዘው የለዩትስ በእናንተ እውቀት መሠረት ለሥልጣንና ለገንዘብ ኖሯልን? እነ ቅዱስ ቄርሎስ፣ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ እነ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ፣ እነ ቅዱስ ፊልክስዮስ ከንስጥሮሳውያንና ከልዮናውያን ጋር ዕድሜ ልካቸውን ሲጋደሉ የኖሩትስ ለገንዘብና ለሥልጣን ኖሯልን?

እስኪ የማኅበረ ቅዱሳንን ጉዳይ ለጊዜው ተወት እናድርገውና ለኦርቶዶክሳዊት እምነት መጠበቅ የደከሙትና የተጋደሉት፣ ብዙ መከራ የተቀበሉትና ሕይወታቸውን ሳይቀር የሰጡት የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አባቶች ዐጽማቸው ይወቅሰናል፣ አምላካቸው ይፈርድብናል ብላችሁ እንኳ ለምን አልፈራችሁም? የቤተ ክርስቲያኒቱ አሳቢዎችና ተቆርቋሪዎች ነን ባዮች፣ የማኅበሩም ከሳሾች እንግዲህ እነዚህ ዓይነት ናቸው!

ከቤተ ክርስቲያኒቱ የጠፉ ምእመናን ጉዳይም ከገንዘብና ከገቢ አንጻር መቃኘቱ ይህንኑ ያሳያል፡፡ እንደዚሁም አንደኛው ተናጋሪ “የኪስ ገንዘቦቿና ቋሚ ሀብቶቿ የሆኑትን ምእመናንን ከተቀራማቾች ካልጠበቅናቸው (ተናጋሪው ከማኅበረ ቅዱሳን ማለታቸው ነው) አገልጋዮቿ ዛሬ በቀላሉ የምንገምጠውን ዳቦ ነገ ፍርፋሪውንም እንደማናገኘው መታወቅ አለበት” ሲሉ የተናገሩትም ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚፈልጓት “ለዳቦ መግመጫ” እንድትሆናቸው እንጂ የሰው ልጆችን ለማዳን ከእግዚአብሔር የተሰጣትን ተልእኮ ከመወጣት አንጻር አለመሆኑን ነው፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ስሌቱ ገንዘብና ዳቦ መሆኑ አሳዛኝ፣ አሳፋሪም ነው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባሉበት ጉባኤ ይህንና ይህን የመሰሉ ብዙ ጸያፍና አስነዋሪ ነገሮች መነገራቸው፣ መነገራቸው ብቻም ሳይሆን እንደ እውነት ተቆጥረው ማስተካከያ ሳይሰጥባቸው ዝም መባላቸው፣ ከዚያም አልፎ መበረታታታቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡ በአደባባይ የተነገረና ሆን ተብሎ እየተሰራጨ ያለ ነገር ባይሆንብን ኖሮ እኛም ባንጽፍበት በእጅጉ እንመርጥ ነበር፡፡ ግን ሆነና ምን ይደረግ!

እነዚህ ሁለት አካላት – የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት እንዳሻቸው ሲመዘብሩና ሲዘርፉ ለመኖር የሚሹት እና ፕሮቴስታንታዊ ዓላማቸውን በመፈጸም ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ አስተምህሮንና ይትበሃልን በሙሉ አጥፍቶ በፕሮቴስታንታዊ ሉተራዊ ባህል ለመተካት የሚሠሩት ተሐድሶዎች – በጋራ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማጥፋት ቆርጠው ከተነሡ ውለው አድረዋል፡፡

ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን የተባሉት በእምነታቸውና በአስተሳሰባቸው የተራራቁ የነበሩት የአይሁድ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማጥፋት ግን በአንድነት ተስማምተውና ተባብረው ነበር፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፣ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ” እንዲል፡፡ ማቴ. 26፡3-4 እነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቷ ገንዘብ ዘራፊዎችና ተሐድሶዎችም እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማጥፋት የጋራ ኅብረት ፈጥረው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ጋር ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ኦሪቱ የመሥዋዕት ፍየል (Scapegoat) ጭዳ አድርገው አሳልፈው ለመስጠት አሰፍስፈው ተነሥተዋል፡፡ ዘሌ. 16፡8 ይህ የሚደረገው ሰዎች በችግር ሲጠመዱና ችግራቸውንም መፍታት አልችል ሲሉ ራሱን የመከላከል፣ መልሶ የመከራከርና የማስረዳት ዓቅም የለውም ወይም ወቅቱና ሁኔታው አይፈቅድለትም ብለው በሚገምቱት በአንድ በሆነ አካል ላይ ያን ችግራቸውን ይለጥፉበታል፡፡ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስም ኃይላቸውን አሟጠው ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ እየተሯሯጡ ናቸው፡፡

እነርሱ ይህን ፈሊጥ እየተከተሉ ቢሆንም የእውነት አምላክ ስላልፈቀደላቸው አልተሳካላቸውም፡፡ ስለዚህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉ ችግሮች ሁሉ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ተለጥፈዋል፡፡ ለምእመናን ቁጥር መቀነሱ ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳን፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መዳከም ተጠያቂው ማኅበረ ቅዱሳን (“ቤተ ክርስቲያኒቱ ጠንካራ የነበረችው እነርሱ ሳይኖሩ ነበር ተብሏልና”)፣ ፓትርያርክ ለመሰደቡ ምክንያቱ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ብቻ አሉ ብለው እውቅና የሰጧቸውን ችግሮች ሁሉ እንደ ኦሪቱ የመሥዋዕት ፍየል ይሸከማቸው ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን ራስ ላይ ለመጫን ተሞክሯል፡፡

የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍን ለመሸጥ እንዲያመቻቸው የዮሴፍን ስም ጥላሸት በመቀባት አሳቅቀውና አስመርረው ለዮሴፍ ብቸኛ ተቆርቋሪና ጠበቃ የነበረውን ታላቅ ወንድማቸውን ሮቤልን ከእነርሱ ተለይቶ እንዲወጣ እንዳደረጉትና በዚያ ክፍተት ተጠቅመው ዮሴፍን እንደ ሸጡት ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶችና ምእመናንም ተረፈ አይሁድ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ዘራፊዎችና የተሐድሶ አራማጆች “ያ ሕልመኛ መጣ፣ እንሽጠው፣ ኑ እንግደለው፣ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው” እያሉ የሚጮኹት የሐሰት ጩኸታቸው ሳያሰለቻቸውና ወደ ኋላ ሳያስብላቸው እውነቱን ከሐሰተኛ ጩኸት በመለየት በርትተው መታገልና ለሃይማኖታቸው ዘብ መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለማኅበረ ቅዱሳን አስቀድመው “አሸባሪ፣ አክራሪ፣ ወዘተ” የሚሉ ታርጋዎችን የሚለጥፉት ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና ቀኖና፣ ለይትበሃሏና ለማንነቷ ያለውን ተቆርቋሪነትና በእግዚአብሔር ቸርነት እያደረጋቸው ያሉትን መልካም ተግባራት የሚያውቁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት፣ እንዲሁም ምእመናን እውነቱን እንዳይናገሩና ሐሰት ብቻውን ያለ ተቀናቃኝ እንዲናኝና እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲያመቻቸው ነው፡፡ አንደኛው ተናጋሪ “የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚወድ ሰው የለም፣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሰይጣን ናቸው” ብለዋል፡፡

“ክፉ ነገር የሚሰፍነው እውነትን የሚያውቁ ሰዎች ዝም ሲሉ ነው” እንደሚባለው ሐሰተኞችና ሌቦች ተጠራርተው ብዙ መስለው ሲጮኹ የቤተ ክርስቲያን እምነቷ ሊጠበቅ፣ ሀብቷም ለግለሰቦች መበልጸጊያ ሳይሆን ለስብከተ ወንጌልና ለመሳሰሉት ለዓላማዋ ማስፈጸሚያ ብቻ ሊውሉ ይገባል የሚሉ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ ሮቤል ተማርረውና ተሰላችተው ወይም ደግሞ በሐሰተኛ ወሬ ተታልለው ጥለው መውጣትና ምን አገባኝ ማለት ሳይሆን ለእውነት ሊቆሙና አስፈላጊውን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ሊወጡ ግድ ይላቸዋል፡፡

ይህ ሁኔታ በተገቢው ጊዜ ተገቢው ሥር ነቀል መፍትሔ ካልተሰጠው ክፉው እርሾ መልካሙን ዱቄት እያቦካ መሄዱ ስለማይቀር የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስም በቀጣዩ ጉባኤ አንድ ወጥና ዘላቂነት ያለው መፍትሔ ይሰጠዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት” ብሎ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች እንደ ወቀሳቸው ዛሬም በየአጥቢያው የመሸጉ ሙዳየ ምጽዋት ገልባጮች፣ የምእመናን ገንዘብ ዘራፊዎች፣ ስለ ስብከተ ወንጌል አንዳችም ግድ የሌላቸውና ስለ ምእመኑ መኖርም ሆነ መጥፋት ሃሳብ የሌላቸው ባንዳዎች፣ እንዲሁም ተሐድሶዎች “አስቀድሞ መጮኽ” በሚል ስልት ጩኸታቸውን እያሰሙ ለማጭበርበር የሚያደርጉት የአደባባይ የነውር ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ ከሥር ከመሠረቱ የሚፈታበትን ሥርዓትና አሠራር ከነ አፈጻጸሙና ትግበራው የሚያሳይ ውሳኔ ይጠበቅበታል፡፡ አለበለዚያ ለቤተ ክርስቲያኒቷ ህልውና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ችግሮች ከሥር ከሥራቸው እየተፈቱ ባለ መሄዳቸው ተጠራቅመውና ተሰብስበው ቤተ ክርስቲያኒቱን በታሪክ አጋጣሚ ከዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትገኝ አድርገዋታል፡፡ ከእግዚአብሔር በታች የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስም ይህን ፈታኝና ወሳኝ ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በአግባቡ ይወጣዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የእስራኤል ልጅ ዮሴፍ በወንድሞቹ ወንጀልና ጥፋት ተደርጎ የቀረበበት “ሕልመኛ” መሆኑ እና በዚህም “ወደፊት አንድ ቀን በእኛ ላይ ይነግሥብናል፣ ይገዛናል” የሚል ስጋትና ፍራቻ ነበር፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የቀረቡት ክሶችም እንደዚሁ ያሉ ናቸው፡፡ ከከሳሾቹ አንደኛው “የእነርሱ ራእይ ማፈራረስ ነው፡፡ ራእያቸው በጣም ረቂቅ ነው፣ ራእያቸው ረጂም ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከአብነት ትምህርት ቤት መምህራን መካከል ብዙዎቹ የሚረዳቸው በማጣታቸው ምክንያት ወንበራቸውን እያጠፉ ወደ ከተማ በመግባታቸው፣ ደቀ መዛሙርትም በዚህ ዘመን ለምኖ መማር በእጅጉ ፈታኝ እየሆነባቸው በመምጣቱ ጉባኤያቱ ከመሠረታቸው እንዳይጠፉ ለማድረግ ዓቅሙ በቻለ መጠን ከአባላቱና ከምእመናን በሚያገኘው ድጋፍ በዚያው ባሉበት እንዲረዱ ለማድረግ መሞከሩም ወንጀል ተደርጎ ቀርቧል፡፡

አንደኛው ከሳሽ ወንጀል አድርገው ያቀረቡትም “ሰው ውጭ ሀገር ሄዶ በሚሠራበት ዘመን ከጎንደር አዲስ አበባ መግባት ኃጢአት ሆኖ ነው?” የሚል ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ማለት መምህራን ለምን በዚያው በያሉበት ይደገፋሉ? ለምንስ ሁሉም መምህራንና ደቀ መዛሙርት ወደ አዲስ አበባ አይመጡም የሚል ነው? በመጀመሪያ አዲስ አበባ የመጡት መምህራንና ደቀ መዛሙርት ቦታ ለማግኘት የሚሄዱበት መንገድ ምን ያህል ቀላል ወይም ከባድ እንደ ሆነ አገር የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡

ይህን እንተወውና የዛሬዎቹ መምህራን ሁሉም አዲስ አበባ ከገቡ ነገ እነርሱን የሚተኩ መምህራንና ደቀ መዛሙርት የሚመጡት ከየት ነው? የገጠሯ ቤተ ክርስቲያንስ? ከአዲስ አበባ ውጭ ያለችው ቤተ ክርስቲያንስ ቤተ ክርስቲያን አይደለችምን? ይህን የተናገሩት ሰው ምናልባት ከጭፍን ጥላቻ የተነሣ እንጂ እርሳቸው እንዳሉት ቢሆንና ሁሉም መምህራንና ደቀ መዛሙርት አዲስ አበባ ቢገቡ ቤተ ክርስቲያንን ነገ ተተኪ የሚያሳጣት መሆኑን ተረድተውት ተተኪ ትጣ፣ ከመሠረቷ እየጠፋች ትሂድ ብለው አይመሰልንም፤ ቢያንስ እንደዚያ ማሰቡ ይሻላል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ሕገ ደምብ መሠረት ምእመናን የወንጌል ትምህርት እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ወንጌል ያልተሰበከላቸውን ወገኖች ትኩረት አድርጎ የሚሠራ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አቋቁሞ ብዙ ምእመናን ወንጌል እንዲሰበክላቸው አድርጓል፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የእግዚአብሔርን ልጅነት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን ይህም ሌላ የመክሰሻ ነጥብ ሆኖ ቀርቦበታል፡፡

ማኅበሩ የምእመናን ቁጥርን በተመለከተ “እየቀነሰ ነውና እባካችሁ አንድ ነገር ቢደረግ መልካም ነው” እያለ የሚመለከታቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች ለማሳሰብ የዓቅሙን ያህል ሲሞክር ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንዳንዶቹ ይሰጠው የነበረው መልስ “ይህን ቁጥር ከየት አገኛችሁት? ሐሰት ነው” የሚል ነበር፡፡

ሆኖም አሁን ደግሞ “የምእመናን ቁጥር ሲቀንስ የት ነበራችሁ? ለምን አላስተማራችሁም?” የሚል ክስ ዓይነት ወቀሳ ማኅበሩ በሌለበትም ቢሆን ቀርቧል፡፡ የምእመናን መቀነስ ሊያሳስበን የሚገባ መሆኑ መነሣቱ የዘገየ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ግን መልካም ነው፡፡ ማኅበሩም መሥራት የሚገባውን ያህል አልሠራም የሚል አባታዊ ወቀሳ ከሆነ እንቀበላለን፡፡ ሆኖም ጉዳዩ የምር በቅንነት ታስቦበት ከሆነና ከሌሎች ነገሮች ጋር ታዝሎ ካልሆነ ግን መፍትሔው በተቻለው መጠን ይህን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ሕግና ደምብ መሠረት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ እየሠራ ያለውን ማኅበር መደገፍ ነው? ወይስ መክሰስና ማደናቀፍ?

ማኅበሩ በተለያዩ ምክንያቶች ስብከተ ወንጌል የበለጠ ደከም ያለባቸውን ሃያ አህጉረ ስብከቶች መርጦ ከአህጉረ ስብከቶቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሥራ አስኪያጆች ጋር መክሮና ዘክሮ ስብከተ ወንጌልን ለማጠናከር አብሮ መሥራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጥረቶችም በእግዚአብሔር ቸርነት አበረታች የሆኑ ውጤቶች እየታዩ ነው፡፡

በእነዚህ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሁሉም አህጉረ ስብከቶች ከየአህጉረ ስብከቶቹ ጋር አብሮ በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑ ዓይኑ ለማየት ጆሮውም ለመስማት ክፍት ለሆነ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህንም በየዓመቱ በሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ የየአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ላይ ሲነገሩና ሲደመጡ የኖሩ ናቸው፡፡ “ኑና እዩ” እንደ ተባለው ለመንቀፍም ሆነ ለማመስገን በቅንነት ሆኖ ልብን ከፍቶ ጊዜ ሰጥቶ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ማየት ያስፈልጋል፤ ሚዛናዊ መሆን የሚቻለው ያን ጊዜ ነውና፡፡

አገልግሎቱን ለመፈጸም በየጊዜው እየተወደደ የሚሄደውን የቤት ኪራይ መክፈል በእጅጉ እያስቸገረው በመሄዱ አባላቱ በተለያዩ ጊዜያት የወር ደመወዛቸውን አዋጥተው ቀሪውን ደግሞ ከባንክ ተበድሮ እየሠራው ያለው ሕንፃም አንድ ሌላ ወንጀል ሆኖ ቀርቦበታል፡፡ እዚህ ላይ ማኅበሩን በሀብት ማካበት የከሰሱት አንደኛው “እኛ ያቺን ጭቃ ቤት ሠራን ተብለን መከራችንን እያየን እኮ ነው” ብለዋል፡፡

ይህ ምን ማለት ነው? እኛ ያሻነን እናድርግ፣ ዝም በሉን፣ አትወቁብን እኮ ነው፡፡ ማኅበሩ በዋናነት የተፈራውም ያለፈውን ጉዳችንን ያወጣብናል፣ ለወደፊቱም ያሻንን እንዳንዘርፍ ያሰናክለናል ተብሎ መሆኑን ራሳቸው ገልጸውታል፡፡ “እነርሱ ካሉ እኛ አንኖርም” የሚሉት ክሶች ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ ጅራፍ ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው አስቀድመው ይጮኻሉ፡፡

ይህን በግልጽ ሲናገሩም “በእኛ በደል ላይ የሚናገር፣ እኛን የሚያሳጣ ምእመን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለምን ይልኩብናል?” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም ማለት ዘረፋችን፣ ወንጀላችን ሳይታወቅብን እንኑር፣ ቢታወቅም ደግሞ ታይቶ እንዳልታየ ዝም ተብሎ ይታለፍ፣ የመዝረፍ መብታችን ይከበርልን ነው፡፡ ይህን የሚቃወም ደግሞ “ወይጥፋእ እምድር ዝክሩ – መታሰቢያው ከምድር ይጥፋ” ነው፡፡ መዝ. 108፡15

እንደዚሁም የማኅበሩን አባላት “የክብር ዶክትሬት ናቸው፣ ክህነትም የላቸውም፣ ወዘተ” እያሉ የተሳደቡት ተናጋሪ በመቀጠል “የተማሩ ከሆኑ ታዲያ ለምን አውሮፕላን አይሠሩም ነበር?” ሲሉ ለመሳለቅ ሞክረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፕላን ማምረቻ ፋብሪካ መክፈት ይጠበቅበት ኖሯል ይሆን? ምናልባት እነርሱ ማኅበሩ ላይ በጉልበት ለመጫን በማሰብ ባዘጋጁት ሕገ ደምብ ውስጥ በቸርነታቸው አካተውልን ይሆናል! የማኅበሩ አባላት የተማሩ ስለ መሆን አለመሆናቸው እኛ ምንም ማለት አንፈልግም፡፡

ምክንያቱም የማኅበሩ ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንጂ ስለ አባላቱ መማርም ሆነ አለመማር ጥብቅና መቆም አይደለምና፡፡ በርግጥ መማር ማለት የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መዝረፍ ከሆነ፣ ተሐድሶ በመሆን ወይም የእነርሱ ተላላኪ በመሆን ኦርቶዶክሳዊነትን መፈተን ከሆነ፣ ሐሰትን በአደባባይ ያለ ሐፍረት መናገር ከሆነ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ማጣት ከሆነ፣ አዎ፣ አልተማርንም፡፡ እንዲህ ያለው ትምህርትም ሁል ጊዜ ከእኛ እንዲርቅልንና ከዚህ ዓይነቱ “እውቀት” ያልተማርን እንድንሆን እግዚአብሔር ያድርግልን፡፡

የዮሴፍን ሕልም የራሱ ወንድሞች እንደ ተቃወሙትና እንደ ጠሉት ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መመሪያና ደምብ መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓቅሙ ለመደገፍ እየሞከረ ያለው የማኅበረ ቅዱሳን እይታና አገልግሎት የማይመቻቸው ዘራፊዎችና ተሐድሶዎች ማኅበሩን ቢቃወሙ የሚገርም ነገር የለውም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆነ ሰው ቤተ ክርስቲያን እንድትጠነክር የሚመኝንና ባለው ዓቅም ለዚህ የሚሠራን ግለሰብም ይሁን ማኅበር መጥላቱ ተፈጥሯዊ ነውና፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ ጠላት ባልሆነ ነበር፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ስብሰባ ዓላማዎች በዋናነት ሲጠቀለሉ አንደኛው ማኅበሩን በማሳቀቅና በማሸማቀቅ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮና ቀኖና መጠበቅ የጀመራቸውን የስብከተ ወንጌል፣ የገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍና የመሳሰሉትን ተግባራት ማደናቀፍ ነው፡፡ የዚህ የማሸማቀቅ ስልት ደግሞ ማኅበሩ ፈርቶ ዝም እንዲልና በዚህም እነርሱ ያሻቸውን እንዲያደርጉ ለማመቻቸት ነው፡፡ አንደኛው ከሳሽ “ማኅበሩ የራሱን ጳጳሳት ያስሾማል፣ በቀጣዩ የሲኖዶስ ስብሰባ የራሱን ሰዎች ለማስሾም አዘጋጅቷል” ሲሉ መደመጣቸውም የዚህ ስልት አካል ነው፡፡

ማኅበሩ “እንዲህ እባላለሁ” እያለ ሲሳቀቅ እነርሱ ለክፉ ዓላማቸው የሚመቿቸውን ሰዎች ቦታ ቦታ ለማስያዝና ከዚያም አልፎ ወደ ጵጵስና ደረጃ ለማውጣት ያሰቡ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ሁኔታቸውና ንግግራቸውም ተሐድሷዊ ኑፋቄን ለማራመድ ታስቦ ወደ ጵጵስና “ከፍ ለማድረግ” የተዘጋጁ ሰዎችና የተደገሰ ድግስ ሊኖር እንደሚችል አመላካች እንዳይሆን አሳሳቢ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ጫና በማሳደር ባለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ቀርበው በሁሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ተቀባይነት ያላገኙትን ማኅበሩን በስም ብቻ እንዲኖር፣ በተግባር ግን ምንም ሥራ እንዳይሠራ እግር ከወርች ቀፍድደው የሚያሥሩትን ሕጎች ለማኅበሩ “መመሪያ” አድርጎ በመስጠት ማኅበሩን በስም ብቻ የሚኖር በተግባር ግን ምውት ለማድረግ ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ይህም ሁሉ ካላዋጣና የታሰበውን ውጤት ካላስገኘ ማኅበሩን ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር ስስ በሆኑ “አሸባሪ፣ አክራሪ፣ ሙሰኛ” የሚሉ ታርጋዎች በመለጠፍ የዮሴፍ ወንድሞች ዮሴፍን ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች አሳልፈው እንደ ሰጡትና እነዚያ ደግሞ ለፈርዖን ባለ ሥልጣን ለጲጥፋራ እንደ ሸጡት እነርሱም ማኅበሩን አሳልፎ መስጠትና እነርሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ግል ቤታቸውና ድርጅታቸው እንዳሻቸው እንዲፈነጩባት መሆን ነው፡፡

ለእነዚህ ወገኖቻችን፣ ዮሴፍን ወንድሞቹ አጠፋነው ቢመስላቸውም በእነርሱ ክፋት አለመጥፋቱንና ከእግዚአብሔር የሆነ ነገር የማይቀር መሆኑን እንዲያስተውሉ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ እንመኛለን፡፡ ገማልያል የተባለው በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ቅዱሳን ሐዋርያትን ወንጌልን እንዳይሰብኩ ሲከለክሏቸውና ሲያስቸግሯቸው የነበሩትን አይሁድን “አሁንም እላችኋለሁ፡- ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ፣ ተዋቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፏቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ” ብሎ የተናገራቸውን ቃል ማስታወሱ ቢጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይመስለንም፡፡ የሐዋ. 5፡34-39

ይህ ማለት ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ሰው ወይም ማኅበር ፈተና አይገጥመውም ማለት አይደለም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎችም የእነርሱን አሠረ ፍኖት የተከተሉ ሁሉ ተፈትነዋል፡፡ ሆኖም ክቡር ዳዊት “በእግዚአብሔር ተወከልኩ ኢይፈርህ ምንተ ይሬስየኒ ሰብእ – በእግዚአብሔር ታመንሁ፣ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” እንዳለ፤ እንዲሁም “እግዚአብሔር ይረድአኒ ኢይፈርህ እጓለ እመ ሕያው ምንተ ይሬስየኒ – እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፣ አልፈራም፣ ሰው ምን ያደርገኛል? ኩሎሙ አሕዛብ ዐገቱኒ ወበስመ እግዚአብሔር ሞዕክዎሙ – አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፣ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው” እንዳለ የእውነት አምላክ፣ ሁሉን ቻይና ኃያል በሆነው በሕያው እግዚአብሔር ስለምናምን የማንንም የሐሰት ክስና ጩኸት ስለ ሰማን አንጨነቅም፣ ከዓላማችንም ወደ ኋላ አንልም፡፡ መዝ. 55፡11፤ መዝ. 117፡6፣ 10

እንዲሁም “እግዚአብሔር ይሴርዎን ለከናፍረ ጉሕሉት – የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል” ተብሏልና፡፡ መዝ. 11፡3 ከዚህም ጋር “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፣ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል” ተብሏልና፡፡ 2 ቆሮ. 5፡10 ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬያችኋለሁ፤ ከምኵራባቸው ያወጧችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” ሲል አስተምሮናልና፡፡ ዮሐ. 16፡1-2

የሰሞኑ የዮሴፍ ወንድሞች ጩኸትም ይኸው ነው፤ “ያ ሕልመኛ መጣ፤ ኑ፣ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፣ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፣ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን” ይላሉ፡፡ የሚያደርጉትን አያውቁምና እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው እንመኛለን፡፡ ኃይለ አጋንንትንና አጽራረ ሃይማኖትን ያስታግሥልን፣ ባለማወቅ የሚሳሳቱትን ደግሞ ልቡናቸውን ይመልስልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ማህበረ ቅዱሳንን በመደገፍ ታላቅ እና ደማቅ የአጋርነት ንቅናቄ ሊደረግ ነው!

By ቀሲስ ሳህለማርያም

ንቅናቄው በጩሐት ሳይሆን ብልሃት እና ብስለት የተሞላበት መሆኑ ታውቋል።

image

የኢሕአዴግ መንግስት እና በቤተክህነት ውስጥ የተሰገሰጉ ካድሬዎች የተዋህዶ እምነትን የፖለቲካ አሽከር ለማድረግ የጀመሩትን ሴራ እና በማህበረ ቅዱሳን ላይ የተሰነዘረውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በመቃወም በድምጻችን ይሰማ ዘኦርቶዶክስ እና በእኔም ለእምነቴ በብስለት እና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ በጋራ የተዘጋጀ ታላቅ እና ደማቅ የአጋርነት ንቅናቄ ማህበረ ቅዱሳንን በመደገፍ ሊካሄድ እንደሆነ እና ምእመናን ለዚሁ ንቅናቄ እንዲዘጋጁ ጥሪው ተላልፏል።
===============================
የመጀመሪያው ዙር ዝርዝር መግለጫ እንደሚከተለው ነው።

ለማኅበረ ቅዱሳን እመሰክራለው :: ለቀጣዩ የአደባባይ ምስክርነት በተጠንቀቅ እንዘጋጅ።
ምእመናን ምን ማድረግ እንዳለብን በቀጣይ ቀናት የሚገለፅ ይሆናል፡፡

††† #ድምጻችንይሰማዘኦርቶዶክስ – #እኔም_ለእምነቴ ! ††† የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነ እና ስለማኅበረቅዱሳን በጎ ሥራ ለመመስከር እንዲቻል ይህ መልዕክት ለሁልም ማዳረስ ሐይማኖታዊ ግዴታችን ነው ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
እኔም ለእምነቴ የማህበራዊ ድረ ገፅ ተጠቃሚ ምንጮቻችን መሰረት፤ በማኅበረቅዱሳን ላይ አሁን እየተፈፀመ ያለው የስም ማጥፋት እና ውግዘት፤ ገና ከጥንስሱ ከማንም በፊት መረጃው ለሁሉም እንዲደር ጥረት ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ ያስተላለፍ ነው መልዕክት ከቁምነገር ሳይቆጠር አብዛኛው ሰው ጉዳዩን በቸልታ አልፏታል፡፡ ሆኖም ግን በእኔም ለእምነቴ መረጃው ከተላለፈ ከ1 ቀን በኋላ ሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳይ ዙሪያ ሰፊ ዘገባ ይዞ ወጥቷአል፤ ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን ስለማኅበረ ቅዱሳን መልካም የሆነ ነገር እየተሳማ አይደለም፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ አሁን ላይ ከጫፍ የደረሰ አሳሳቢ የቤተክርስቲያናችን ጭንቀት ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ/ክ እጅግ በጣም ለቁጥር የሚታክት መንፈሳዊ አገልግሎት የሰጠ እና እየሰጠ የሚገኝ መኅበር ነው፡፡

ይሁንእንጂ ጥቅምት፯ቀን፳፻፯ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተክህነት የስብሰባ አዳራሽ በተጀመረው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ በረከት እንዲሰጡ የተጋበዙት ፓትርያርክ አባማትያስ፣ ማኅበረቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝገዥ›› ነው ፣ ‹‹እኔ ብቻዬን የምሠራው ነገር የለም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ፤ አባ ማትያስ አላበደም፤ መልእክቴን እያስተላለፍኹ ነው ያለኹት፤መልእክቴን ተቀበሉ ብዬ እማፀናችኋለኹ፡፡››አስከትለውም ‹‹ቤተክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ፤ ካህናቱ ከመከራ ይውጡ›› በማለት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የመጨረሻ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ትዕዛዘቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመሆኑም የፊታችን እሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓም በቅድስትሥላሴ ካቴድራል ቤተ/ክ “ዝክረ አቦ ሊቀነጳጳሳት” መንፈሳዊ መራሃ-ግብር ይካሄዳል፡፡ በዕለቱም የአባጳውሎስ የሐውልት ምረቃ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን የዚህ መረሃ-ግብር ዋንኛ ዓላማ ቀደምት ቅዱስ ጳጳሳት እና ብፁዓንሊቃነጳጳሳትን በሥጋሞት የተለዩትን በማስብ የፀሎት እና የፍትሐት ስነ-ስርዓት ይደረጋል፡፡

ይህም የሚሆነው የቅ/ሲኖዶሱ ዓመታዊ ስብሰባ ከመካሄዱ የመጀመሪያው እሁድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መረሃ-ግብር ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄድ የሚገኝ ነው፡፡
ስለዚህም የፊታችን እሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ/ክ ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ፤ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ በአገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ በሙሉ ብፁዓን ሊቃነጳጳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ገዳማትና አድብራት አስተዳደሪዎች እና ፀሐፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የውጪሀገር ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት በሚገኙበት ታላቅ መንፈሣዊ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

በዕለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነ ሁሉ በመረሃ-ግብሩ የመሣተፍ ሓይማኖታዊ ምግባር ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ሐይማኖታዊ መረሃ-ግብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በሙሉ መገኘት አለብን፡፡ በዕለቱም ስለማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት 17 ዓመታት ማኅበሩ በቤተክርስቲያናችን የሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት እንጂ ‹‹የቤተክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› አለመሆኑ የምንመሰክርበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

በዕለቱም ምእመናን ምን ማድረግ እንዳለብን በቀጣይ ቀናት የሚገለፅ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነ እና ስለማኅበረቅዱሳን በጎ ሥራ ለመመስከር እንዲቻል ይህ መልዕክት ለሁልም ማዳረስ ሐይማኖታዊ ግዴታችን ነው ፡፡

ወስብህትለእግዚአብሔር !!!

ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ወዳጆች አፈራ? ጠላቶችስ ለምን ተነሡበት?

Eotcmk.org

“ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ…በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል ትን.ዕንባ.3፡17-19”

image

በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመደገፍና ለማጠናከር የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ ፈተናዎችን እያሳለፈ 22 ዓመታት ተጉዟል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዓመታት ጉዞው ባከናወናቸው መልካም ተግባራት ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ ወዳጆችን እንዳፈራ ሁሉ ጥቂት በተቃራኒው የቆሙ ስሙን በየጊዜው በክፉ የሚያነሱ ቡድኖችም ተነሥተውበታል፡፡

ወዳጆቹ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች ናቸውና በአገልግሎቱ ተማርከው በሚሠራቸው መልካም ሥራዎች ተስበው ቤተ ክርስቲያን ያለባትን የአገልግሎት ክፍተት ለመሙላት በጋራ ከማኅበሩ ጋር በመሥራት ሲተባበሩ፤ በአንጻሩ ጠላቶቹ ደግሞ የተለያዩ አጋጣሚዎችን እያስታከኩ ማኅበሩን ለመወንጀል እየተጣጣሩ ይገኛሉ፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ወዳጆች አፈራ? ጠላቶችስ ለምን ተነሡበት?

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ፈቅዶ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ወጣቶችን በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታቸው ጎን ለጎን በየአካባቢው ወደሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሔደው መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ፤ በተጨማሪም ወጣቱ ሀገሩንና ሕዝቦቿን አክባሪ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን በማስቻሉ ብዙ ወዳጆችን አግኝቷል፡፡

 

ከዚህም ሌላ የመናፍቃኑንና ቤተ ክርስቲያኒቱን እናድሳለን ብለው የተነሡትን የመናፍቃኑ ተላላኪ ቡድኖችን ሴራና የአክራሪ እስልምናውን እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፎ በማጋለጡ፣ ከክፉ ትምህርታቸው መመለስ ያልፈለጉ የተሐድሶ ቡድን አባላት ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ስለተወሰነባቸው እና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች እየተከታተለ ለዕድገቷና ለብልጽግናዋ በመሥራቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆችን አፍርቷል፡፡

 

ከዚህ በተቃራኒው የተሰለፉት ወገኖች ደግሞ ወጣቱን እንደጠፍ ከብት ወደ ማያውቀው የመናፍቃን አዳራሽ የመንዳት ልምዳቸው በመቋረጡና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመግባት የሚያደርጉት ሥርዓቷን የማፋለስ እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም አገልጋዮቿንና ምእመናኖቿን የማስኮብለሉ አካሔድ ማኅበሩ በክትትል በተለያዩ መረጃዎች ስለገለጠባቸው ማኅበረ ቅዱሳንን በጠላትነት በማየት ማኅበሩ እንዲፈርስ የማይቧጥጡት ዳገት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

 

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብለው የነበሩ ቢሆንም አሁን ባገኙት አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጀራዋን እየበሉ የሚኖሩ ወዳጆቻቸውን በማጠናከርና በማስፋፋት በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ከወዳጆቻቸው ተመድቦላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማዛባትና በጎቿን ለመበታተን ሌት ከቀን እየሠሩ ነው፡፡

 

ይኼ ዕቅዳቸው የሚሳካው እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዓት መጠበቅ የሚቆረቆሩ ማኅበራትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አጀንዳ በማድረግና እንዲበተኑ ክፉ ሥራ በመሥራት ነው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ይሔንን ከንቱ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግም በቤተ ክርቲያኒቱ የተለያየ ሓላፊነት ላይ የሚገኙትን የዓላማቸው አስፈጻሚዎች ሁሉ እየተጠቀሙ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡

 

ከዚህም ሌላ ድብቅ ዓላማቸው እንዲሳካ ተላላኪዎቻቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚሆን ነገር ግን ስውር ዓላማ ያለው ማኅበር እንዲመሠርቱና ከዚህ በፊት ከንቱ ተግባራቸው ታውቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታግደው የነበሩ ማኅበራት ሁሉ ከሞቱበት እንዲቀሰቀሱ እየሠሩም እያደረጉም ይገኛሉ፡፡

 

በቤተ ክርስቲያን ስም ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያቋቋሟቸውና የሚያቋቁሟቸው፣ ማኅበራትንም ሕጋዊ ዕውቅና ለማሰጠት እንዲያመቻቸው ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከኔ ሌላ ሌሎች አያስፈልጉም የሚል አቋም ያለው ማኅበር እንደሆነ ያስወራሉ፡፡

 

በእርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ደንብ ተከትለው በሚቋቋሙት ማኅበራት ላይ የማኅበሩ ጠላቶች ከሚያወሩትና ከሚያስወሩት አሉባልታ የተለየ አቋም አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን የሁለት ሺሕ ዓመታት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ትሁን እንጂ መንበሯ ከሊቀ ጵጵስና ደረጃ ወደ ፕትርክና ለማሳደግ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ መራራ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በዚህ ማለፏ ደግሞ ሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበት ዘመናዊ የአደረጃጀት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልቻለችም፡፡ ልጆቿንም ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ ለመምራት ሳትችል ስለቆየች እነዚህን ክፍተቶች የሚሞሉ አንድ አይደለም በርካታ ማኅበራት እንደሚያስፈልጓት ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ነገር ግን እኩያኑ እንደሚሉት ሳይሆን እነዚህ ማኅበራት ሲቋቋሙ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዕድገትና የአገልግሎት ሥምረት የሚንቀሳቀሱ ተልእኮአቸውና ዓላማቸው ተለይቶ የሚታወቅ፣ መንፈሳዊ ተግባርን ብቻ የሚፈጽሙ፣ የሚናበቡና በስልት ለአንድ ውጤት የሚተጉ ሊሆኑ ይገባቸዋል የሚል ጽኑ አቋም አለው፡፡

 

ይሔንን አቋሙን ደግሞ በርካቶች የሚደግፉት እንደሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የመናፍቃኑ ተላላኪዎች በቤተ ክርስቲያን ስም ያቋቋሟቸው ማኅበራት ከዚህ በፊት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥለውት የሔዱት ጠባሳ የሚታወቅ ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራት ላይ ግልጽ አቋም አለው፡፡ ከዚህም ሌላ እነዚህ የውስጥ ዐርበኞች ይኽ ስውር ዓላማቸው ያልታወቀባቸው ይመስል ማኅበሩን ለመወንጀል የማይለጥፉለት ታፔላ፣ የማይለፍፉት ወሬ የለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላቶች ስለማኅበሩ የሚያወሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ እና ሁሉም የሚገነዘበው ግልጽ እውነታ መሆኑን ባለማወቃቸው እናዝናለን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን ምንም ስውር ዓላማ የለውም፤ ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዳና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብና መመሪያን ሳያዛንፍ እየሠራ ያለ፤ በተሰጠውም መተዳደሪያ ደንብና ሓላፊነት መሠረት ከአባላቱ የሰበሰበውን የገንዘብ መዋጮ ገቢና ወጪ እያሰላ በውስጥ ኦዲተሮችም እያስመረመረ በመሥራት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ማኅበር እንጂ በወሬ የሚኖር አይደለም፡፡ ይሔንን አሠራሩንም ቀርቦ ማየት ይቻላል፡፡ አባላቱም በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው በጉልበታቸውና በመላ ሕይወታቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ እንጂ እንደ መናፍቃኑ ተላላኪዎች ለሆዳቸው ያደሩ፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነባቸው እዚህም እዚያም ደሞዝ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡

 

ማንኛውም አካል እንዲያውቅልን የምንፈልገው ሐቅ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰጠው ሓላፊነትና አባላቱም ለገቡለት ቃል ኪዳን ሃይማኖታቸው የሚፈቅደውን መስዋዕትነት ለቤተ ክርስቲያን ልዕልናና ክብር ለመክፈል የተዘጋጁ እንጂ በተዛባ አመለካከት ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉ አለመሆናቸውን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱ የሚታይ አሠራሩም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም የመናፍቃኑ ተላላኪዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላ ከአገልግሎታችን አንዲት ጋት ወደ ኋላ እንደማይመልሰን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡ ርእይና ተልእኮአችንን ለማሳካት ዛሬም ነገም እንሠራለን፤ ትናንትን ያሻገረን እግዚአብሔር ዛሬንም ያሳልፈናልና፡፡

ይህ ጽሑፍ ግንቦት 16 ቀን 2003 ዓ.ም ወጥቶ የነበረና ታርሞ በድጋሚ የቀረበ ነው፡፡

 

የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ያዕ1፡2

ማኅበረ ቅዱሳን

image

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተዋጀችውና የተመሠረተችው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ ነው፡፡ ሐዋ.2ዐ፥28፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልጽም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ብሏል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ሲዋጅ ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስን ድል ነስቶ፣ ምርኮውን መልሶ፣ ሞትን ደመስሶ በመሆኑ ዲያቢሎስ የድል ነሺውን ቤተ ክርስቲያንና ወደ ነጻነት የተመለሱትን ክርስቲያኖች ዘወትር ይፈትናቸዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው እግዚአብሔር ኃላፊያቱንና መጻእያቱን በገለጸለት ራዕይ ስለ ዲያቢሎስ ፈተና ሲጠቁም “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ ….ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና። ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።” ዮሐ. ራዕ. 12፥9-17፡፡

ታሪክና መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ጌታን የሰቀሉ አይሁድ ደቀመዛሙርቱን በእርሱ ስም እንዳያስተምሩ ለማድረግ በማስፈራራት ብዙ ጥረዋል፤ አስረዋቸዋል፣ ገርፈዋቸዋል፣ አሳደዋቸዋል፣ ገድለዋቸዋል፡፡ ሐዋ.ሥ 4፥17-21 ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአለት ላይ የተመሠረተችና በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ስለሆነ ሥራዋ አልተቋረጠም፤ ተከታዮቿም አልጠፉም ዕለት ዕለት ይበዛሉ እንጂ፡፡ ማቴ. 16፥18

ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት፣ በዘመነ ሰማእታትና በዘመነ ሊቃውንት እንደጊዜው የተለያየ መከራና ፈተና አሳልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ጥንት በአይሁድ፣ በሮማዊያን ነገሥታት፣ በአህዛብ እያደረ፤ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው በመጽናታቸውና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገላቸው ሰውነታቸው በሰም ተነክሮ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ በቁርበት ተጠቅልለው ለአንበሳ እንዲሰጡ፣ በድንጋይ ተወግረው እንዲሞቱ፣ በስለት እንዲቀረደዱ፣ በሰይፍ እንዲቀሉ ያስደርግ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችም በእምነታቸው እየጸኑ ከሞት የተረፉት፤ በዋሻ በግበበ ምድር እየሆኑ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ጌታ “የሲዖል ደጆች አያናውጧትም” ያላት ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ዳርቻ እየሰፋች የመሰረታትን ጌታ እያመሰገነች ትኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ለማሳካትና የዲያቢሎስን ሽንገላ ለመቋቋም በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች ልጆቿን ታሰማራለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ሰጥታ ልጆቿን ለአገልግሎት ካሰማራችባቸው መንገዶች አንዱ የማኅበራት አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ የማኅበራት አገልግሎት የዲያቢሎስን ፈተናና ሽንገላ ተቋቁመው በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን እያበረከቱ ከሚገኙ ማኅበራት መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከ22 ዓመታት በፊት ቅርጽ ይዞ የተዋቀረና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎቱን የሚፈጽምበት ደንብና ሥርዓት የተበጀለት ማኅበር ነው፡፡ አባላቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የሆኑና በየአጥቢያቸው የልጅነት ግዴታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ሲሆኑ በቅናተ ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው ለቤተ ክርስቲያን እድገት የሚያግዙ የትሩፋት ሥራዎችን የሚሠሩ ናቸው፡፡

ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተለይቶ በተሰጠው ተግባር መሰረት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችን በየአጥቢያቸው አሰባስቦ፤ ከየሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ጋር በመተባበር ትምህርተ ሃይማኖትን የሚያስተምር፣ አባላቱንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ስብከተ ወንጌል በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም እንዲስፋፋ የሚያደርግ፣ አድባራትና ገዳማት በልማት ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደረግ፣ የቤ ተክርስቲያናችን ሀብት የሆነው የአብነት ትምህርት እንዲጠናከርና ሊቃውንቱም ወንበራቸውን እንዳያጥፉ በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ይህ መንፈሳዊ ተግባር በቤተ ክርስቲያን በመተግበሩ፤ ቤተ ክርቲያንን የማይወዱና ውድቀቷን እንጂ ጥንካሬዋን የማይሹ አካላት የማኅበሩን አገልግሎት አልወደዱትም፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ማኅበረ ቅዱሳንን ጠልፎ መጣል እንደ ዋነኛ ስልት አድርገው ቆርጠው መሥራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነዚህ አካላት ለዓላማቸው የሚጠቅም ሆኖ እስካገኙት ድረስ ማንኛውንም ነገር ይጠቀማሉ፡፡ በተለያየ ደረጃ ያሉ ሰዎችን በማሳሳት፣አሉባልታ በመንዛት፣የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጭምር በማሳሳት የሚፈልጉትን ተግባር ለመፈጸምና ለማስፈጸም ይተጋሉ፡፡ ማሩን በማምረር ወተቱን በማጥቆር- ደጋግመው እየወተወቱ ብዙ የዋሐንን የነርሱን የማደናቀፍ ተግባር ተባባሪ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡

በጎ ነገር ሲሠራ በጠላት ዲያብሎስ በኩል እንቅፋት እንደሚቀመጥ ሁልጊዜ የታወቀ ነው፡፡ ፈተናውን ማለፍ መሰናክሉን መቋቋም ግን የአንድ ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም እንደነዚህ ዓይነት ፈተናዎች ከቀድሞ ጀምሮ ሲያጋጥሙት ቢቆይም በአገልግሎቱ ምክንያት የመጡ መሆናቸውን በመገንዘብ በአባቶች ጸሎት፣ በእግዚአብሔር ኃይል አሸንፎ ላለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ ወደፊትም በእግዚአብሔር ፈቃድ ይቀጥላል፡፡

ከላይ በጠቀስናቸው አካላት አማካኝነት አንዳንድ ወገኖቻችን ስለማኅበሩ የተሳሳተ መረጃ ሲደርሳቸው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ መስሏቸው አገልግሎቱን የሚያደነቅፉና ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ የሚፈርጁትን አካላት ወግነው ሲቆሙ ይታያሉ፡፡ እነዚህ አካላት ትክክለኛውን መረጃ ቢያገኙ፣ ቢያውቁና ቢገነዘቡ ከማኅበሩ ጋር የዓላማ ልዩነት ስለሌላቸው፤ አብሮ በፍቅር ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ምንም የሚቸግራቸው ነገር የለም ብለን እናምናለን፡፡ ወደፊትም ከማኅበሩ ጋር አብረው ሊሠሩ የሚችሉ፣ የሚመክሩና የሚያስተካክሉ እንደሆኑ ማኅበሩ ያምናል፡፡ ካሁን ቀደምም እንዲህ ዓይኖቶቹን አካላት ባገኘ ጊዜ ሁሉ ማኅበሩ በማወያየቱና በማስረዳቱ የማኅበሩን አገልግሎት እየደገፉ የሚገኙ በርካታ ናቸው፡፡

ቤተ ከርስቲያንን በዓላማ የሚጠሉ ግን የማኅበሩን አገልግሎት ቢያውቁና ቢረዱትም የዓላማ ልዩነት ስላላቸው መቼም አገልግሎቱን በቀና አያዩትም፡፡ ዕለት ዕለት ለማደናቀፍ ይጥራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ሆነው ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ጠልፈው ለመጣል የሚታገሉ፣ እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን በአፍኣ ሆነው እጃቸውን ባስረዘሙ አንዳንድ አካላት ማኅበሩ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡

ለምሳሌም ያህል በአንዳንድ ሀገረ ስብከቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት በዋናነት የሚያስተባብረውን የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዳያስተምር ሲከለክሉና ሲያቋርጡ ይታያሉ፡፡ ማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ማእከላት ቢሮዎች የሚዘጉ አንዳንድ አጥቢያዎችም ይስተዋላሉ፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ አካላትም በሕዝብ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ሳይቀር የማኅበሩን ስም እያነሱ ተገቢ ያልሆነና ማኅበሩን በፍጹም የማይገልጹ ቅጽሎችን እየሰጡ ለማስረዳት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡

እነዚህ ለማሳያነት በተጠቀሱት የማኅበሩ ተግዳሮቶች መነሻነት በአንዳንድ ግለሰቦች አማካይነት መዋቅሮችን አላግባብ በመጠቀም የግለሰቦቹን ምኞት ከግብ ለማድረስ የሚሠሩና ጥንቃቄ ያልታከለባቸው እርምጃዎች እንጂ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመንግሥት ውሳኔ ነው ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆኑ ፈተና ስለማይለየው ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች በጸሎት፣ የሚመለከታቸው አካላት በማስረዳትና በመወያየት፣ እንዲሁም በመታገስ አልፎ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ያገለግላል፡፡

ማኅበሩ ፈተና ሲያጋጥመው መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት የሚሄድባቸው መንገዶች ሁልጊዜም የታወቁ ናቸው፡፡ ችግሮች ሲመጡ ጊዜያዊና በእግዚአብሔር ኃይል በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በመረዳት በጥበብና በትዕግስት ከሚመለከከታቸው አካላት ሁሉ ጋር እየተወያየ ይፈታል፡፡ የችግር አፈታቱ ሥርዓት መንፈሳዊነትን የተከተለ በመሆኑ ሥጋዊ አስተሳሰብን ሳይጨምር ሃይማኖታዊ ፈተና ሲመጣ ማሸነፊያው ሃይማኖታዊ ኃይል ነው ብሎ ያምናል፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በጾምና በጸሎት በትዕግስትና በጽናት፤ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ነው፡፡

በማርቆስ ወንጌል ላይ እንደምናገኘው፡- (ማር. 4፡37) “ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።” ይላል፡፡ በታንኳይቱ የተመሰለችው ቤተ ክርስቲያን በፈተና ልትናወጥ ትችላለች፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ በውስጧ ያለውን፣ ነገር ግን እኛ የድርሻችንን እስክንወጣ ድረስ የሚጠብቀውንና ዝም ያለ (የተኛ) የሚመስለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፈተናን ጸጥ የሚያደርግ አምላክ እንደምናመልክ ልንዘነጋ አይገባምና ፡፡

ማኅበሩ በቤተክርስቲያንም ሆነ በማኅበራችን ዙሪያ ስላሉ ነገሮች ማንኛውንም መረጃ የሚያስተላልፈው በራሱ ሚዲያና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሥርዓት ባለው መልኩ በሚመለከታቸው የማኅበሩ ኃላፊዎች በኩል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የሚተላለፍ ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ሀሳቦችን በመያዝ ማኅበሩን በተመለከተ የግል ሀሳብንና ተግባርን ማንጸባረቅ አግባብ አለመሆኑን ሁሉም አካላት ሊያውቀው ያስፈልጋል፡፡

ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማን ግብ ያለው በመሆኑ በጊዜው በሚታዩ ጥቅመኞችና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሁከት ሳንዘናጋ የወንጌል ተልእኳችንን በጥበብና በትዕግስት ከግብ ማድረስ ይገባናል እንላላን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ያዕቆብ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ ያዕ.1፡2 እንዳለ ስለ እምነታችንና ስለቤተ ክርስተያናችን የምናደርገውን አገልግሎት ፈታኙ ዲያብሎስ ሊያደናቅፍ ሠራዊቶቹን ቢያሰማራም እግዚአብሔር አምላካችንን ትዕግስትንና ጽናትን እንዲሰጠን ፈተናውንም እንዲያሳልፍልን በጽናት እንለምነው፡፡- እርሱ በሰው ዘንድ የማይቻለውን እንድንችል ማድረግ ያውቅበታልና፡፡ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔ