ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት 

በእውቀቱ ስዩ

image

ምኒልክ ጥቁረቱን ክዶ ነበር የሚል ቀደዳ በፌስቡክ ሲዞር ኣየሁ ልበል?

ትልልቅ ቅጥፈቶች ጀርባ ኣንድ ትንሽ መነሻ ይኖራል፡፡
መነሻውን እንመርምር እስቲ፡፡

ያድዋ ድል ማግስት የምኒልክ ዝና የጠራቸው የውጭ ኣገር ሰዎች ኢትዮጵያን መጎብኘት ጀምረው ነበር፡፡ ከኒህ እንግዶች ኣንዱ የሄቲው ታጋይ ጋዜጠኛ ቤኒቶ ሲልቪያን ነው፡፡

ሲልቪያንና ምኒልክ ያደረጉትን ጭውውት ስኪነር የተባለ ኣሜሪካዊ ዘግቦታል፡፡

በጭውውታቸው መሀል ምኒልክ ለሄቲው ሰውየi am not a Negro I am a Caucasian ማለቱን ስኪነር ዘግቧል፡፡

ምኒልክ ኔግሮ ኣይደለሁም ብለው ከሆነ ደግ ኣደረጉ ከማለት ውጭ የምለው የለኝም፡፡ ምኒልክ ጥቁር እንጂ ኔግሮ ኣይደለም።ኔግሮ የውርደት ስም ሲሆን ጥቁር የክብር ስም ነው፡፡

ኮኬሽያን የሚለው ቃል ግን ያስተርጓሚ ስተት መሆን ኣለበት፡፡በምኒልክ ዘመን ሰዎች ዘርን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ከብሉይና ሃዲስ የተቀዱ ናቸው፡፡የሴም ዘር የካም ዘር የያፌት ዘር ወዘተ ይሰኛሉ፡፡ ኮኬሽያን የሚለው ቃል በወዘተ ውስጥ ኣይካተትም፡፡ኮኬሽያን በጊዜው በሊቃውንቱም ሆነ በመኳንንቱ ኣንደበት የሚዘወተር ቃል ኣልነበረም፡፡

ምኒልክ የሚገዛቸው ህዝቦች ጥቁር እንደሆኑ ያምን ነበር፡፡
እንደ ኤውሮፓ ኣቆጣጠር በ1878 ለንጉስ ሊዎፖልድ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

“የኦሮሞ (ቃሉ ተተክቷል) የኣማራ የሱማል መልኩ ኣንድ ነው፡፡ ሁሉም ጥቁር ነው፡፡”
ምንጭ Acta Ethiopia vol 3 Edited by Sven Rubenson page302

ምኒልክ ጥቁረቱን ከመቀበል ኣልፎ ኣፍሪካዊ ጌቶች ጋር ጥቁረትን መሰረት ያደረገ ትብብር ጠይቆ ያውቃል፡፡ለምሳሌ ከሱዳኑ የማህዲስት መሪ ጋራ ሲደራደር የተናገረውን ታሪክ ጸሃፊዎች እንዲህ መዝግበውታል፡፡
Between us there has been no war. Now we have worse enemy who will make slaves of you and me.I am black :and you are black. Unite with me”
ትርጉም፤
”ባንተናኔ መሀል ጠብ ኖሮ ኣያውቅም፡፡ሁለታችንን በባርነት ሊገዛን የተሰናዳ የከፋ ጠላት ኣለብን፡፡ እኔ ጥቁር ነኝ፡፡ ኣንተም ጥቁር ነህ፡፡ እንተባበር“

ልብ በሉ ይህንን የሚለው ምኒልክ ነው፡፡

በካሊፋውና በምኒልክ መካከል የተደረገው ይህ ታሪካዊ ልውውጥ ተመዝግቦ የተገኘው ከጥልያኑ መኮንን ከባራቴሪ ማስታወሻ ውስጥ ሲሆን በእንግሊዝኛ ተርጉማ መጽሃፏ ውስጥ የዶለችውChris Prouty ናት፡፡Empress Taitu and Menilk በተባለው መጽሀፏ ገጽ 119 ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

በተረፈ “ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት”የሚለውን ያባቶቻችንን ምክር በመጋበዝ ልሰናበት፡፡

ይኸ አዲስ ይሆን? ማን ነው ሰላቢው? ማን ነው ጡት ቆራጩ?

image

ይኸ አዲስ ይሆን?
አስፋ ጫቦ

ገነሼ ማዳ የተባለ ሰው፤ጋሞ፤ሆላንድ በትምህርት ላይ ያለ፤ እዚሁ Facebook ላይ ዛሬ ጥዋት የነገረኝን ላካፍል ፈለግሁ። ጋላን/ ኦሮሞን ፤ጋሞ ጌርጌዳ ነው የሚለው አለ። ከዚህም ሌላ ኦቾሎና ዶኮ የጌርጌዳ መቃብር አለ፤ይህም የወረራረው ጦርነት ውጤት ነው የሚል ነው።
ኦቾሎ ማለት ከአርባ ምንጭ ወደጨንቻ ሲወጣ በስተቀኝ አንደ ጉዙፍ ምሰሶ ቆሞ የሚታየው አገር (ዴሬ) ነው። ዶኮ ደጎሞ ከጨንቻ ከተማ ምዕራብ፤ከኤዙሜ ወንዝ ወዲያ የሚታየው አገር(ዴሬ) ነው፤
እኔ ጌርጌዳን አውቃለሁ። የማየውቅ ጋሞ ያለ አይመስለኝም። እስከ 1956 ፤ማለትም ጋንታ ጋሮ የሚባለው ቦታ ህዝቡ ተንቅሎ አርባ ምንጭ ከተማ ከመሆኑ በፊት በየአመቱ መጥተው የሚዘርፉ፤ የሚስልቡ፤እርጉዝ ሴት ሳትቀር ሆድዋን ዘረጥጠው ሽሉን ወንድ ከሆነ የሚስሉቡትን ጉጂውች ጌርጌዳ እንደሚልዋቸው ነው። እንጅ ጌርጌዳ ማለት ጋሞ ጋላን/ ኦሮሞን መጥሪያ ስሙ አድርጌ አልወስደኩም ነበር።
ይህ ከኩሉፎ ወንዝ አርባ ምንጭ ጀምሮ አስከ ጨንቻ መታጥፊያ ያለው የስምጥ ሸለቆ ዘንበል ያለው አባያን የሚነካው ቦታ መሬት ጋንታ ጋሮ፣ሻራጋሮ፤ኦቾሎ ጋሮ ፤ይባላል። ጉጂዎቹ/ ጌርጌዳዎቹ የጋንታንና የሻርን ህዝብ ሲዘርፉም ሲስልቡም የኦቾሎን ህዝብ አይዘርፉም፤ አይስለቡም ይባላል። ለምን? ሲባል ከኦቾሎ ጋር እንዳይነካኩ ዉል ገበተዋል ይላሉ።

ይህ ከሆነ ይህ የሚያመለክተው ጋላ/ ኦሮሞ የወረረው ጊዜ/ወቅት ረዥምና (sustained) ለውል የሚያበቃ፤ የመቃብር ቦታ ሁሉ ለታሪክ የተወ ረዣዝም ጦርነቶች አድረገዋል ማለት ነው። ወይም ሊያሰኝ የሚችል በቂ አቅጣጫ ጠቋሚ የሚታዩ የሚዳሰሱ መርጃዎች አሉ ማለት ነው። የጌርጌዳ ጭፍጨፋን ድንገት አርጅተው ሊሆን ይችላል እንጅ የሚያዉቁ የጋንታ ፤የሻራ ሰዎች ዛሬም በህይወት ይገኛሉ ብየ አምናለሁ።ጋንታ የእናቴ የማቱኬ አገር ስለሆነና ልጅ ሁና ይህንን የጌርጌዳ ዘረፋና ጭፍጨፋና ወረራ የአይን ምስክር ብቻ ሳትሆን ብዙ ዘመዶችዋም ተፈጅተዋል። እኛም ይህንን እየሰማን ነው ያደገነው። የመጨረሻው የጌርጌዳ ስለባ የተፈጸመው በ1970ዎቹ ውስጥ ነበር። አባያ ሀይቅ ዳርቻ የተሰለበው የፖሊስ ባልደረባ ነበር።
ይህ ጋላና ኦሮሞ እያልኩ የተጠቀምኩት ስራዬ ብየ ነው።ጋላ ማለት ኦሮሞን የማከሰስና ዝቅ የማደርጊያ የንቀት ምልከት ነው እየተባለ ይነገራል። ነው እንዴ? እላለሁ።

ዓጼቴዎድሮስ ለንግስት ቪክቶርያ በጻፉት ደብዳቤ “አባቶቼ አምላክን ስለአሳዘኑ ጋላና እስላም ስደደባቸው” ይላሉ ዓጼ ቴዎድሮስ ጋላን ለማንኳሰስ ብለው ነው ጋላ ያሉት? ከዚያ በፊት የማያውቁትን ሕዝብ እንዴት ለምንስ ያንኳስሳሉ? ይንቃሉ? ዝቅ አድርገዋቸው አይተዋቸው ነው እንዳይባል ይኸው በጦርነት አሸንፈው “ያባቶቼ አገር” የሚሉትን ወስደውባቸዋል። ከዚህም ሌላ እኔው ራሴ በተዘዋወርኩባቸው የኦሮም አካባቢዎች አጋጣሚው ሲገኝ “አሁን ጋላ ብል መዝለፌ ነው!” ብየ እጠይቃለሁ። “ብትፈልግ ኦሮሞ ብትፈልግ ጋላ ልትል ትችላለህ!” የሚል መልስ በጠይኩ ቁጠር አገኛለሁ። የሚታየኝ ከዚህ ውስጥ የፖለቲካ ትኩሳቱን አውጥተን የዚህ ጋላ የሚለው ቃል ታሪካዊውና እርግጠኛ ምንጩ ምንና ከየት እንደሆነ ብናውቅ ምስሉን ሙሉ የሚያደርገው ይመስለኛል።
አንድ ሌላ ነገር ፤ ዶኮ ከበርብር ግፋ ቢል የ3 ስአት መንገድ ነው። ኦቾሎ ደግሞ ግፋ ቢል የ4 ሰአት መንገድ ነው። ብርብር ማለት አባ ባህርይ ዜናሁ ለጋላን የጻፉበት የብርበር ማርያም ያለችበት ባለፈው በዩሱፍ ያሲን መጽሐፍ ግምገማ ያነሳሁት ነው።ይኸ ከሆነ አባ ባህርይ የሰሚ-ሰሚ ሳይሆን ለጋላ ወረራ የዐይን ምስክር ሳይሆኑም አይቀሩም ወደሚል አስተያየት የሚወስደን ይመስላል።
ይህንን ነገር ለወዳጄ ፤ለዜናሁ ለጋላ ተርጓሚ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ልነግረው ፈልጌ ስልኩም አልስራ አለኝ፤ በemail አልመልስልኝ አለ። ያኔ፣ ዜናሁ ለጋላን ያሳተመ ስሞን የብርብር ማርያምን ፎቶግራፍ ልኬለት “ምነዉ ምነው አስፋ መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት ብትልክልኝ ሽፋን የማደገውን” ብሎ አዘነብኝ። አሁን ደግሞ በዚህም ሳያዝንብኝ የሚቀር አይመስለኝም። ከኔ የተሻለ ግኑኝነት ያላችሁ ብትነግሩት ደስታውንም አልችለውም።
ሌላ፤ ፊንፊኔ ከሚባል የኦሮሞ ራዲዮ ጣቢያ ጋርም የ2.30 ሰአት ያክል ቃለ ምልልስ አድርጌ ነበር። ኦሮሞ አዲሳባን ፍንፍኔ ይላል። ዕቴጌ ጣይቱ ደግሞ አዲስ አበባ አሉ። ጋሞ ደግሞ ቱንጋ ይላል።ቱንጋ ጥንት የጋሞ ዴሬ ነበር? 

ፊንፊኔ ራዲዮ እዚያ ተቀባይነቱ ጥሩ ሆኖ ተጨማሪ ብዙ ዘለፋ፤ ብዙ ትኩሳት ያለው ቃላት፤ ብዙ አርፋም ደፍቋል።Facebook ላይ የሰማሁትን ነዉ።ሁሉንም እቀበላለሁ።ሌላ ቦታ እንዳልኩት “አስፋ አደባባይ ውጣ፤ጻፍ ፤ተናገር፤ተናዘዝ!” ብሎ ያስገደደኝ ሰው የለም። ወድጄ ያደርግኩጉት ነውና ምርቱን እንዳለ እቀበላልሁ። ሌላ ቦታ እንዳልኩት ያሜሪካው ፕረሲዳንት የነበረው ትሩማን እንዳለው ወይም ብሏል እንደተባለው ነው:: If You Can’t Stand the Heat Get Out of the Kitchen” “ሙቀቱን፤ጢሱን የማትቋቋም ከሆነ ከማድቤቱ ውጣ!” እኔ ከዚህ ከኢትዮጵያ ማድቤት የምወጣ መስሎ አይታየኝም። ከሸጋው፤ከመጥፎውም ሆነ ከጥፉው። ያው እንደማንኛቸውም አገር በየአይነቱተሰጥቶናልና! ይልቁንም ከዚህ ታሪካዊ አዲስ ግኝት፤ከጢሱም ፤ከአረፋዉም ተጨማምቆ የተሻለ፤የሚያምር፤የሚበጅ ኢትዮጵያን ልናመጣ እንችላለን ብዬ አምማናለሁ!! አሰፋ ከሚደደፍቀዉ አረፋም የሚገኝ አለ ብሏል እንዳትትሉኝ! አረፋ ያፀዳል! ነዉ ያልኩት:: Yes! We Can!! ነው የሚሉት
አዎን !!እንችላለን!!