ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት 

በእውቀቱ ስዩ

image

ምኒልክ ጥቁረቱን ክዶ ነበር የሚል ቀደዳ በፌስቡክ ሲዞር ኣየሁ ልበል?

ትልልቅ ቅጥፈቶች ጀርባ ኣንድ ትንሽ መነሻ ይኖራል፡፡
መነሻውን እንመርምር እስቲ፡፡

ያድዋ ድል ማግስት የምኒልክ ዝና የጠራቸው የውጭ ኣገር ሰዎች ኢትዮጵያን መጎብኘት ጀምረው ነበር፡፡ ከኒህ እንግዶች ኣንዱ የሄቲው ታጋይ ጋዜጠኛ ቤኒቶ ሲልቪያን ነው፡፡

ሲልቪያንና ምኒልክ ያደረጉትን ጭውውት ስኪነር የተባለ ኣሜሪካዊ ዘግቦታል፡፡

በጭውውታቸው መሀል ምኒልክ ለሄቲው ሰውየi am not a Negro I am a Caucasian ማለቱን ስኪነር ዘግቧል፡፡

ምኒልክ ኔግሮ ኣይደለሁም ብለው ከሆነ ደግ ኣደረጉ ከማለት ውጭ የምለው የለኝም፡፡ ምኒልክ ጥቁር እንጂ ኔግሮ ኣይደለም።ኔግሮ የውርደት ስም ሲሆን ጥቁር የክብር ስም ነው፡፡

ኮኬሽያን የሚለው ቃል ግን ያስተርጓሚ ስተት መሆን ኣለበት፡፡በምኒልክ ዘመን ሰዎች ዘርን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ከብሉይና ሃዲስ የተቀዱ ናቸው፡፡የሴም ዘር የካም ዘር የያፌት ዘር ወዘተ ይሰኛሉ፡፡ ኮኬሽያን የሚለው ቃል በወዘተ ውስጥ ኣይካተትም፡፡ኮኬሽያን በጊዜው በሊቃውንቱም ሆነ በመኳንንቱ ኣንደበት የሚዘወተር ቃል ኣልነበረም፡፡

ምኒልክ የሚገዛቸው ህዝቦች ጥቁር እንደሆኑ ያምን ነበር፡፡
እንደ ኤውሮፓ ኣቆጣጠር በ1878 ለንጉስ ሊዎፖልድ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

“የኦሮሞ (ቃሉ ተተክቷል) የኣማራ የሱማል መልኩ ኣንድ ነው፡፡ ሁሉም ጥቁር ነው፡፡”
ምንጭ Acta Ethiopia vol 3 Edited by Sven Rubenson page302

ምኒልክ ጥቁረቱን ከመቀበል ኣልፎ ኣፍሪካዊ ጌቶች ጋር ጥቁረትን መሰረት ያደረገ ትብብር ጠይቆ ያውቃል፡፡ለምሳሌ ከሱዳኑ የማህዲስት መሪ ጋራ ሲደራደር የተናገረውን ታሪክ ጸሃፊዎች እንዲህ መዝግበውታል፡፡
Between us there has been no war. Now we have worse enemy who will make slaves of you and me.I am black :and you are black. Unite with me”
ትርጉም፤
”ባንተናኔ መሀል ጠብ ኖሮ ኣያውቅም፡፡ሁለታችንን በባርነት ሊገዛን የተሰናዳ የከፋ ጠላት ኣለብን፡፡ እኔ ጥቁር ነኝ፡፡ ኣንተም ጥቁር ነህ፡፡ እንተባበር“

ልብ በሉ ይህንን የሚለው ምኒልክ ነው፡፡

በካሊፋውና በምኒልክ መካከል የተደረገው ይህ ታሪካዊ ልውውጥ ተመዝግቦ የተገኘው ከጥልያኑ መኮንን ከባራቴሪ ማስታወሻ ውስጥ ሲሆን በእንግሊዝኛ ተርጉማ መጽሃፏ ውስጥ የዶለችውChris Prouty ናት፡፡Empress Taitu and Menilk በተባለው መጽሀፏ ገጽ 119 ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

በተረፈ “ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት”የሚለውን ያባቶቻችንን ምክር በመጋበዝ ልሰናበት፡፡

‹‹ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር፡፡››

…………….. ‹‹ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር፡፡›› …………

492-433 ከክርስቶስ ልት በፊት የኖረውና የታሪክ አባት ተብሎ የሚታወቀው ሄሮዶቱስ ስለኢትዮጵያ ሲናገር ‹‹…እስከ ኤለፋንቲን (የአሁኑ አስዋን) ዳርቻ ድረስ ሄጃለሁ፤ ኢትዮጵያውያን ከኤለፋንቲን ደሴት ጀምሮ ከግብጽ ወደ ደቡብ የሚገኘው አገር ሁሉ ይኖሩበታል። ኢትዮጵያውያን ረጃጅሞችና የላቁ ቆንጆዎች ሲሆኑ በባህላቸውም ከሌላው አለም የተለዩ ናቸው፤አማልክቶቻቸውም ዜውስ እና ዲዮናስዮስ ብቻ ናቸው ፡፡›› Herodotus: The Histories. ትርጉም በመማር፡፡

ሌላው ታላቁ ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ደግሞ ስለ ኢትዮጵያውን መልካም ስነምግባርና ስለ ሀቀኝነታቸው ሲቀኝ ‹‹ አማልክት ከኢትዮጵያውያን ጋር የወሲብ ግንኙነት ለማድረግ ስሜታቸው ይቀሰቀስ ነበር፡፡›› ብሎ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በተጓዘችባቸው ሶስት ሺህ (ኧረ እንዲያውም ከአምስት ሽህ ዓመታት በላይ ነውም ይባላል .. ፕ/ር ላጲሶ ጌዴሌቦ) የመንግስትና የሀገር ምስረታ ዓመታት ቀደምት አባቶቻችን አያሌ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ለአንድነቷና ለነፃነቷ ሲሉ ከበርካታ ተስፋፊና ወራሪ መንግስታት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው በደማቸውና በአጥንታቸው ባመጡት ድል ከፍ ብለን እንድንታይ አድርገውን አልፈዋል፡፡ በሰላም ጊዜ ገበሬ፤ ሀገር ስተወረር ደግሞ ጀግና ወታደር ይሆኑ የነበሩት አባቶቼ ሁሌም ይህችን ሀገር እንዴት አድርገው እንዳቆዩልኝ ሳስበው ይገርመኛል፣ ልናገር የምችለው አንድም ነገር አላገኝም፤ ቃላቶቹ አፌ ውስጥ እንደ ጨው ይሟሟሉ፡፡ መናገር ካለብኝ ግን የኔ ውድ ጂጂ የተጠበበችበትን ‹‹አድዋ›› ደግሜ ደጋሜ እዘምራለሁ፡፡ ታላቁ ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህንም የተቀኘውን ‹‹አድዋ ሩቅዋን›› ቀጥየ አነበንበዋለሁ፡፡

የሰው ልጅ ክቡር፣
ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር፡፡
………………………………….
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተክፍሎበታል ከደም ከአጥንት፡፡

በ 1884 እ.ኤ.አ ሃያላኖቹ የአውሮፓ መንግሥታት፣ በጀርመን በርሊን ከተማ ተሰባሰቡና በመካከላቸው የነበረውን መናናቅና አለመስማማት ለጊዜው ወደ ጐን ትተው አፍሪካን ለመቀራመት መከሩ፤ ከዚያም አፍሪካውያን ሰዎች ሳይሆኑ ትልልቅ ‹‹ትሎች›› ‹‹ቅንቡርሶች›› ናቸው፤ ስለዚህም እኛ እንሂድና መሬታቸውን እንውሰድ ብለው ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በዚህ ስምምነታቸው ኢትዮጵያን ጣ ልያን እንድትወስድ ገጸ በረከት ተሰጠቻት፡፡ ጣልያንም ይህንን በልቧ ይዛ መስከረም 21 ቀን 1981 ዓ. ም ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ውል ተዋዋለች፡፡ ይህ ውል በኢትዮጵያው እንደራሴ ራስ መኮንንና በጣልያን ንጉስ ተወካይ በፍራንሲስኮ ክሪስፒ መካከል በናፖሊ ከተማ ኢጣልያ ውስጥ ተፈረመ፤ የውጫሌ ስምምነት፡፡

ታድያ ጣልያን ይህን ውል እየተዋዋለች ያለችው ከአንድ ሀያል ህዝብ ጋር መሆኑን ዘንግታ ነበረና በውሉ የጣልያንኛ ቅጂ አንዱ አንቀጽ ላይ ሆን ብላ አንድ መሰረታዊ ነገር ገደፈች፤ አንቀጽ 17 ላይ፡፡ የውሉ የአማርኛ ቅጂ አንቀጽ – 17 ላይ እንዲህ ይላል “ኢትዮጵያ ከማንኛውም የውጭ ሀገር ጋር ስትገናኝ በጣልያን በኩል ማድረግ ይቻላታል፡፡” የጣልያንኛው ቅጂ ላይ ደግሞ “ኢትዮጵያ ከማንኛውም የውጭ ሀገር ጋር ስትገናኝ ግንኙነቱን በኢጣልያ በኩል ማድረግ አለባት::” ይላል፡፡ የአማርኛው ይቻላታል (ከፈለገች) እንደማለት ሲሆን፣ የጣሊያንኛው ቅጂ ደግሞ አለባት (የግድ በኢጣልያ በኩል መሆን አለበት) የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ጣልያንም ይህንን ውል ለሌሎች መንግስታት በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት የቅኝ ግዛት አስተዳድር መመስረቷን አስታወቀች፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ኢትዮጵያ ለጣልያናውያን ትልልቅ ትሎች የሚርመሰመሱባት ችጋራም ሀገር እንጂ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የሆነች ታላቅ ሃገር አይደለችም፤ የአክሱም ነገስታት ሀገር፣ ላሊበላን የገነቡ ህዝቦች ሃገር አይደለችም፡፡

የሸዋው ንጉስ ኃይለ መለኮት ልጅ፣ የንግስት ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ባለቤት፣ የታላቋ ኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ምኒልክ ግን ይህን የጣልያንን አይን ያዋጣ ሌብነት ቆይተውም ቢሆን ተረዱት፡፡ ከዚያ ታላቁና ገናናው ንጉስ እምየ ምኒልክ፤ ይህማ አይሆንም እምቢኝ አሻፈረኝ !! ከፈለግሽ ይህን አንቀጽ አስተካክይ አይሆንም ካለሽ ደግሞ ሀገሬ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ለዚህ ህግ አትገዛም ብለው ለጣልያን መልዕክት ላኩ፡፡ ንጉሱም ወቅቱ ለዘመቻ አመችና ቶሎ ጣልያንን መውጋት የሚያስፈልግ መሆኑን መክረውበት በየካቲት ወር 1885 ዓ. ም የውጫሌን ውል በዓዋጅ ሻሩ፡፡ ለዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ መንግስታት በሃገራቸው ላይ የተቃጣው ተንኮል የሚያወግዝ ደብዳቤ ጻፉ፡፡ በደብዳቤው ላይ የኢጣልያንን ጠባ ጫሪነት ከመኮነን ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ገዳሪፍ፣ ካርቱም፣ ቦረና፣ ኦጋዴንንና የሶማሌ ጠረፍን ጨምሮ እንደሆነ አሳወቁ፡፡ ጣልያንም ሟች ነበረችና ያንቀዠቀዣት ጀመር፤ ኢትዮጵያንም ለመውጋት ጦሯን ሰብቃ ተንቀሳቀሰች፡፡ በአራት ጀኔራሎች የሚመራውንም ስለጡን ጦሯን ወደ አድዋ ተራሮች ላከች፡፡ ከዚያም ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካ እና ጥቁር ህዝብ መመኪያ የሆነው፣ በባርነት እየማቀቁ ለነበሩት ጥቁር ህዝቦች ከተራራ ላይ እንደሚንገቦግ ችቦ፣ ከሩቅ የሚታየው የነጻነት ወጋገን አድዋ ያኔ ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን የጣልያንን ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ድምጥማጡን አጠፉት፡፡ የጣልያን ህዝብም በንጉሳቸው ኢማኑኤል ላይ ኡኡታውን አሰማ፡፡ በሮማ አደባባይ ላይ ምኒልክ ለዘላለም ይኑር ብለው ጮሁ፡፡ በመላው አለም ያሉት ጥቁር ህዝቦችም ታላቁን ንጉስ እምየ ምኒልክን በሌሉበት የነጻነት ትግል መሪ አድርገው መረጧቸው፡፡

ትናገር አድዋ ትናገር ሀገሬ፤
እንዴት እደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፡፡

ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹The Battle of Adwa›› ባለውና ሙሉቀን ታሪኩ ‹‹ አፄ ምኒልክ እና የአድዋ ድል›› ብሎ በተረጎመው መጽኀፍ ላይ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ይህ ድል የዓለምን ተለምዷዊ ስርዓት የቀየረ ታሪክ ነው፡፡››
‹‹አድዋ ለኢትዮጵያውያን ደማቅ ድል፤ ለዘመናዊቷ ጣልያን ደግሞ ከፍተኛ ውርደትን ያከናነበ የሁለት ሀገራት ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ እንደኔ አመለካካት የዓድዋ ድል የዓለም ታሪካዊ ቅርስ ነው፡፡ ከዓድዋ በኋላ የዓለማችን ታሪካዊ እውነታ ተቀይሯል፡፡ በዓድዋ የተነሳ በአፍሪካ የነበረው የአውሮፓውያን አገዛዝ ከሃምሳ ዓመታ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አክትሟል፡፡ በእርግጥም ዓድዋ ለጥቁር አፍሪካ መለያ መሆን የቻለ ድል ነበር፡፡››

ለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሲሰጣቸው መልካምነትም፣ ሩህሩህ ልብም ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ለጀግና፣ የጠላትም ቢሆን ትልቅ ክብር ይሰጣሉ፡፡ ወደ አድዋ ከሄዱት ታላላቅ ሰዎች አንዱ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ አባት ራስ መኮንን አንዱ ነበሩ፡፡ ታድያ እኒህ የምኒልክ መመኪያ የጦር መሪ የሀረሩ ልዑል ራስ መኮንን በጊዜው አምባላጌን ይዟት የነበረውን ቶልሲን የተባለውን የጣልያን ሻለቃ እንዲህ ብለውት ነበር “ ውድ ወዳጄ ሻለቃ ቶልሲ ጀግንነትህንና ቆራጥነትህን አውቃለሁና አከብርሃለሁ አደንቅህአለሁም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጦርነት ትሸነፋለህ ስለዚህ አምባላጌን ለቀህ ሽሽ፡፡ ስትሸሽም መቀሌ እስክትደርስ ማንም እንደማይነካህ ቃሌን እሰጥሃለሁ፡፡ ወዳጄ ሻለቃ ቶልሲ ያለህን ጦር አውቃለሁ፡፡ አኔ የአንተን አስር እጥፍ ጦር አለኝ፡፡ በኋላ በወታደሮቼ ብትገደል ልቤ ያዝናልና እባክህ አምባላጌን ለቀህ ውጣ፡፡” ብለው መልዕክት ላኩበት፡፡ ሻለቃ ቶልሲን ግን በጄ ሊል አልቻለም፡፡ ከዚያ ራስ መኮንን ድጋሚ እንዲህ ብለው መልዕክት ላኩበት “ ነገ ማለዳ ጦሬ ይዘምትብሀል፡፡ አሁን ደግሜ ልለምንህ፤ ጦርህን ይዘህ ሂድ፡፡ ልቤን እንዳታሳዝነው፡፡” አሁንም ቶልሲ እምቢ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የራስ መኮንን ጦር የቶልሲን ጦር እየተከታተለ ጨረሰው፡፡ ከውጊያው በኋላ ራስ መኮንን የሻለቃ ቶልሲን አስክሬን አስፈልገው አይናችው እንባ እያቃረ በክብር እንዲቀበር አደረጉት፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ነበሩ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ረጅም የህዝብና የመንግስት ታሪክን›› አይተናል፡፡
‹‹የሀበሻ ጀብዱን›› ገልጥ ገለጥ አድርገናል፡፡
በ‹‹ አፄ ምኒልክ እና የአድዋ ድል›› ውስጥ ተመላልሰንበታል፡፡
‹‹ባለታሪክ ኢትዮጵያን›› አንብበናል፡፡
ደስም ብሎናል!!

ዘለዓለማዊ ክብር ለአድዋ ሰማዕታት!!
መማር ነኝ ከሃገረ ምኒልክ!!