ይታይሽ የኔ አለም

ይታይሽ የኔ አለም…
በድሀ አንደበቴ አፈቅርሻለሁ ስል
ይታይሽ አለሜ….
በድሀ ትክሻ
ፍቅርን ያህል ነገር ተሸክሜ ስዉል
ልብ አርጊዉ እንግዲህ…
የድሀ አንደበቱ ጉልድፍ ተብታባ ነዉ
አፈቀርኩኝ ሲል ነዉ የተባዉ የሰላዉ
ልብ አርጊዉ እንግዲህ…
የድሀ ትክሻ ቀጭን ጎባጣ ነዉ
ፍቅርን ሲሸከም ነዉ ወፍሮ የቀናዉ
ተመልከች እንግዲህ…
የድህነት ባህር ጥልቀት ባይለካም
ልብ አርጊዉ እንግዲህ ይታይሽ የኔ አለም
ከፍቅር ጋር ሲኮን…
መስመጥ አያሰጋም መሞት አያስፈራም
አይገርምሽም ታድያ…
ይሄ ከንቱ ሁላ…
የፍቅርን ሚዛን የማያዉቅ ነሁላላ
ያለልኩ ሂዶ…
ያላቅሙ አፈቀረ እያለ እሚያወራ
ያዉም ፍቅርን ሳያዉቅ ያዉም ሳይጠራ
የልቡን ዉብ መሻት የህይወቱን ዜማ
ከድህነት በርኖስ ከችግር አዉድማ
በመንፈስ ተነጥቆ በነብሱ ሳይሰማ
እያያት መሻቱን ፊት ለፊቱ ቁማ
መደብ ይሉት ግድብ ብሄር ይሉት ባህር
የፍቅር እርግቡን እንዳትበር የሚያስር
ታካች በበዛበት
ሰነፍ በሞላበት እንቅልፍ በወረሰዉ
በዚህ ሁሉ ድብርት በዚህ ቅዠት ማሀል
ይሰማሽ የኔ አለም…
በድሀ አንደበቴ አፈቅርሻለሁ ስል
የመደብ ግድቡን በፍቅርሽ አልፌ
የብሄር ባህሩን በሳቅሽ ቀዝፌ
ፍቅርን ብቻ ብየ ፍቅርሽን አግዝፌ
ከኔ ልመሳሰል ካንች ልቀላቀል
ይሰማሽ የኔ አለም…
በድሀ አንደበቴ አፈቅርሻለሁ ስል


(በሰለሞን ሳህሌ)