Adebabay (ከኤፍሬም እሸቴ)
ኢትዮጵያ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ናት። በመላው አገሪቱ የተቀሰቀሰው እምቢተኝነት በመንግሥት በኩል የገጠመው ጠንካራ እጅ ብዙ ዜጎችን ለሞት፣ ለእስር፣ ለስደት እና ለንብረት ውድመት የዳረገ ሆኗል። በመሆንም ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የመንግሥት የብረት ጡጫ (አይረን ፊስት) ነገሮችን ከማረጋጋት ውጪ የበለጠ ቀውሱን እያሰፋውና እያበረከተው በመሔድ ላይ ይገኛል። በመንግሥት የሚፈጸሙት መንግሥታዊ ሽብሮች ደግሞ እንደ ቀድሞው ዘመን ተደብቀው የሚቀሩ ሳይሆን በተለያዩ ዘዴዎች ለሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚደርሱ ሆነዋል። በአልሞ ተኳሾች የተገደሉ ወጣቶች፣ በፖሊሶች ድብደባ ሲፈፀም የሚያሳዩ አሰቃቂ ቪዲዮዎች፣ ቃለ ምልልሶች እና የተቃጠሉ ንብረቶች ዘመኑ በፈቀዳቸው ቴክኖሎጂዎች በመሰነድ ላይ ይገኛሉ። ሌላው ቀርቶ መንግሥት ራሱ በምስጢር የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የድምጽ ቅጂዎች የአደባባይ ሲሳይ በመሆን ላይ ናቸው። በዚህ ዘመን ተወርቶና ተፈጽሞ ተደብቆ የሚቀር ምንም ምሥጢር ምንም ወንጀል አይኖርም።
የለውጡ ማዕበል አንዴም ለብ፣ አንዴም ሞቅ፣ አንዴም በረድ እያለ የከረመ ሲሆን አሁን ግን በተለይም በኮንሶ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ አያያዙን በማጠናከሩ ወደኋላ ከማይመለስበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። በአገር ውስጥ ብቻ የሚከናወነው ተቃውሞ አድማሱን በማስፋት በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በስፋት በማጠቃለል ላይ ነው። በዚያውም መጠን የመንግሥትም ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ በከፋ መልኩ ቀጥሏል። መንግሥት በሚያደርገው ሰፊ እንቅስቃሴ ተቃውሞው በተለይ የምዕራባውያን ድጋፍ ሳያገኝ ለመቆየት የቻለ ቢሆንም አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ተቃውሞውን ለዓለም ከገለጠ በኋላ ምዕራባውያንም የሚያውቁትን፣ ነገር ግን ጀርባቸውን የሰጡትን ቀውስ በይፋ ወደመቃወም መግባታቸው እየታየ ነው። ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ወቅት እንኳን የአሜሪካ ኮንግረስ ጉዳዩን ወደ ሕግ ደረጃ ለማድረስ ረቂቅ መዘጋጀቱን ጉዳዩን የሚመሩት የኒውጄርሲ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ (Chris Smith) ገልጸዋል።
የቀውሱ መጠን ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ትኩረት ባገኘበት በአሁኑ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ አጋር የሆኑትን ምዕራባየውያንንም ሳይቀር የሚያሳስባቸው «ቀውሱ በምን መልክ ይጠናቀቃል?» የሚለው ጉዳይ ነው። ይህንን የሚገነዘበው ሕወሐት ዜጋውንም ፈረንጆቹንም ለማስደንበር «የሶሪያ»ን ካርድ በመሳብ ላይ ይገኛል። ተቃውሞው ከቀጠለ እንደ ሶሪያ የጦርና የውድመት አውድማ እንሆናለን በማለት ላይ ነው። ሽማግሌዎቹ መሪዎቹ ከጡረታቸው በመሰባሰብ ይህንኑ «የሶሪያ ካርድ»፣ የጀርመኖችን ሆሎኮስት እና የሩዋንዳን ፍጅት በማንሣት ላይ ናቸው። የኮሙኒኬሽን ዋና መሥሪያ ቤቱ በፎቶዎች የታጀበ የሶሪያ ውድመትን እንደ እያሰራጩ ነው። ጥያቄው ግን በአገራችን ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንጂ ጦርነት አይደለም። አገሪቱን ሶሪያ የሚያደርጋት አውዳሚ ጦር መሣሪያ የያዘው ሕወሐት እና ወታደሩ ነው። ስለዚህ ማስፈራሪያቸውን «እንደ ሶሪያ እናደርጋችኋለን» በሚል እንወስደው ካልሆነ ሌላ ምንም አንድምታ የለውም። የፖለቲካ ምሁራን የራሳቸውን ትንታኔ መስጠታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በበኩላችን «ቀውሱ በምን መልክ ይጠናቀቃል?» የሚለውን በተለይም ከኦርቶዶክሰ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ለመመልከት እንሞክራለን።
ሑነት (Scenario ሴናሪዮ) አንድ፡-
ምንም ለውጥ ሳይመጣ «ዘሀሎ»ው (Status Quo) ከቀጠለ
(ማሳሰቢያ – ዘሀሎ የሚለው ስታትስኩዎ/ Status Quo የሚለውን ቃል የሚተረጉም ነው።)
ሑነት አንድ ለረዥም ጊዜ የቀጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በመንግሥት አሸናፊነት ቢደመደም የሚለውን መላምት የተከተለ ነው። ይህ ሑነት ድኅረ 1997 ዓ.ም ምርጫ ያለውን ሑነት ይመስላል። እምቢተኝነቱ በሕዝቡ የበላይነት የማይጠናቀቅ ከሆነ ሕወሐት መራሹ መንግሥት ከ1997 በኋላ እንዳደረገው የዚህ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መሪ ናቸው ብሎ የጠረጠራቸው ላይ በሙሉ የማያዳግም ርምጃ ይወስዳል። ይህም በተለይ የራሱ የኢሕአዴግ ክንፎች በሆኑት በብአዴን እና በኦሕዴድ የበታች አመራሮች፣ አባላትና ካዴሬዎቹ ላይ የከረረ ይሆናል። ከዚያም አልፎ ለእምቢተኝነቱ መፈጠር ምቹ ሁኔታ ናቸው የሚባሉትን ነገሮች በሙሉ ያጸዳል። ወጣት መሆን እንደ ወንጀል የሚታይበትን ክፉ አመለካከት ያበረታዋል። ወጣቶች የችግሩ ቀዳሚ ተጠቂዎች መሆናቸው ይቀጥላል። የአገዛዙ ቀንበር ከመቼም ጊዜ በላይ የጠነከረ ይሆናል። የአገዛዙ አካሎች የበለጠ በራስ መተማመን፣ ትዕቢትና ማን አለብኝነት ያሳያሉ። ማንም አያሸንፈንም የሚለው የቆየ ዘፈን የበለጠ ይጠነክራል።
አሁን ያለው ዘሀሎ በዚሁ እንዲቀጥል ትልቅ ፍላጎት ያለው የቤተ ክህነት አመራር የተቆጣጠረው አስተዳደር ያለ እንደመሆኑ ጉዳዩ በሕወሐት/ኢሕአዴግ የበላይነት መጠናቀቁ ለቤተ ክህነቱ መሪዎች ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን ይታወቃል። ለዚህም በአቅማቸው የለፉበት እና የሠሩበት፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ ሽባ በማድረግ የዚህ መንግሥት አገልጋይ ያደረጉ እንደመሆናቸው ሑነት አንድ የልፋታቸው ውጤት ተድርጎ ሊታሰብላቸው ይቻላል።
ይሁን እንጂ ቤተ ክህነቱ ለመንግሥት ባሳየው ጠንካራ ድጋፍ ምክንያት ብዙው ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ረገድ የሚኖረው ቀቢጸ ተስፋ ወትሮም ከነበረው የባሰ መሆኑ አያጠያይቅም። በካህናት እና በመነኮሳት ላይ እንዲሁም በጳጳሳት ላይ የሚኖረው አሉታዊ አመለካከት የበለጠ ስር ይሰድዳል። በምዕራቡ ዓለም በካቶሊክ ካህናት ላይ አሉታዊ አመለካከቶች በመፈጠራቸው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ችግር እንደገጠማት ሁሉ በአገራችንም ቤተ ክርስቲያናችን የዚያ ዕጣ ሊወድቅባት ይችላል። ስለዚህም ከእምነት የሚያፈገፍጉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ቢችል የሚደንቅ አይሆንም።
በሌላም በኩል የኢሕአዴግ ማሸነፍ እና የበላይነቱን መጨበጥ በተለይም በካህናቱ አካባቢ ያለውን አድርባይነት እና ለፖለቲካው ተገዢ የመሆን «መለካዊ» ኑፋቄ የበለጠ ያሰፋዋል። ቤተ ክርስቲያን ለጣለችባቸው ሃይማኖታዊ ዓላማ ከመቆም ይልቅ በአድርባይነት እና ተመሳስሎ በመኖር አባዜ የፖለቲካውን ከበሮ በመደለቅ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የወንጌል ዓላማ የሚዘነጉት ሰዎች ቁጥር አሁን ካለው የበለጠ አሳፋሪ ሆኖ ይቀጥላል። ሙስናው፣ ዓለማዊነቱ፣ አሰረ ክህነትን ያልጠበቁና ምንጫቸው ያልታወቀ መነኮሳት መብዛት፣ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም አብነት ት/ቤቶችን መዘንጋቱ የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህ መለካዊ ዓላማቸው እንቅፋት ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ተቋማት፣ አገልጋዮች እና አሠራሮች ወደ ማጥፋት ይሄዳሉ።
ሑነት (Scenario) ቁጥር ሁለት
ጥገናዊ ለውጥ
ሁለተኛውና ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አንዱ ሑነት መንግሥት «ጥገናዊ ለውጥ በማድረግ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ያቀዘቅዘዋል» የሚለው መላ ምት ነው። ጥገናዊ ለውጥ መሠረታዊ ለውጥ አይደለም። መንግሥት የያዘውን መሠረታዊ ማንነት ሳይለውጥ አንዳንድ ለውጦችን በማድረግ ከምዕራባውያን አጋሮቹ እና ፖለቲካዊ ብስለት ከጎደላቸው ወገኖች ያጣውን መተማመኛ ማግኘት ነው። የኦሮሞን ጥያቄ ለመመለስ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ሰርዣለኹ እንዳለውና ጥቂት የሙስሊም መሪዎችን እንደፈታው ያለ የታይታ ምልክቶችን ማድረግ ነው። ነገር ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ርምጃዎች ከማንም አንጀት ጠብ የማይሉ በመሆናቸው ጥገናዊ ለውጥ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ አይደሉም።
ስለዚህ ፈረንጆቹንም፣ አንዳንድ የሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ተሳታፊዎችን ቀልብ ሊስብ የሚችለው ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ቢያንስ ከ1997 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ሁኔታ መመለስ ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ሕወሐት በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ድርሻ ሳያስነካ፣ በኢኮኖሚው፣ በውትድርናውና በደኅንነቱ እንዲሁም በሌሎች መንግሥታዊ እርከኖች ላይ ያለውን የአንበሳ ድርሻ ሳያስወስድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የጣለውን የብረት መጋረጃ በጥቂቱ ገለጥ ማድረግ፣ የግል ቴሌቪዥንና ሬዲዮኖችን እንዲሁም ጋዜጣና መጽሔቶችን መፍቀድ፣ ኢሕአዴግ ያልሆኑ ሰዎችን በሥልጣን ላይ ማስቀመጥ የመሳሰሉትን ሊያደርግ ይችላል። በሃይማኖቱ በኩልም አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ፓትርያርክ ማትያስና አጋዦቻቸው የሆኑ የዘሀሎው ተጠቃሚዎችን ሳያነሣ ውጪ አገር በስደት የሚገኙት አባቶች እንዲገቡ፣ በቤተ ክህነቱ ያለው የአንድ ብሔረሰብ የበላይነት በመጠኑ ጋብ እንዲል የጥገና ለውጥ ሊያደርግባቸው ይችላል።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሽምግልና ስም «አንተም ተው አንተም» በሚል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መንግሥት የተቀሰቀሰበትን እምቢተኝነት ሊያረግቡ የሚችሉ የተለያዩ አካላትን ሚና ሊቀበል ይችላል። ተሸምግሎ ለሌሎች ሐሳብ እንደተገዛ በማስመሰል የጥገናውን ለውጥ ሊያካሒድ ይችላል። የአሸማጋይነቱን ሚና የሚጫወቱት ሰዎች በቅን ኢትዮጵያዊ መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ያሉበትን ያህል ልባዊ ድጋፍ ለሚሰጡት የሕወሐት/ኢሕአዴግ ቡድን በምንም በምን ብለው የሕዝቡን ቁጣ በማብረድ ነገ ነጣጥሎ ለሚመታቸው አካል የሚያመቻቹም አሉበት።
በርግጥ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች የታየ እንደመሆኑ ሽምግልና እና ሕወሐት አብረው ይሄዳሉ ተብሎ አይጠበቅም። በሽምግልና የሚመጣ ጥገናዊ ለውጥ ከፍ ብለን በቁጥር አንድ ካየነው ሑነት ብዙም የተለየ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። የቀለም ቅብ የመሠረት ችግር ያለበትን ቤት ከመፍረስ አይታደገውም፤ ምስጥ የበላውን ምሶሶ ቀለሙን በመቀያየር ለውድቀት ማትረፍ አይቻልም። በጥገናዊ ለውጥ የሚታለሉ ሰዎች በጥቂት ነገር የሚደለሉና ከመጀመሪያውም የነገሮችን ጥልቀት ያልተረዱ ብቻ ናቸው።
ሑነት (Scenario) ቁጥር ሦስት
ሥር ነቀል ለውጥ
ነገሮችን በጥሙና ስንመረምራቸው አሁን የተያዘው ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ዝግመታዊ ለውጥ አንድ ነገር ሥር ነቀል ለውጥ እየመጣ መሆኑን በቅጡ ያመለክታል። ይህ ሥር ነቀል ለውጥ ፍፁማዊ የመንግሥት ለውጥን ሊያመጣ የሚችል ርምጃ ነው። መንግሥት የፈቀደውን ያህል መሣሪያ የታጠቀ ቢሆን፣ የፈቀደውን ያህል አሰቃቂ እመቃ እና አፈና በማድረጉ ቢገፋም፣ አንዱን ብሔረሰብ ከአንዱ ማጋጨቱ ምንም ያህል በመንግሥት ደረጃ ቢናፈስም ይህ የኅዳጣን (የጥቂቶች) መንግሥት መውደቁ አይቀርም። ምናልባት መቅረብ ያለበት ጥያቄ «መቼ?» የሚለው ነው።
ሥር ነቀል ለውጡ ይዞት የሚመጣቸው በጎ ውጤቶች እንዳለው ሁሉ ላለፉት 25 ዓመታት በተፈፀሙ አፍራሽ ተግባራት ምክንያት አገሪቱን የሚያስከፍላት ዋጋም መኖሩ ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ሕወሐት የተደራጀ ኃይል እንደመሆኑ በአንድ ጊዜ ብን ብሎ ሊፈርስ የሚችል አይደለም። ነገር ግን መንግሥታዊ ሥልጣንን ተቆናጥጦ ለመቆየት ሕዝቡ አልገዛም ከማለቱ የተነሣ «ቤዝ« ወደሚለው የትግራይ ግዛት ሊያፈገፍግ ይችላል። ብዙዎቹ መሪዎቹና ደጋፊዎቹም ንብረታቸውን ወደማሸሽ፣ አገር ጥለው ወደመሸሽ ሊገቡ ይችላሉ። የዚያ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ መቆየታቸውን ልብ ይሏል።
ሕወሐት ወደ ቤዙ ማፈግፈግን ከመረጠ (ደርግ ትግራይንና ኤርትራን ለቅቆ ሲወጣ እንዳደረገው) በሰላም፣ ያለምንም ውድመት ይወጣል ብሎ መገመት የዋህነት ይሆናል። ከዚህ ቀደም በመሐል አዲስ አበባ ሳይቀር ፍንዳታዎችን በማቀነባበር «አሸባሪዎች ፈጸሙት» እንዳለውና ከጥቂት ሳምንታት በፊትም በመተማ ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን የዘር ፍጅት እንደደረሰባቸው በማስመሰል በደኅንነቱ በኩል እንዳሰደዳቸው ሁሉ (http://wazemaradio.com/?p=2853)፣ አሁንም በትግራይ ሕዝብ ንብረቶች እና ሕይወት ላይ እንዲሁም በተቀረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ንብረቶች ላይ ውድመት ሊቃጣ ይችላል የሚል ስጋት አለ። «ባልበላው ጭሬ ላፍሰው» የሚለው ተረት በተግባር ሲውል ስላየን ይህንን አለመጠበቅ የዋሕነት ይሆናል። ጥያቄው ለዚያ ጊዜ ያለን ዝግጅት ምንድነው የሚለው ብቻ ነው።
የሕወሐት የብረት አገዛዝ መላላት ብቻ ሳይሆን መሰባበር ሲጀምር ይኸው ቀውስ የንጹሐን ወገኖችን ሕይወት የሚያበላሽ እንዳይሆን በተለይም ቤተ ክርስቲያን እና ቤተ ክርስቲያንን የመሳሰሉ ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ሕወሐት በደህና ጊዜ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማሽመድመዱ ምክንያት እና ማኅበረሰባዊ ሰንሰለቱ ባይበጠስም እንዲቀጥን በማድረጉ ለዚህ ዓይነቱ ክፉ ጊዜ ይጠቅም የነበረውን ማኅበራዊ ካፒታል አባክኖታል። ስለዚህም ለችግር ጊዜ መድረስ ይገባት የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ያንን ሰማያዊ ኃላፊነቷን ልትወጣ የምትችልበትን አቅም አድክሞታል። መሪዎቿ በመለካዊነት የተጠመቁ በመሆናቸው ምክንያት የአስታራቂነትን እና የአረጋጊነትን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ዕድል በእጅጉ ተመናምኗል። በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት የተጎዳ በመሆኑ ቃላቸውን ሊሰማ የሚችል ሰው ማግኘት ከባድ ይሆናል። ከሕዝብ ጋር አብሮ ችግርን መካፈል፣ ስቃዩን መሰቃየት፣ ኃዘኑን ኃዘን ማድረግ የሚጠቅመው ለዚህ ዓይነቱ ክፉ ጊዜ ነበር።
ሕወሐት ሥልጣኑን ሲለቅ አሜሪካዊው ፓትርያርካችን ዜግነት ወደተቀበሉበት አገር መመለሳቸው የማይቀር ነው። እሳቸውም በተራቸው የስደት ሲኖዶስ፣ የስደት አስተዳደር፣ የስደት ካህናት ወዘተ ወዘተ ይዘው ይቀጥላሉ። በስደት አገር በሕዝቡ ላብ የተቋቋሙት አብያተ ክርስቲያናት ሰላም እና አገልግሎት በዚህ አይታወክም ብሎ መገመት የዋሕነት ነው። የዘመናችን ክፉ ፖለቲካ በአስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአገር ልጅነት፣ በብሔረሰብ እና በቋንቋ ላይ የቆመ እንደመሆኑ የአብያተ ክርስቲያናቱም አሰላለፍ ያንን መከተሉ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ በፊት የተሞከረ እንጂ አዲስ ነገርም አይደለም። እውነታውን ላለመመልከት ዓይናችንን ካልጨፈንን በስተቀር።
አገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ ስታደርግ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም ሥር ነቀል ለውጥ ይጠብቀዋል። ፓትርያርክ ማትያስና አጋሮቻቸው ስደትን መረጡም አልመረጡም በስደት ላይ የነበሩት አባቶች በፈንታቸው በኅብረትም ይሁን በየግላቸው ወደ አገራቸው መግባታቸው የሚጠበቅ ነው። ከ25 ዓመታት በላይ ከቤተ ክህነቱ አስተዳደር ተለይተው እንደመቆየታቸው የተሰደዱት ሲመለሱ በአገር ውስጥ ካለው ጋር ያለ ምንም ችግር ተዋሕደው አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ ምን ሊደረግ ይገባል? በዚህ 25 ዓመት በቤተ ክርስቲያን ላይ ወንጀል የፈፀሙ፣ ንብረቷን የዘረፉ ሰዎች አሉ። አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንጀሎች ተፈጽመዋል። የነበረው እንዳልነበር ሆኗል። ሥር ነቀሉ ለውጥ የበለጠ መተረማመስና ዝርፊያ የነገሠበት እንዳይሆን ዝግጅት እስካልተደረገ ድረስ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ለሚሉ ወንጀለኞች በር መከፈቱ አይቀርም።
እንግዲህ ዞሮ ዞሮ ጥያቄው ለቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ለሊቃውንቱ፣ ለምእመናኑ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ነው። አገራችን ላይ እየመጣ ያለውን ሑነት አስመልክቶ ምን ያህል ተዘጋጅተናል? የዳር ተመልካቾች ሆነን እንቅር ወይንስ በአገራችን ጉዳይ ወሳኝ ሚና እንጫወት? ጥቂት ግለሰቦች ከደም አፍሳሹ መንግሥት ጋር ወግነው በሚፈጽሙት በደል የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በሙሉ በዚህ ጥቁር ነጥብ ይበላሽ ወይንስ ይህንን የሚክስ ተግባር እንፈጽም? እዚህም እዚያም በግላችን እንጩህ ወይንስ በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ለአገራችን በአንድነት ድምጻችንን እናሰማ? ታሪካዊው ጥያቄ ቀርቦልናል። መልሳችን ይጠበቃል። ይቆየን