በኢትዮጵያችን በጥርስና በጥፍር የሚደረግ ትግል እንዴት ይቁም?

By ግርማ ሠይፉ ማሩ

image

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ/አንድነት አሳዛኙን የ2002 ምርጫ ውጤት ተከትሎ ፍራሽ አንጥፎ ኢህአዴግን ምርጫ ዘረፈ ከሚል መደበኛ ለቅሶ መውጣት አለብኝ ብሎ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰን ውስጣችንን መፈተሸ ተገቢ አቅጣጫ ነው ብሎ በማመን በእኛ በኩልስ የነበረው ችግር ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጎዋል፡፡ ይህ ነገሮች ወደ ውጭ ከማላከክ በዘለለ ሙሉ ቁጥጥር ባለን በራሳቸን ላይ የውስጥ ፍተሻ ማድረግ ጠቃሚና ተገቢ ነው ከሚል እምነት የመነጨ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የውጭ ጫናዎች በተለይም የኢህአዴግ አፈና የነበራቸውን ተፅዕኖ አሳንሶ ማየት እና የኢህዴግን አፋኝነትን ዝቅ አድርጎ መመልከት አድርገው የሚውስዱ ሰዎች አይጠፉም፡፡ ዋናው ጉዳይ እና ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የውሰጥ ጥንካሬና ድክመትን ማወቁ ነው የሚለው ነበር፡፡ በዚህም መነሻ አንድነት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የአምስት ዓመት ሰትራቴጂና ዕቅድ አዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሪፖርተርን የመሰሉ ጋዜጦች ተቃዋሚዎችን በጅምላ የሚመሩበት አቅጣጫ የሌላቸው አድርገው መፈረጃቸወን አላቆሙም፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ ይህን ተከትለው ከማሰተጋባትና ተቃዋሚዎችን በጅምላ ከመክሰስ ወደኋላ አላሉም፡፡ ለማነኛውም ፍረጃው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነት ያለፉትን አራት ዓመታት ጎዞዉን ባስቀመጠው ሰትራቴጅና አምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት አድርጎ ቀጥሏል፡፡ የእቅዱ ማጠቃለያ ዘመንም ከምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ጋር የሚገጣጠም ነው፡፡

ይህ የአምስት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወደፊት እንደሚካሄድ ታሳቢ ተደርጎ የመጨረሻው ዓመት ሊኖረን የሚገባው ዋነኛ ሰራ ምርጫን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ በጥርሱም በጥፍሩም ምርጫን ለማሸነፍ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እግረ መንገዱን ደግሞ የተቃዋሚዎችን በተለይም ደግም የአንድነትን ጥርስ ማውለቅና ጥፍር ማዶልደሙን ተያይዞታል፡፡ የጫወታው ህግ በጥርስም በጥፍርም መጫወት የሚፈቅድ ከሆነ ተወዳደሪዎች በተመጣጣኝ ጥርስም ጥፍርም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቦክስ ጫወታ ደረጃ የሚወጣው በኪሎ ነው፡፡  አጫዋቹም/ዳኛውም ጫወታው ከመጀመሩ በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ማረጋገጥ ያለበት ይህን ጉዳይ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ማሟላታቸውን ነው፡፡

አንድነት በዚህ ዓይነት የጥርስና የጥፍር ጫወታ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ለማድረግ እንደሚፈልገው የተወዳደሪን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም ተመጣጣኝ ምላሹ የገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም መፍትሔ ይሆናል ብሎ አያምንም፡፡ ለውድድሩ ጥርስም ጥፍርም አስፈላጊ ከሆነ የአንድነት ፓርቲ ጥርስና ጥፍር እንዳይጎዳ መጠበቅ ቅድሚያ ይሰጠው ነው፡፡ ይህ ነው በቁጥጥራችን ስር የሚገኘው እና ዋና ትኩረታችን ሊወስድ የሚገባ እንዲሁም ተገቢ ጊዜ መስጠት አለብን የምንለው፡፡ የገዢውን ፓርቲ ጥርስ ለማርገፍና ጥፍርሩን ለማዶልዶም የምናባክነው ጊዜ የራሳችን በመጠበቅ ብሎም በቁርጠኝነት ባለማስደፈር ቢሆን የበለጠ አዋጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡

በገዢው ፓርቲ መንገድ የምንሄድ ከሆነ ግን ወደፊት ለሚደረግ ውድድር በሁለቱም ወገን የሚኖሩ ተወዳደሪዎች በድድ እና በዱልዱም ጥፍር የሚወዳደሩ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጫወታውን ህግ መለወጥ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በዛሬው የጥርስና ጥፍር ተምሳሌት ዋነኛ ወካይ ባህሪዎች በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ነው፡፡ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን በተለይ የአንድነትን ጥርስና ጥፍር ላይ አደጋ አደረሰ ማለት በየደረጃው ያሉ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚወስዳቸው ቅጥ ያጡ ህገወጥ እርምጃዎች ማለታቸን ነው፡፡ በአፀፋው አንድነት ይህን ያድርግ ሲባል ደግሞ በኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ቅጥ ያጡ ሕገ ወጥ እርምጃዎች እንውሰድ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ኢትዮጵያዊያንን በፖለቲካ አቋማቸው ከመጉዳት የሚተናነስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ በተጎዳ ህዝብ ውስጥ ወደፊትም ቢሆን የተሸለ እና የሰለጠነ አማራጭ ይዞ በፖለቲካ መወዳደር ይቻላል የሚል እምነት አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው ጉልበታችንን የኢህአዴግ አባላትን ለመጉዳት ወይም ለመበቀል ሳይሆን የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን አቅም በማሳደግ የአይደፈሬነት ሰነልቦና ማዳበር መሆን ይኖርበታል የምንለው፡፡

በአንድነት በኩል የአባላቶቻችንን አቅም እናሳድጋለን ብለን ስንነሳ በዋነኝነት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውድድር የሚመነጨው አንዱ ሀገር ወዳድ ሌላው ጠላት ነው ከሚል መንፈስ፣ ወይም በግል በደረሰብን በደል በቁጭትና ለበቀል መሆን እንደሌለበት በማሰተማር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለያዩት በሚመርጡት የርዕዮተ ዓለም፣ ይህን ለመተግበር በሚያወጡት ፖሊሲና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች መሆኑን በማስረዳት በማስከተለም እነዚህ ልዩነቶች ሀገርን ሊጎዱ እንደሚችሉ ለህዝብ በማሰየት ህዝብ ለሚሰጠው ብይን ተገዢ ለመሆን ዝግጁ ሲኮን ነው፡፡ ይህን ልዩነታችንን ከጠባብ ቡድናዊ/የፓርቲ ወይም ሌላ ስብስብ ፍላጎት ከመነሳት “ሀገር ወዳድ እና የሀገር ጠላት”በሚል እንድንፈራረጅ ምክንያት ከሆነ የጋራ ሀገር እንዲኖረን እየሰራን ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለሁሉም ፓርቲዎች የጋራ መኖሪያ ከመሆን በዘለለ የሁሉም ፓርቲዎች አባላት የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን ለልጅ ልጆች በተሻለ ደረጃ ልናስተላልፋት ትልቅ ራዕይ ሰንቀን የምንቀሳቀስ መሆኑ በሁሉም ዘንድ መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያችን እንድትኖር እኛም በእርሷ እንድንኮራ በሁሉም ጎራ የተሰለፍን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለብን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
በኢህአዴግ በኩል የሚገኙ አባላት ብሎም ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ኪራይ ሰብሳቢ” ከሚል ቅጥ አንባሩ ከጠፋው ፍረጃ በላይ ግልፅ ሆኖ በወጣ መልኩ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፍን ዜጎች በፍፁም ለሀገር ደንታ የሌለን አድርገው መሳል የተለመደና አስልቺ ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ቆይቶዋል፡፡ ይህ በእውነቱ የኢህአዴግ በጥርስም በጥፍርም ለመጫወታ እንዲመቸው የሌላውን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶሚያ ስትራቴጂው ነው፡፡ ይህ መንገድ ግን ብዙ ርቀት የማያስኬድ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም የሚበጅ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡

በተቃዋሚ መስመር የተሰለፍን ሰዎች መካከልም ኢህአዴግን መሳደብ እንደ ዋና የትግል ሰልት የተያዘ እስኪመስ ድረስ ጥግ እንደምንሄድ አምኖ መቀበል ስህተታችንን ለማረም ጉልዕ ድርሻ አለው፡፡ አንዳንዴም የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ ከመግለፅ ይልቅ ሰነምግባር በጎደለው ሁኔታ በተለይ የግለሰቦችን ስብዕና የሚነኩ አላስፈላጊ የቃላት ጫወታዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ “ቅኔው ሲጣፋበት ቀረርቶ ሞላበት” የሚለው አባባል በሁለቱም ጎራ የመከራከሪያ ሃሰብ ድርቀት ምልክት ሊሆን ይቻላል፡፡ ይህንን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ከላይ እንደተገለፀው አባላትን በስነምግባር መኮትኮት እና ዋነኛው የፓርቲዎች ልዩነት መሰረት መሆን የሚገባው የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በከፍተኛ ሀገራዊ መግባባት ሰሜት መንቀሳቀስ ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ይዳብራል፡፡

girmaseifu32@yahoo.com
girmaseifu.blogspots.com

አቶ በላይ ፍቃዱ አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ፕሬዘዳንት ሆኑ፤ ኢንጂንር ግዛቸው በፍቃዳቸው ለቀቁ

አቡጊዳ

image

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አቶ በላይ ፍቃደን የድርጅቱ ፕሬዘዳንት አድርጎ መርጧል።

ከሰባት ወራት በፊት ድርጅቱን እንዲመሩ የተመረጡት ኢንጂነር ግዛቸው ፣ “ወጣቶችን ወደ አመራር አመጣለሁ፣ ወጣቶችን ባካችሁ አቅማችሁን አጎልብቱና ተኩኝ” በማለት ለወጣት አመራሮች ሃላፊነታቸውን ለማስረክብ ፍላጎት እንደነበራቸው መግለጻቸው ይታወቃል። ቃላቸውን በመጠበቅ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፊት መምጣታቸው ትግሉን ይረዳል የሚል እምነት ስላደረባቸው ኢንጂነር ግዛቸው፣ በፍቃዳቸው ሃላፊነታቸውን በመልቀቃቸው ነው፣ በድርጅቱ ሕገ ደንብ መሰረት፣ ብሄራዊ ምክር ቤቱ አዲስ አመራር የመርጠው።

አቶ በላይ ፍቃደ የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የሰሩ፣ በድርጅቱና አባልትና አገር ዉስጥም ሆነ ከውጭ ባሉ ደጋፊዎች ዘንድ፣ ከመኢአድ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ፣ ከትብብር …እንዲሁም ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት እንዳላቸው ይነገርላቸውል።

መንግስታዊ ሽብርተኝነትን የሚሸከም ትከሻ አይኖረንም!!!

SemayawiParty.org

image

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም

የህወሓት/ኢህአዲግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ዜጎችን በማፈንና በማሰቃየት ብሎም በመግደል የአፈና አገዛዙን ለረጅም ጊዜ ሲያራምድ መቆየቱ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማፈን እስራትና ግድያውን ህጋዊ ለማስመሰል የተለያዩ አፋኝ አዋጆችን አውጥቷል፡፡ እነዚህን አዋጆችንም ተገን አድርጎ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባለትን፣ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማት መሪዎችን እና በአገዛዙ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ማሰሩን፣ ማሰቃየቱንና ግድያውን ተያይዞታል፡፡ በህገ መንግስቱ የተካተቱ የሰብዓዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በሙሉ የሚጥሰውና የአምባገነንነት ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ያፀደቀው የፀረ-ሽብር አዋጅ ከፀደቀበት እለት አንስቶ ኢህአዴግ ለስልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን ፍፁም ሰላማዊ ታጋዮችንና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በድፍረት የፃፉ ጋዜጠኞችን ብሎም የእምነት ነፃነታችን ይከበር ብለው የጠየቁ የሀይማኖት መሪዎችን በጠራራ ፀሃይ ያለምንም ወንጀል በዚሁ ህገ ወጥ አዋጅ ‹‹የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል›› በሚባል ማንነቱ በማይታወቅ የጨለማ ቡድን ወደ እስር ቤት እያጋዘ ይገኛል፡፡

ይህን የሚያጋልጡ ሚዲያዎችንም ለማፈን እስር ቤቶችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያፈሰሰ የአየር ሞገድ ያውካል፤ በዚህ ሳያበቃ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ፖለቲከኞችን ለማሸማቀቅ እንደ ኢሳት ያሉ ሚዲያዎችን የአሸባሪ ልሳን ብሎ በመፈረጅ ሚዲያውን የሚጠቀሙትን ደግሞ ከአሸባሪዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው አድርጎ መወንጀሉን ቀጥሎበታል፡፡ እንደሰማያዊ እምነት ማንም አካል መልእክት የሚያስተላለፍበትን የሚዲያ ተቋም ሊመርጥለት እንደማይችል መንግስት እንዲገነዘበው ከዚህ በፊት በግልፅ ያሳወቀ ሲሆን አሁንም ፓርቲው በዚሁ የፀና አቋሙ እንደሚቀጥል በድጋሚ ይገልፃል፡፡

ባጠቃለይ የዚህን ገዢ አካል የእውር ድንብር ሀገር የማስተዳደር ጉዞ ለመታገል በርካቶች በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም በህወሓት/ኢህአዲግ ግፍና መከራ ተገፍተው ስርዓቱን በሃይል እናስወግዳለን ብለው ሀገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የህወሓት/ኢህአዲግ ማናለብኝነትና የስልጣን ጥመኝነትም በግለሰቦች ላይ ከሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ በላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋትን አስከትሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ይህ ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ስርዓት የሀገሪቷን ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር በማጥበብ ሀገራችንን ወደ አልተፈለገ አለመረጋጋትና ቀውስ እየመራት ይገኛል፡፡ፓርቲያችንም እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም በቅርቡ እየተፈፀሙ የሚገኙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ስላሳሰበው ይህን መግለጫ ለማውጣት ተገዷል:-

1. ሰኔ 16 2006 ዓ.ም የየመን መንግስት የዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን በመጣስና በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ በመግባት የአማፂ ቡድን ግንቦት ሰባት ዋና ፀሃፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዟ ይታወሳል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለህወሓት/ ኢህአዴግ ተላልፈው መሰጠታቸውን ከ16 ቀናት በኋላ መታወቁና ይህንንም ሁለቱ ሀይሎች ማመናቸው ተሰምቷል፡፡ ነፃነት በሌለበት ሀገር ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት የሌሎች ሀገር መንግስታት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በተለይ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጥላ የሚያጠላ መሆኑን ግንዛቤ አለመወሰዱ እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከተያዙ በኋላ ላለፉት 16 ቀናት በምን አይነት ሁናቴ እንደቆዩ ህዝብና ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁት አለመደረጉ፤ ስለ አያያዛቸው ሁኔታም በማህበረሰቡና በፓርቲያችን ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲኖር አድርጓል፡፡ሰማያዊ ፓርቲ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሰብዓዊ አያያዝ እያሳሰበው ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ አገዛዝ አያያዛቸውን ግልፅ እንዲያደርግ ሰብዓዊ ክብራቸውም እንዲጠበቅ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
2. በዚሁ ሳምንት ገዢው ፓርቲ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የአምባገነኑን መንግስት ህወሓት/ኢህአዲግን ሲታገሉ የነበሩ ፖለቲከኞችን በስመ አሸባሪ ከያሉበት እየለቀመ ህገ-ወጥ እስራት መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ ህወሓት/ኢህአዲግ ይህ ግብታዊ ተግባሩ ምንም እንኳን አዲስ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት ለውጥን ለማምጣት በቆራጥነት እየታገሉ ያሉ ሰላማዊ ታጋዮችን ማሰሩ በሀገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎችን ከአማፂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው በማስመሰል ሰላማዊ ትግሉን ለማዳከምና መጪውን 2007 ዓ/ም ምርጫ ያለ ተቀናቃኝ ለማለፍ የሚደረግ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የፓርቲያችን ብ/ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነው አቶ የሺዋስ አሰፋ በሰላማዊ ትግሉ በቁርጠኝነት እየተሳተፈ ባለበት ሁኔታ ለእስር መዳረጉ፤ የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፤ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር ላይ ያለው የአረና /ትግራይ/ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑትን አቶ አብረሃ ደስታ ለእስር መዳረጋቸው ህወኃት/ኢህአዴግ የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ በመሆኑም አገዛዙ እያካሄደ ያለውን መንግስታዊ ሽብር አቁሞ ለሀገርም ሆነ ለራሱ የሚበጀውን መንገድ እንዲከተል እያሳሰብን የታሰሩት የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ፓርቲያችንን መንግስት እያደረገ ያለው ሽብርን የመንዛትና ህግን የመጣስ ተግባሩ መቼም ቢሆን ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያቆመውና ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአፅንኦት እየገለፀ እነዚህንና ከላይ የተጠቀሱትን የገዢውን ፓርቲ መርህ አልባነት፣ ህገ-ወጥነት እና የለየለት አምባገነንነትን አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አጣምሮ የትግል ስልቱን ደረጃ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳለበት አምኗል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ለምናደርጋቸው ሀገር አቀፍ ንቅናቄዎች መላው የሀገሪቱ ህብረተሰብ በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን እያስተላለፈ ለዚህም ቁርጠኛ አመራር ለመስጠት ዝግጁነቱን ለመግለፅ ይወዳል፡፡በዚህ አምባገነንነትን ለመታገል በሚደረገው ንቅናቄም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ህጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች፤አለም አቀፍ ተቋማት፤የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ሲቪክ ማህበራት፤መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሰላማዊ ትግሉ ጎን በጋራ እንድንቆም እንጠይቃለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰማያዊ ፓርቲ
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም