አርማጭሆ መልስ፤ ወደ ወገራ ጉዞ ክፍል ፬

አርማጭሆ መልስ፤ ወደ ወገራ ጉዞ

ክፍል ፬

ከአርማጭሆ ጎንደር ስገባ ድርገት ነበር፡፡ በጣም መሽቷል፡፡ ቀበሌ 12 ቢራ ለመጠጣትና ወሬ ለመቃረም ገባሁ፡፡ የገባሁባት ቤት አንድ ጊዜ ከአንድ ወዳጄ ጋር አውቃታለሁ፡፡ የቀበሌ ቤት ናት፡፡ ቤቷ ከዐሥር ሰዎች በላይ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ አትችልም፡፡ ስለዚህ ደንበኞች በአንድ ሰዓት ከገቡ ሌላ የውጭ ሰው መግባት አይችልም፡፡ ከዚህች ቤት የማይዳሰስ ፖለቲካ አሊያም አገራዊ ጉዳይ የለም ማለት ይችላል፡፡ ቤቷን በወሬ ማድመቅ የሚችል ሰው መቼም ቢሆን ቢራ ከፍሎ ላይጠጣ ይችላል፡፡ ሞቅ ያለው የሰሊጥ ነጋዴ ‹‹አባቴ ይሙት!›› እያለ የሁሉንም ሰው የሳምንት ሒሳብ ሊዘጋ ይችላል፡፡ የቻልከውን ያክል እየጠጣህ መጫወት ነው፡፡

ከዚህች ቤት ብዙ ነገር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ የተሸከምነው አምባገነን ሥርዓት በዜጎች መካከል አለመተማመን ፈጥሯል፡፡ የዚች ቤት ደንበኞች ሕወሓት በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ግፍ ከመጠን የዘለለ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ከመጠጥ ደንበኞች መካከል የሰሜን ጎንደር ፖሊስ መምሪያ በኃላፊነት ቦታ ላይ እንዳሉ የተረደዋቸው ሰዎች ሁሉ ነበሩበት፡፡ የጎንደር ዐማሮች ሕወሓትንና የትግራይ ሕዝብን አንድ አድርገው ይመለከታሉ፤ እርግጥ ነው ይህ በብዙ የአገራችን አካባቢዎች እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ጎንደር ግን በግልጽ ያለ ምንም ፍርሐት እከሌ አለ የለም ሳይባል በግልጽ የሚወራ አሊያም የሚነገር ነው፡፡ ከዚችው መሸታ ቤት የሰማሁት እውነታ (ቀልድ ሊሆን ይችላል) አስተሳሰቡ ምን ያክል የሰረጸ እንደሆነ ሊሳይ ይችላል፡፡

አንድ ከሽሬ የመጣ ሰው ቸቸላ ሆስፒታሉ ጋር ለመሔድ መስቀል አደባባይ ላይ ባጃጅ ኮንትራት ይጠይቃል፡፡

‹‹ዋይ! አንተ ቸቸላ ሆስፒታል ስንት ትወስደኛለህ ኮንትራት?›› ይላል ከትግራይ የመጣው ሰው፡፡

የባጃጅ ሾፌሩ ‹‹መቶ ብር!›› በማለት ይመልሳል፡፡ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቸቸላ ሆስፒታል የኹለት ብር ታክሲ ትራንስፖርት ነው፡፡ ኮንትራት የሚይዝ ሰው ከዐሥር ብር የበለጠ አይከፍልም፡፡ ሆኖም እንግዳው ሰው ባልጠበቀው የዋጋ መናር ተገርሞ ‹‹ዋይ አቡነ አረጋይ! አንተ ለዚህ ቸቸላ ሙቶ ብር ያልከኝ አገሬን ሽረ አድርሰኝ ብልህ ስንት ልትወስደኝ ነው?›› በማለት የባጃጅ ሾፌሩን ጠየቀው፡፡

‹‹ተመልሰህ ካልመጣህ በነጻ እወስድሃለሁ!›› በማለት መለሰለት፡፡

ይህ እዚች መሸታ ቤት ሲነገር የሰማሁት ነው፡፡ መሸተኞች የራሳቸው ጓደኛ እንደተናገረው አድርገው ነው ያወሩት፡፡ ቁም ነገሩ እውነት ወይም ቀልድ መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ የትኛውም ቢሆን አገዛዙ የትግራይ ተወላጆች እንደ ባዕድ እንዲቆጠሩ አድርጓቸዋል፤ ትግሬዎች በየትኛውም የአማራ አካባቢ በጥርጣሬ ይታያሉ፡፡ ይህ ከኹለት ነገር ሊፈጠር ችሏል፡፡ አንደኛ አገዛዙ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚልካቸው ደኅንነቶች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ትግሬ የተባለ ፍጥረት ሁሉ የአገዛዙ አጋዥ እንደሆኑ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አገዛዙ የትግሬዎችን መጠላት የሚፈልገው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ትግሬዎች በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደጠላት ሲቆጠሩ አንድነታቸውን አጠናክረው ሕወሓትን ሊደግፉ ይችላሉ ከሚል ያረጀ ያፈጀ የፖለቲካ ፍልስፍና የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡

በጣም ረጅም የበረሀ መንገዶችን ሳቆራርጥ ሰንብቼ በምሽትም መሸታ ለመሸታ ቤት መንከራተቴ ያለኝን ጊዜ ለመቆጠብ መሆኑን አንባቢ ይረደዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ካደርኩበት የ‹ኤል ሸፕ› ሆቴል ሰማዩ ገና የአህያ ሆድ ሳይመስል ነቃው፡፡ በድካም የሰነበተ ሰውነቴን በቀዝቃዛ ውኃ ነክሬ በጠዋት ወደ ደባርቅ አቅጣጫ ወጣሁ፡፡ ትናንት ወደ አርማጭሆ የሔድኩበትን አቅጣጫ ትቼ ወደ ኮሶዬ አመራሁ፡፡ የዛሬው መንገዴ ትናንት የሔድኩበትን በርሀ ወደ ታች እየተመለከትኩ ደጋ ደጋውን ነው፡፡ ከጎንደር ከተማ ርቄ አሁን ወገራ ወረዳ እገኛለሁ፡፡ በደጋማው የወጋራ አፋፍ ላይ ሆኘ የአርማጭሆና የኹመራ ጫካ ታዬኝ፡፡ ‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካው›› አልኩኝ በውስጤ፡፡

የወገራ እረኛ በቅርርቶ፤

‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ

ላንተም ይሻልሃል ብቻን ከማደሩ፡፡

ተንኮለኛው ገደል በሬ ያሳልፋል፤ ዝንጀሮን ይጠልፋል

ጂል ያመጣው ነገር ለሁሉም ይተርፋል›› ኮሶዬ አፋፉ ላይ ሆኖ ዋሽንቱን ከድምጹ ጋር እያቀናጀ ይሸልላል፡፡

ምን ታደርገዋልህ! እኔ ከጫካ ጋር የማደር ልምድ የለኝም፡፡ ከራማዬ ከአርማጭሆና ከቋራ ጫካዎች ጋር ስላልሆነ ቻው ብያቸው መጥቻለሁ፡፡ እተራራው ላይ ሆኜ እንደገና ሳያቸው ለምን እንደ እናቴ ልጅ እንደናፈቁኝ አላውቅም፡፡ የምር ግን በጭጋግ የተሸፈነውን ከአድማስ ማዶ ዓይኔ እስኪታክተኝ የማየው የሆነ የሚናፍቅ፣ የሚስብ ነገር አለው፡፡ ‹‹አልበር እንዳሞራ›› ነው ነገሩ፡፡ ወይ እንደ አእዋፋት አሊያም እንደ መላእክት ሆኜ ክንፍ ቢኖረኝ ኖሮ ምንኛ በታደልኩ፡፡ በ‹‹ኖሮ›› አይኖርም፤ ወደ ከምናቤ ልወጣ ግድ ነው፡፡

የኮሶዬ ነፋሻማ ሜዳ ከጎንደር በግምት 15 ኪሎ ሜትሮች አካባቢ ይርቃል፡፡ ኮሶዬ ለዓይን የሚስብ ገደል ጫፍ ያለ ሜዳማ ቦታ ነው፡፡ ነፋሻማና ብርዳማ ነው፡፡ በጠዋት ስለደርስኩ የብርዱ ነገር አይጣል ነው፡፡ የኮሶዬ ሜዳ ገደሉ ጫፍ ላይ ሎጅ አለ፡፡ የሎጂው አልቤርጎዎች በእሳር ክዳን (ትኩል) የተሠሩና በነገሥታቱ የተሠየሙ ናቸው፡፡ ሎጂውን እየዞርኩ ስመለከት በአጼ ኃይለ ሥላሴና በንግሥት ኤልሳቤጥ የተሰየሙ የጎጆ አልቤርጎዎች (ትኩል) ሳይ ጊዜ ለምን እንደሆነ ሰዎችን ጠየቅኩ፡፡

ንግሥት ኤልሳቤጥ ኢትዮጵያን በ1956/7 ዓ.ም. ከንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ስትጎበኝ ካየቻቸው ቦታዎች መካከል የጢስ አባይ ፏፏቴና የሰሜን ተራሮች ይገኙበታል፡፡ የሰሜን ተራሮችን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ጎብኝታ ስተመለስ መስንግዶ የሚደረግበትን ቦታ መምረጥ ያስፈልግ ነበር፡፡ ከዚህ አካባቢ ከኮሶየ የተሻለ መስህብነት ያለው ቦታ ጠፋ፡፡ ከእከሌ ሆቴል አሊያም ሎጅ የሚሉት ነገር አልነበረም፡፡ ኮሶዬ መስኩ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የሰባውን ሰንጋ አርደው በብላክ ሌቨል ፋንታ የወገራን ጠላ ዘልለው፤ በእንግሊዝ ኬክ ፋንታ የጎንደርን እንጀራ አዋጥተው የታላቋን ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና የታላቋን ብሪታኒያ ንግሥተ ነገሥት ለመቀበል ዳስ ሠሩ፡፡ በዚህ ቦታ የሁለት ታላላቅ ርዕሳነ ብሔራት ተስተናግደዋል፡፡ ያኔ አሁን ከተራራው አናት ላይ ያለው ሎጂ አልነበረም፡፡ ያኔ ሎጅ ሳይሆን የቆርቆሮ ክዳን የነበረው ቤት አልነበረም፡፡ የሰው ልጅ ከሠራው ይልቅ ተፈጥሮ ያበጀችው እይታ ይማርክ ነበርና ነገሥታቱ ይህን ቦታ በድንኳንና በዳስ አረፉበት፡፡ እንኳን እኔ ሐበሻው ንግሥት ኤልሳቤጥም በዚህ ቦታ ውበት ለመማረኳ አልጠራጠርም፡፡

አሁን ካለው ዘመናዊ ሎጅ የሚያስተናግድ ልጅ ‹‹የታላቋን ብሪታኒያ ንግሥትና የታላቋን ኢትዮጵያ ንጉሥ በጊዜው ያስተናገዱ አዛውንት እዚያ ጋ አሉ፤ ማገኘት ትችላለህ›› አለኝ፡፡ በደስታ እየሮጥኩ ወደ አመላከተኝ ቤት ሔድኩ፡፡ የባህር ዛፍ መከላከያ ለበቅ ባልይዝ ኖሮ ቤት የነበረው ውሻ ይበላኝ ነበር፡፡ ሆኖም ውሻው ሲታገለኝ እደጅ የነበሩ የቤተሰቡ አባለት ደረሱልኝና በውሻ ከመነከስ ተረፍኩ፡፡ የታላላቅ አገሮቹን ንጉሥና ንግሥት ያስተናገዷቸው ሰው ማግኘት እንደምፈልግ ነገርኳቸው፡፡ መደብ ላይ የተቀመጡ አዛውንት አመላከቱኝ፡፡ ጠየቅኳቸው፡፡ እድልለኛ አልነበርኩም፡፡ እኔ ያገኘዋቸው የእድሜ ባለጸጋ ንጉሡና ንግሥቲቱ ሲስተናገዱ የተመለከቱ እንጅ እራሳቸው አስተናጋጅ አልነበሩም፡፡ የሆነው ሆኖ የእድሜ ባለጸጋው ከቤታቸው ወጣ ብለው ወደ ሜዳው በብትራቸው እያመለከቱ ‹‹ድንኳን የተጣለው እዚያ ላይ ነበር፤ አይ ምን የመሠለ ሠንጋ አርደን ነበር መሠለህ! ግን ያዘጋጀነውን ሁሉ በደንብ ሳይበሉ ትተውን ሔዱ›› አሉኝ፡፡ በጊዜው ርዕሳነ ብሔሮቹን ለማስተናገድ የተመረጠ ሰው አልነበረም ወይ? የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ አሁንም በድጋሚ ከቤታቸው በላይ ወደ ተራራማው ጫፍ እያመላከቱ ‹‹ወደ አቀበቱ መውጣት የምትችል ከሆነ መንገድ የሚመራህ ሰው ልስጥህ›› አሉኝ፡፡

የምችል አይደለሁም፡፡ ሩጫዬ ከጊዜም ከገንዘብም ጋር ነው፡፡ አንድ ቀን የጉዞዬን ጊዜ ባራዘምኩ ቁጥር የጋዜጣው መውጣት አለመውጣት ያሳስበኛል፡፡ ደግሞም በመንገድ ላይ የያዝኩት ስንቅ ቢያልቅ መመለሻ እንኳ አይኖረኝም፡፡ ስለዚህ በያዝኩት የጊዜ ገደብ መሠረት መጓዝ አለብኝ፡፡ የኮሶዬ ተራራ አናት ላይ ሆኜ ወደ በርሀው ስመለከት የተራራ ሰንሰለቶችን በጭጋግ ተሸፍነው አየሁ፡፡ ትናንት የነበርኩበት የአርማጭሆና የጠገዴ በርሃ በርቀት ይታየኛል፡፡ በእጄ የምነካት የምትመሥለው የጩጌ ማርያም ገዳምም ከሥሬ ናት፡፡ የጩጌ ማርያም ገዳም በድንጋያማ የተራራ ሰንሰለት ላይ ያለችና በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገደመች ናት፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ሒጄ አይቻታለሁ፡፡ አካባቢውን ለማያውቁ አንባቢያን የጩጌ ማርያም ገዳምን በትንሹም ቢሆን መናገር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ገዳሙን ለማየት ስሔድ የያዝኩትን ማስታዎሻ ሳገላብጥ የሚከተለውን አገኘሁ፡፡

የአገሬዉ ሰዉ ለሰዉ ብርታት የሚሰጥበትን ዘዴ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ የወገራ ሰዉ ‹በአገጩ በዚህ በኩል በጣም ቅርብ ነዉ!› ካለህ ቢያንስ ለሰዓታት ትጓዛለህ፡፡ በትሩን በረጅሙ እያጠቆመ ‹በዚያ በኩል ቅርብ ነዉ!› ካለህ ቢያንስ ለግማሽ ቀን ትሔዳለህ፡፡ ኮሶዬ ያገኘሁት ሰው ወደ ጩጊ በየት በኩል እንደምሔድ እንዲያሳየኝ አቅጣጫውን ስጠይቀው ሊነካት ያሰባት ይመስል እያንጋጠጠ ‹‹እዚች ተራራ ገደሉ ላይ የሆነ ቤት የሚመስል ነገር ይታይሃል?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ከአለንበት አፋፍ ገደል ሥር እየተመለከትኩ ጫካና አምባ ተራራ እንጅ ቤት አለመኖሩን ነገርኩት፡፡ ‹‹ያችን አምባ እያት እንጅ! ከአምባዋ ጎን ካለዉ ገደሉ ላይ ተመልከት ቤት ታያለህ!›› አለኝ፡፡ እንደምንም ከርቀት ከጭጋግ ጋር ለመለየት የሚያስቸግር ቤት አየሁ፡፡ ‹‹አየሁት አየሁት!›› ስል አጻፋ መለስኩ፡፡

‹‹ያች ብዙ ተዐምራት የተሰራባት ጩጊ ማርያም ገዳም ናት›› አለኝ፡፡ ‹‹በየት በኩል ነዉ መንገዱ?›› ተጨማሪ ጥያቄ አስከተልኩ፡፡

‹‹በዚህ ነዋ›› በግንጭሉ እየጠቆመ ገደሉን አሳዬኝ፡፡

‹‹እንዴ! ይህ እኮ እንኳን ለሰዉ ለዝንጀሮም አይመችም!›› አልኩት፡፡

ሳቀብኝና ‹‹ቅርብ ነች፡፡ በአንድ ሰዓት ውስጥ ደርሰህ መመለስ ትችላለህ!›› አለኝ፡፡ በወኔ መንገዱን ጀመርኩት፡፡

ይህን ገደል በሽርታቴ ተያያዝኩት፡፡ ገደሉ ያን ያክል እንዳየሁት የሚያስፈራ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በቀላሉ በስበት ኃይል እየተምዘገዘግኩ ወረድኩት፡፡ በጫካ ውስጥ ፈንዛ ጅራት ካላቸዉን ጉሬዛዎች እና ዝንጀሮዎች ጋር እየተላጋሁ ከራሴ ጋር እያወራሁ ሸመጠጥኩ፡፡ ዝንጀሮዎች እየጮሁ ገደል ለገደል ሲሮጡ መርግ ቢልኩብኝ እያልኩ በፍርሃት አስጨንቀውኝ ነበር፡፡ ደግነቱ በዛፎቹ ጥላ ሥር ስለምጓዝ ትንሽ ያስፈራል እንጅ ሙቀቱ አይታወቅም፡፡ በርቀት ገዳሙን እያየሁ የደረስኩ እየመሰለኝ እኔም በአገጬ ለመንካት እየሞከርኩ ለአንድ ሰዓት ያክል ለመጓዝ ተገደድኩ፡፡

ገዳሙ መግቢያ አካባቢ አፈሩ አንሸራቶ ጉድ ሰርቶኝ ነበር፡፡ ከዚያ ቦታ ላይ ብወድቅ ማንም ሳያየኝ መዳረሻዬ ተጨማሪ ኹለት ሰዓት የሚያስኬድ ገደልን እጨርስ ነበር፡፡ ሸርተት ካሉ መዳረሻው የማይታወቅ አገርና ዓለም ነው፡፡

ገዳሙ ያለበት እጅግ ገደል የበዛበት ሰንሰለታማ የድንጋይ አምባ ነዉ፡፡ መነኮሳቱና አርድዕቱ በገደሉ ላይ እንደዚያ ሲሮጡ በዝንጅሮቹ የገደል ላይ ጉዞ መደነቄ አናደደኝ፡፡ በዚያ ገደል ‹ሰዉ ዓለምን ንቆ በባዕት ለእድሜ ልካቸዉ የሚኖሩ መነኮሳት› እንዳሉ ማየት እጅግ ይገርማል፡፡ እኔ ላንድ ቀን እንቅልፍ ወስዶኝ የምተኛ አይመስለኝም፡፡

ይህ ገዳም የተገደመው በአባ ምዕመነ ድንግል በአስራ ሰባተኛዉ ክ/ዘመን ነዉ፡፡ በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት (ከ1600- 1624 ዓ.ም.) አባ ምዕመነ ድንግል ብዙ መከራንና እንግልትን እንደተቀበሉ ገድላቸው ይመሰክራል፡፡ ገዳሙ ካለበት የቋጥኝ ተራራ ወገብ ላይ ዋሻ አለ፡፡ ዋሻዉ ውስጥ ደግሞ በክረምትም በበጋም የማይሞላ የማይጎድል ‹ማዬ ዮርዳኖስ› ወይም ‹የዮርዳኖስ ዉኃ› የሚሉት አለ፡፡ ጸበሉ በርካታ ምዕመናን ይጠመቁበታል፡፡ ግን አይጎድልም፡፡ የሚጠመቅ ሰዉ ከሌለም ሞልቶ አይፈስም፡፡ አፈር በሆነበት ቦታ ምንጮች እየደረቁ ባለበት ጊዜ ግጥም ካለ ቋጥኝ ተራራ ላይ ይህ መሆኑ ለእንደኔ ዓይነቱ ተጠራጣሪ አጃኢብ ያስብላል፡፡ ጸበሉን ጠጣሁት- አይሰለችም፡፡ እንዲያዉም እዉነት ለመናገር ከመጣሁ በኋላ ናፍቆኛል፡፡ መልኩ ሀጫ በረዶ ይመስላል፡፡ በመቆሙ ብዛት አረንጓዴ (አልጌ) አልጣለበትም፡፡ ይህን ጸበል ጠጣሁትም፤ ሲያጠምቁ ያገኘዋቸው አባም አጠመቁኝ፡፡

ብቻ ግሩም ነዉ እላችኋለሁ፡፡ ጸበሉን የሚጠጡ ፍጥረታት ገላቸው (አካላቸዉ) አይፈርስም፡፡ ጸበሉን የጠጡ 16 ፍየሎች ከነ ሙሉ አካላቸዉ ለ400 ዓመታት ለገባሬ ታእምር እስካሁን አሉ፡፡ ወልደዉ ለመሳም ያልታደሉ ሰዎች ከዚህ ቦታ መጥተዉ ተጠምቀዉ ጸበሉን ቢጠጡ የልጅ ጉጉታቸዉን እዉን ለማድረግ ዘጠኝ ወራት ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው ከገዳሙ ያገኘዋቸው አርድእት ነግረውኛል፡፡

ቦታዉ የዋልድባዉ ሰቋር ኪዳነ ምህረት ዓይነት ነዳላ አምባ አለዉ፡፡ ወደ ነዳላዉ አምባ ለመሄድ ጸበሉን የጠመቁኝ አባት በዚህ በኩል ሒድ አሉኝ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ እያመለከቱ፡፡ በተቀደሰዉ ቦታ ጫማህን አዉልቅ በሚለዉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ መሠረት ጫማ መልበስ ክልክል ነዉ፡፡ ጫማ የለመደ እግር በሚያቃጥል አለትና በሚቆረቁር አሸዋ ላይ መሔድ ይጠበቃል፡፡ በዚያ ድንጋያማ ተራራ እንደ ገበሎ አስተኔ በልብ አሊያም በአራት እግር መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ከዋሻዉ ማዶ ‹ሰማያዊ ኬንዳ› የመሰለ ነገር ማዶ ካለዉ ገደል ላይ ተንጣሎ ይታያል፡፡ ያ ኬንዳ ምንድን ነዉ? ስል ጠየቅኩ፡፡ በተቀደደዉ የቋጥኝ ተራራ አልፎ የሚታየዉ ሰማይ ነዉ አሉን አባ፡፡ ከጸበሉ የነበረች አንዲት እናት ጋር አብረን እንድንሔድ አባ ነገሩን፡፡ ጉዞ ወደ ነዳላዉ አምባ፡፡ አብራኝ የምትጓዘዉ እናት እጅግ የበረታች ናት፡፡ እርሷ በዚያ ገደል ላይ ከዝንጀሮ እኩል ትፈጥናለች፡፡ ተከተልኳት፡፡ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እየወጣን ወደ ነዳላዉ አምባ ተቃረብን፡፡ ወደ ገደሉ ስንወጣ በእጃችን እየቧጠጥን ነው፤ በእጃችን አጥብቀን ከመያዛችን በፊት ያገኘነውን ጎቶ ጥንካሬ መለካት ያሻል፤ አሊያ ዲካው ወደ ማይታወቀው ገደል መጓዝ ይመጣል፡፡ ከቦታዉ ስንደርስ አንድ ሽማግሌ አባት ከንቃቃት ድንጋይ ሥር እንደቤት አደርገዉ ሲጸልዩ ደረስን፡፡ አባ ከባዕታቸዉ ፈጽመዉ አይወጡም፡፡ የምጽዋት ገንዘብም ፈጽመዉ አይቀበሉም፡፡ ፎቶ ግራፍና ምስል እንድወስድ ብጠይቃቸዉ ‹‹ልጄ አወግዝሃለሁ›› አሉኝ ተቆጥተዉ፡፡ ይቅርታ ጠይቄ አቡነ ዘበሰማያት ደግመዉልኝ በበረከት ተለየዋቸዉ፡፡

በመጨረሻ እኔን ጠየቅኩት? ‹አባቶች ለነፍሳቸዉ እና ለአገር ደኅንነት ከዱር አራዊት፣ በልባቸዉ ከሚሳቡ ነፍሳት ጋር ሁሉ እንዲህ ይታገላሉ፡፡ እኔ ግን ከዚህ ድረስ መጥቼ በረከት እንኳ መውሰድ እንዴት ተሳነኝ?› እማሆይ ማዕድ አቀረቡልን፡፡ በላን፡፡

በልቤ የአባቶቼን ጽናት እያሰብኩ ወደ መጣሁበት ዓለም ለመመለስ ተነሳሁ፡፡ ከፊቴ አምዘግዝጎ ያረወደኝን ገደልና ጫካ ለመዉጣት፡፡ ዝንጀሮዎቹን ቢያዝሉኝ ስል ተመኘሁ፡፡ ዛፍ ለዛፍ የሚሯሯጡት ዝጉርጉር ጉሬዛዎች አስቀኑኝ፡፡ በ180 ዲግሪ ቀጥ ያለው የወገራ አቀበት ፊቴ ላይ ተደቀነ፡፡

……….

ወደ አያሌው ብሩ አገር ዳባት መንገድ ጀምርኩ፡፡ አምባ ጊዎርጊስ፣ ገደብዬ፣ ዳባት፣ ወቅን፣ ደባርቅ…፡፡ ዳባት ላይ የአያሌው ብሩ ቤተ መንግሥት አለ፡፡ አያሌው ብሩ የወገራ ገዥ የነበሩ ሲሆን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ሀትሪክ ተሠርተዋል አሉ፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ አዲስ አበባ እንዲሔዱ ጥሪ ሲልኩባቸው የወገራ ሰው እንዳይሔዱ መክሯቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የወገራን ሰው ምክር ባለመሥማታቸው የአጼው ተንኮል ሰለባ ሆነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ድፍን በጌምደሬ ሲዘፍን ‹‹አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ ሰው አማኙ፤ ኧረ አያሌው ተው በለው ተው በለው›› የሚለው የእርሳቸውን ሞኝነት ለማመለከት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቀሪውን ማጣራት የባህል ተመራማሪዎች ፋንታ ይሆናል፡፡

አምባ ጊወርጊስ ላይ ሆኖ ወደ ደባርቅ ሲመለከቱ አንዲት ኮረብታ በርቀት ትታያለች፡፡ ዳባት ላይ ሆኖም ይህችው ተራራ ከትክተት አትሰወርም፡፡ ዳባትን አልፈን ደባርቅ ሆነንም እናያታለን፡፡ የሰሜን ተራሮች አናት ላይ ብንወጣም ይህችን ተራራ ማንም አይጋርደንም፡፡ ይህች ተራራ ‹‹ወቅን›› ከተባለች አነስተኛ ከተማ ራስጌ ላይ የምትገኝ ስትራቴጂክ አምባ ናት፡፡ ስያሜዋም ‹‹ዞሮ ዞሮ ወቅን›› ትሰኛለች፡፡ ዞሮ ዞሮ ወቅን ከወገራ እስከ ኹመራ፣ ከአርማጭሆ እስከ ጃናሞራ፣ ከአዲአረቃይ እስከ ሽሬ ድረስ ቁልጭ ብላ በጉልህ ትታያለች፤ ዞሮ ዞሮ ወቅን፡፡

የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን የስድብ ውርጅብኝ

 

የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል” በማለት፣ ለብአዴን ነባርና አዳዲስ ካድሬዎች ተናግረዋል።

ካድሬዎቹ “የአማራው ህዝብ ለምን ይሰደዳል? ለምን በእየክልሉ ጥቃት ይደርስበታል? አማራውን ከጥቃት ለመከላከል ለምን ሙከራ አይደረግም በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ም/ል ፕሬዚዳንቱ የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው ከሌላው ጋር ለመኖር መልመድ አለበት ብለዋል።

አማራው “በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪውና የብአዴን የጽህፈት ቤት ሃላፊው፣ ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ አክለዋል።
ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት ያሉት አቶ አለምነው፣ ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም ሲሉ ድምድመዋል።
ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምክንያቱንም ሲገልጹ ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው ብለዋል። ያንን ምግብ እየተመገበ እንደሚያቅራራም ገልጸዋል።

እሳትን ያድምጡ