Keep reading books, but remember that a book is only a book, and you should learn to think for yourself. –Maxim Gorky
ከተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)
አንዳርጋቸው ፅጌን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት የ2014 የፋሲካ በአል በዋለ ማግስት ነበር። ወደ ለንደን
መንገድ ስለነበረው ከተከዜ በረሃ ወደ አስመራ መጥቶ ሳለ ደወለልኝና ተገናኘን። ሳገኘው ታሞ ነበር። ከምግብ
ወይም ከውሃ ጋር የተያያዘ ቀላል ህመም እንደሆነ ነገረኝና ወደ ፋርማሲ ሄደን መድሃኒት ገዛን።
እየደወልኩ ስለ ጤንነቱ ስጠይቀው ቆየሁ። በሶስተኛው ቀን ተሲያት ላይ ይመስለኛል ወደ ቤቱ ብቅ
አልኩ። የግቢውን በር ገፍቼ ስገባ አንዳርጋቸው በሁለት እጆቹ ልሙጥ የባህር ድንጋዮችን ተሸክሞ ቁጭ ብድግ
እያለ ስፖርት ሲሰራ አገኘሁት። ማጅር ግንዱ በላብ ርሶአል። ግቢው ውስጥ ካለችው የብርቱካን ዛፍ ላይ
ያንጠለጠለውን ፎጣ አንስቶ ላቦቱን ማደራረቅ ያዘ።
በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ጥቂት ካወጋን በሁዋላ ለመሄድ ተነሳሁ። በዚህ ጊዜ ከሶስት ቀናት በሁዋላ ወደ
ለንደን ለመሄድ ትኬቱን እንደቆረጠ ገልፆልኝ በነጋታው ምሽት የራት ቆይታ እንድናደርግ ጠየቀኝ። ሁለታችንም
በጋራ የምናውቀውን ሰው ስም ጠቅሶም በራት ቆይታው ላይ እንደሚገኝ ጠቆመኝ። ተስማማሁና ቀጠሮ ያዝን።
በነጋታው በቀጠሮአችን መሰረት ተገናኘን። ምንም ልዩ ርእሰ ጉዳይ አልነበረንም። ስለ አካባቢያችን
ፖለቲካ ተጨዋወትን። ስለ ግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል አንስቶም ጥቂት ነገረን። በሰው ሃይልና በአንዳንድ አስፈላጊ
ተሽከርካሪዎች በመጠናከር ላይ መሆናቸውን፣ ወያኔ ያዳከመውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመመለስ የሚሰራው
የፖለቲካ ስራ ራሱን የቻለ ጊዜ የሚወስድ ስራ እንደሆነ፣ በጥቅሉ ግን ትግሉ ተስፋ እንዳለው ነበር ያጫወተን።
ሞራሉ ጥሩ ነበር። ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ አላየሁበትም።
ራት እስኪቀርብ፣ “የጀሚላ እናት” በሚል ርእስ ካዘጋጀሁት (በወቅቱ ካልታተመ) መፅሃፍ አንድ ትረካ
አነበብኩላቸው። “የአዲሳባ ቀብር” የሚል ነበር። ትረካው ኮሜዲ አይነት ስለነበር እየሳቁ ነበር ያዳመጡኝ።
ከእኩለ ሌሊት በፊት መለያየታችን ትዝ ይለኛል። አንዳርጋቸው መኪና ስላልያዘ ቤቱ አድርሼው፣ “መልካም
መንገድ” ተመኝቼ ተሰናበትኩት።
ያቺ ምሽት ከአንዳርጋቸው ጋር የመጨረሻ የምተያይባት እለት ትሆናለች ብዬ ግን እንዴት ማሰብ ይቻላል?
አሁንም ቢሆን ለዘልአለሙ አንተያይም ብዬ አልደመደምኩም። ሌላው ቀርቶ ይህች መጣጥፍ እንኳ ካለበት ጉረኖ
ደርሳ ሊያነባት እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ስለነገ ማንም አያውቅም። መለስ ዜናዊ ከግርማ ወልደጊዮርጊስ ቀድሞ ይሞታል ብሎ ሊያስብና ሊገምት
የሚችል ማንም አልነበረም። ደካማና በቀላሉ ተሰባሪ የሆነች ነፍሳችን ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ምን ሊገጥማት
እንደሚችል እንኳ አናውቅም። ተስፋ ግን በልባችን ሞልቶ ተርፎአል። ስለዚህም ሰዎች በተስፋ ይኖራሉ። ሰዎች
በተስፋ አሻግረው ያልማሉ። ሰዎች በተስፋ እርቀው ይጓዛሉ…
ደጋግሜ እንደገለፅኩት አንዳርጋቸው ከነሙሉ ችግሮቹ ብርቱ ሰው ነበር። አንዳርጋቸው አደጋ ላይ
በመውደቁ ኢትዮጵያውያን “የአንድነት ሃይል” ፖለቲከኞች ትልቅ ሰው ጎድሎባቸዋል። ርግጥ ነው፣ ከአንዳርጋቸውጋር ስናወጋ የኦሮሞ ጉዳይ ከተነሳ ተግባብተን አናውቅም። አንዳርጋቸው በያዘው የፖለቲካ አቋም ከሰፊው የኦሮሞ
ህዝብ ደጋፊ ሊያገኝ እንደማይችል መናገሬም አልቀረ። በተለያዩ ፅሁፎች የማንፀባርቀውን አቋም አነሳ ነበር። አንድ
ጊዜ በወግ መሃል፣
“የታሪክ እስረኛ ላለመሆን ምኒልክ የኦሮሞ ህዝብ ላይ ለፈፀመው ግፍ ይቅርታ ጠይቃችሁ አጀንዳውን
ለመዝጋት ለምን አትሞክሩም?” ብዬ ጠይቄው በአነጋገሬ በጣም መቆጣቱን አስታውሳለሁ።
አንዳርጋቸው ለአማራ ብቻ ሳይሆን፣ ለትግራዩም፣ ለኦሮሞውም በአጠቃላይ ለመላ ኢትዮጵያውያን
የሚጠቅም የፖለቲካ መስመር ተከትያለሁ ብሎ በጥብቅ ያምናል። ለነገሩ ወያኔም እንዲሁ ይላል። ኢህአፓም
ይህንኑ ይላል። ሞአ-አንበሳ እንኳ በአቅሟ የዘውድ መመለስ ለኢትዮጵያ አንድነት ፍቱን መፍትሄ መሆኑን
ትሰብካለች። ፈላስፋው ዘርአያእቆብ እንደጠየቀን ‘ሁሉም የኔ መስመር ትክክል ነው’ የሚል ከሆነ ‘በዚህ መካከል
ማነው ፈራጅ?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ምላሹ ቀላል ነበር። ፈራጅ ሊሆን የሚችለው ህዝብ ነው። የምንመፃደቅበት
ህዝብ ግን የሚሻለውን የመምረጥ እድል አላገኘም…
ሌላ ቀን ደግሞ እንዲሁ ከአንዳርጋቸው ጋር ስንጨዋወት እንዲህ አለኝ፣
“የወያኔ መውደቅ የማይቀር ነው። ከወያኔ መውደቅ በሁዋላ በአገሪቱ ሊፈጠር የሚችለው ክፍተትና
መለያየት ግን በጣም ያሳስበኛል። ከባድ ፈተና ከፊታችን ተደቅኖአል። ለብሄርና ለቋንቋ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ
መስጠት ይጠበቃል። ከፊታችን የተደቀኑትን ቋጥኝ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያበቃ በቂ ዝግጅት አለን ለማለት ግን
እቸገራለሁ። ችግሩ ምን መሰለህ? መሬት ላይ የሚሰራው ስራ ከፕሮፓጋንዳው ጋር አልተመጣጠነም።
ፕሮፓጋንዳው መቅደሙ አደገኛ ነው።”
አንዳርጋቸው ይህን መሰረታዊ ችግር የሚዳስስና መፍትሄ የሚያስቀምጥ አዲስ መፅሃፍ በመፃፍ ላይ ነበር።
የመፅሃፉን ርእስ “ነፃነትን የማያውቅ ነፃአውጪ – ክፍል ሁለት” እንዳለውም ነግሮኝ ነበር። የመጀመሪያው “ክፍል
አንድ” መፅሃፍ፣ የአርትኦት ስራ ያስፈልገው ስለነበር፣ በአጫጭር አረፍተነገሮችና በቀላል አማርኛ እንድነካካው
ጠይቆኝ በትርፍ ጊዜዬ እያገዝኩት ነበር። ሁለቱንም መፃህፍት አንድ ላይ የማሳተም አሳብ ነበረው።
ወያኔ አንዳርጋቸውን የመን ላይ አሸምቀው እንደያዙት የሰማሁ ቀን በድንጋጤ ደንዝዤ ነበር። ማመን
አቃተኝ። አንዳርጋቸው ከአራት አመታት በላይ ወደ ኤርትራ ሲመላለስ የሱዳንና የየመንን አየር መንገዶች ተጠቅሞ
እንደማያውቅ አውቃለሁ። እኔ አልፎ አልፎ የየመንን መንገድ እንደምጠቀም ስለሚያውቅ፣ “ተው፣ አትመናቸው”
ብሎ ጭምር መክሮኛል። የመን ላይ ‘መንግስት አለ’ ለማለት እንደማይቻል አንዳርጋቸው እያወቀ ምን ሊሆን የመን
ሄደ? ያልተመለሰ ጥያቄ ሆነብኝ።
ዜናውን ስሰማ የተደበላለቀ አሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ። ሊሆን የማይችል ጥርጣሬ ነገሮች ጭምር
ረበሹኝ። ዜናውን በሰማሁበት ደቂቃ ስንቱን አወጣሁ፤ ስንቱን አወረድኩ። ማን ዘንድ ደውዬ ማንን እንደምጠይቅ
ግራ ገባኝ። በመጨረሻ ወደ አንዳርጋቸው ዘመዶች እየበረርኩ ሄድኩ።
አስመራ ላይ አንዳርጋቸው “ዘመዶች” አሉት። የስጋ ዘመዶቹ አይደሉም። አዲስአበባ ጎረቤቶቹ የነበሩ
ናቸው። ነገሩ እንኳ ከጉርብትና በላይ ነው። አንዳርጋቸው ወጣት የኢህአፓ አባል ሆኖ ሲንቀሳቀስ የደርግ አፋኞች
ሊገድሉት ያሳድዱት ነበር። ወንድሙንና አንድ ኤርትራዊ ጓደኛውን ጎዳና ላይ ሲረሽኑበት አንዳርጋቸው የሚገባበት
ቀዳዳ አልነበረውም። በዚህ ችግር መሃል፣ የእናቱ ጓደኛ የነበረች አንዲት ኤርትራዊት ሴት አንዳርጋቸውን ወደ
አስመራ በመውሰድ ከመኖሪያ ቤቷ ሸሸገችው። ስድስት ወራት ከቤት ሳይወጣ ከቆየ በሁዋላ ያቺ ሴት የሃሰት
መታወቂያ አውጥታለት፣ ትንሹን አንዳርጋቸው እንደ ገበሬ አልብሳ ወደ ገጠር በመውሰድ ለሻእቢያ አስረከበችው።
ሻእቢያ አንዳርጋቸውን በሱዳን በኩል ሸኘው። ከዚያም አንዳርጋቸው ወደ ለንደን አቀና። አንዳርጋቸው መፅሃፉን
ሲፅፍ የመፅሃፉን መታሰቢያ ከሰጣቸው መካከል ጓደኛው የነበረ የእነዚሁ የኤርትራውያኑ ልጅ የነበረ ነው። ይህን
የተከበረ ቤተሰብ አንዳርጋቸው ወስዶ አስተዋውቆኝ ነበር። ስድስት ወራት የተደበቀባትን ክፍል ጭምር
አይቻለሁ። አንዳርጋቸው ይህን ቤተሰብ እንደ ስጋ ዘመዱ ያያል። እነርሱም አንዳርጋቸውን ሲያዩ በደርግ የተረሸነ
ሟች ወንድማቸውን ያስታውሳሉ።
እንግዲህ አንዳርጋቸው የመን ላይ መያዙን ስሰማ ወደ እነዚህ ሰዎች ነበር የበረርኩት። እንደደረስኩ
የግቢውን በር ደበደብኩ። አንዲት ሴት ብቅ አለች። አላውቃትም። እንግዳ ሳትሆን አትቀርም። ማንን እንደምፈልግ
ነገርኳት። የፈለግሁዋት ሴት እንደሌለች ነገረችኝ። እና የእጅ ስልኳን ሰጠችኝ። ደወልኩ። የምፈልጋት ሴት ስልኩን
አነሳች። ማን እንደሆንኩ ከነገርኳት በሁዋላ፣
“ስለ አንዳርጋቸው ሰማሽ?” ስል ጮህኩ።
“አልሰማሁም። ምን ሆነ?” ስትል እሷም ጮኸች።
“አሁኑኑ ነይ። እነግርሻለሁ…”
ከአስር ደቂቃ በሁዋላ እዚያው ከቤታቸው በራፍ ላይ ቁጭ ብለን የሰማሁትን ሁሉ ነገርኳት። ቃል
መተንፈስ እንኳ ተቸገረች። ትንፋሿ ቆሞ ድርቅ ብላ ቆየች። በመጨረሻ ግን ጥቂት ጥያቄ አዘል ቃላት ተናገረች፣
“በየመን በኩል ለምን እንደመጣ አልገባኝም? በየመንያ እንደማይጠቀም ከዚህ በፊት ነግሮኝ ነበር?”
በመቀጠል ከአንዳርጋቸው “ዘመዶች” ወደሌላው ደወልኩ። ተገናኝተን ስናወጋ ዜናውን ሰምቶ ነበር
የጠበቀኝ። ግራ ተጋብቶ ነበር። ግራ በተጋባ ስሜትም፣
“አንዳርጋቸው ከለንደን ሲነሳ ደውሎልኝ ነበር።” አለኝ። አያያዘና አከለበት፣ “…ትኬቱ በኤርትራ አየር
መንገድ ከዱባይ በቀጥታ ወደ አስመራ የተቆረጠ ነበር። ለምን በየመን በኩል እንደቀየረው አልገባኝም?”
አንዳርጋቸው ከየመን ወደ አዲሳባ መዛወሩን እስከሰማሁባት እለት የነበሩት ቀናት ለኔ እጅግ አስጨናቂ
ነበሩ። ወሬው አስመራን አዳርሶ ነበር። ፖለቲካ የማይከታተሉ ሰዎች ሳይቀሩ የአንዳርጋቸውን ስም እያነሱ ሲነጋገሩ
ሰማሁ። የኔና የአንዳርጋቸውን መቀራረብ የሚያውቁ እየደወሉ ይጠይቁኝ ነበር። አንዳርጋቸውን በፖለቲካ አቋሙ
የሚቃወሙት የኦነግ ከፍተኛ አመራር አባላት ጭምር በየመን ድርጊት ክፉኛ ተቆጥተው ነበር። የኦነግ አመራር
ከመቆጣት አልፎ የመን ላይ ዛቻ የቀላለቀለ መግለጫ አወጣ። ዳሩ ግን ማንም ምንም ማድረግ በማይችልበት
ፍጥነት አንዳርጋቸው ተላልፎ ለወያኔ ተሰጥቶ ኖሮአል። ኦሮማይ!
አንዳርጋቸው እንዴት ከወያኔ እጅ ሊገባ እንደቻለ ዛሬም ድረስ ግልፅ መረጃ የለም። የተለያዩ መላ
ምቶችን እየሰማን፣ እያነበብን ቆይተናል። አንዳርጋቸውን በቅርብ ከሚያውቁት አንዱ እንደመሆኔ እኔም ካለኝ
መረጃ በመነሳት የራሴን ግምት መውሰዴ አልቀረም። የኔን ግምት ይፋ ከማድረጌ በፊት ሌሎች የሚሉትን
ለመስማት በሚል እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ሳልፅፍ ቆይቼ ነበር። አሳማኝ መረጃ ሳይፃፍ ወይም ሳይገለፅ ጊዜው
ስለረዘመ እነሆ! እኔም የግል አስተያየቴን ለማኖር ወሰንኩ…
ኤልያስ ክፍሌ ethiopianreview ላይ የፃፈውን አንብቤያለሁ። ግንቦት 7 የኤልያስን መረጃና ትንታኔ
በደፈናው፣ “ውሸት” ሲል ማስተባበሉንም ተከታትያለሁ። ግንቦት 7 ከማስተባበል አልፎ አንዳርጋቸው እንዴት
ሊያዝ እንደበቃ መግለፅ አለመቻሉ ግን ማስተባበሉን ጎደሎ ያደርገዋል። ያም ሆኖ የኤልያስ ክፍሌ ዘገባ ለኔ
አሳማኝ አልነበረም። በተመሳሳይ ከአንዳርጋቸው መያዝ ጋር በተያያዘ ጥቂት ወሬዎችን ተከታትያለሁ።
ከሰማሁዋቸው መካከል፣
“አንዳርጋቸው ከዱባይ አስመራ በቀጥታ የሚወስደው የኤርትራ አየር መንገድ ትኬት ነበረው። ዱባይ
ላይ የኤርትራ አይሮፕላን ስላመለጠችው የየመንን ትኬት ገዛ።” የሚለው አንዱ ነው።
ለዚህ መረጃ ክብደት ልሰጠው አልቻልኩም። አንዳርጋቸው ተጨማሪ አንድ ቀን ዱባይ በማደር
የሚቀጥለውን የኤርትራ አይሮፕላን መጠቀም እየቻለ፣ እንዴት አስተማማኝ እንዳልሆነ በሚያውቀው የመኒያ
ለመጓዝ ይወስናል? አንዳርጋቸው በየመን አየር መንገድ የተጓዘው በግማሽ ቀን ውስጥ በራሱ ውሳኔ ብቻ ከሆነ፣
የወያኔና የየመን የፀጥታ ሰዎች በዚያችው ቅፅበት አንዳርጋቸውን ለማፈን መቀናጀት ችለዋል ብሎ ማመን
ይቸግራል። የመሆን እድሉ በጣም አናሳ ነው። ለንደንም ሆነ አስመራ የሚገኙ የአንዳርጋቸው ዘመዶች የማያውቁት
አንድ ጉዳይ ያለ ይመስላል። በርግጥም አንድ ምስጢር ሊኖር እንደሚችል እጠረጥራለሁ።
ነገሩ ወዲህ ነው…
በአንድ ወቅት ግንቦት 7 ከነ ነአምን ዘለቀ እና ከአንድ የሆነ የአፋር ድርጅት ጋር ውህደት ነገር
መፈፀማቸውን በዜና ነግረውን ነበር። ከውህደቱ በሁዋላ ብዙም የተወራ ነገር ሳይኖር ነገሩ ተድበሰበሰ። ነአምን
ዘለቀ ከግንቦት 7 ጋር አብሮ ሲሰራ ስመለከት ግን አፋሮቹም ሆነ እነ ነአምን ጠቅልለው ግንቦት 7 ውስጥ ገብተዋል
የሚል ግምት ወስጄ ነበር። የአንዳርጋቸው የመያዝ ሂደት ከዚያ ሳይጀምር አልቀረም።
አንዳርጋቸው ከአፋሮቹ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነቱን አጥብቆ ቀጥሎ እንደነበር አውቃለሁ። ምን
እንደሚሰራ ግን ፈፅሞ ነግሮኝ አያውቅም። በመካከሉ ሆላንድ ሳለሁ ከግንቦት 7 ሰዎች በኩል የሾለከ የሚመስል
ወሬ ሰማሁ። ይህም ወሬ ለስራ ተብሎ 30 ሺህ ዶላር ተሰጥቶት ወደ የመን የተላከ አንድ አፋር የመሰወሩ ወሬ
ነበር። ወሬው በሰፊው የተሰራጨ አልነበረም። እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ ቀዳዳ ነበር የሰማሁት። ይህ ወሬ
ሲመዘን ተራ ወሬ ሊመስል ይችላል። አፋሩ ገንዘብ መያዙ በርግጥ መረጃውን ከፍ አድርጎታል። ከገንዘቡ በላይ ግን
“የመን” የሚለው መረጃ ክብደት ነበረው። ግንቦት 7 የመን ላይ ትኩረት ማድረጉ ትልቅ መረጃ ነበር። አፋሩ
የመን-ሰንአ ሲደርስ ተሰወረ። ከዳ ወይስ ተያዘ? አይታወቅም። ከድቶም ሆነ ተይዞ ወያኔ እጅ ገብቶ ሊሆን
እንደሚችል ግን መገመት ይቻል ነበር። ይህ ከሆነ የግንቦት 7ን የተደበቀ ፍላጎት ወያኔ አውቆአል ማለት ነው።
ግንቦት 7 ምን እንደሚፈልግ ወያኔ ካወቀ፤ የግንቦት 7ን ፍላጎት ለማጥመጃ ሊጠቀምበት ይችላል። ቀላል
ጉዳይ አይደለም። ግንቦት 7 የመን ላይ ምንድነው የፈለገው? ከስደተኞች መካከል ታጋዮችን መመልመል?
የተመለመሉትን ደግሞ ወደ ተከዜ በረሃ ማሻገር? ይህን ስራ ለማከናወን ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። ውድ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን ይህን ስራ ለመስራት የሚችል፣ አላማ ያለው ብቁ ሰው የመን ላይ ማግኘትን ይጠይቃል።
አፋሩ ገንዘብ ይዞ የመን ላይ ከተሰወረ በሁዋላ አንዳርጋቸው ተስፋ ቆርጦ ጉዳዩን ይተወዋል ተብሎ
አይገመትም። እንደገና ይሞክራል። ወያኔዎች በዚህ በአንዳርጋቸው ዳግማዊ ሙከራ ጊዜ የራሳቸውን ሰው የመን
ላይ አስቀምጠው አንዳርጋቸውን እንዲገናኘው አድርገው ይሆን? አንዳርጋቸው በረጅም ሂደት ወያኔዎች
ያዘጋጁለትን ሰው እንደራሱ ሰው በማመን ለግንቦት 7 አባልነት በምስጢር መልምሎት ይሆን? እና በረጅም ጊዜ
ሂደት አንዳርጋቸው ወያኔዎች ባዘጋጁለት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶላቸው ይሆን? ማለትም አንዳርጋቸው
እነዚያ አባላቱን ለማነጋገር፣ አሊያም ታጋዮቹን ወደ ተከዜ ለማሸጋገር እንዲቻል አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፈፀም
በምስጢር የመን ገብቶ ለመውጣት ሞክሮ ይሆን?
ጥያቄዎቹ “አንዳርጋቸው እንዴት ተያዘ?” ለሚለው ጥያቄ ፍንጭ ሰጪ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀጥተኛ መረጃ
ያለው አካል የተፈፀመውን በዝርዝር እስካልነገረን ድረስ ከምናውቀው በመነሳት ለመገመት እንገደዳለን።
ከዚህ ሁሉ በሁዋላ፣ “ወያኔዎች አንዳርጋቸውን ይዘው በማሰራቸው አተረፉ ወይስ ከሰሩ?” የሚል ጥያቄ
ይነሳል። የወያኔ ሰዎች “አተረፍን” እያሉ ነው። ማትረፍና መክሰራቸውን ለማየት በርግጥ ጥቂት ጊዜ መጠበቅ
ያስፈልግ ይሆናል። “አትርፈናል” ባዮች ከበሮ ሲደልቁ ሰምተናል። በአንዳርጋቸው መያዝ ቆሽቱ የደበነ ወገን፣ ነገ
በቁጣ ምን ሊፈፅም እንደሚችል አለመገመት የፖለቲካ የዋህነት ነው። እነ በቀለ ገርባ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ
ኦልባና ሌሊሳ፣ እነ ኢንጂነር መስፍን አበበ (ራሶ)፣ እነ ጫልቱ ታከለ፣ እነ ኢብራሂም ሱልጣን፣ እነ ሰይድ አሊ፣ እነ
ፊፈን ጫላ፣ እነ ኮሎኔል ኦላኒ ጃሉ፣ እነ ውብሸት ታዬ፣ ዛሬም ድረስ እስርቤት ናቸው። አንዳርጋቸው ፅጌ
ተጨምሮአል። ይህን ፅሁፍ እየጻፍኩ ሳለም በርካታ ነፃነት ጠያቂዎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት በመጓዝ ላይ ነበሩ።
እስርቤት የተወረወሩትን ዜጎች በቀን 24 ሰአት የሚያስታውስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ በመላ ኢትዮጵያ አለ።
በደል ሲበዛ ወደ በቀል ይለወጣል። ብዙውን ጊዜ ተበዳዮች ጉልበት ሲያገኙ የማመዛዘን ችሎታቸውን
ያጣሉ። በቀል ከመጣ ከደሙ ንፁህ የሆነውን ከተጠቃሚው መለየት ሳይቻል ጊሎቲኑ ከፊቱ ያገኘውን ሊበላ
እንደሚችል ከታሪክ በተደጋጋሚ አይተናል። ወያኔ አንዳርጋቸውና መስፍን አበበን በመሳሰሉ ታጋዮች ላይ
እየፈፀመ ባለው የማፈን ድርጊት ከህዝቡ መራር ቂም በማትረፍ ላይ ነው። ጭፍን ደጋፊዎቹ አደጋ ላይ
እንዲወድቁም አጋልጦ እየሰጣቸው ነው። በመሆኑም ወያኔ አትራፊ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አይችልም።
የፅጌ ልጅ – አንዳርጋቸው ከጠላቶቹ እጅ ላይ ወድቆአል። በወያኔ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦም ጥቂት ቃላትን
ተናግሮአል። አንዳርጋቸው በጨካኝ ጠላቶቹ እጅ ላይ ወድቆ ሳለ የተናገራቸውን ቃላት በቀጥታ መውሰድ ወይም
ንግግሩን እንደ መረጃ ተጠቅሞ በዚያ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አለመሆኑን እረዳለሁ። ያም ሆኖ
አንዳርጋቸው በንግግሩ፣ “እኔን ተክቶ በረሃ የሚወርድ ሰው ማግኘት ይቸግር ይሆናል” አይነት አባባል መጠቀሙ
በተዘዋዋሪ የትግል ጥሪ ይመስለኛል። መስማት የሚፈልግ ካለ ይህን ሊሰማ ይችላል…
ርግጥ ነው አንዳርጋቸው ከተያዘ በሁዋላ በመላ አለም የሚገኙ “የአንድነት ሃይሎች” በቁጣ የተቃውሞ
ሰልፎችን አካሂደዋል። “አንዳርጋቸው ነኝ!” የሚል መፈክር ይዘውም ታይተዋል። “ሁላችንም አንዳርጋቸው ነን!”
የሚለው መፈክር ለአንዳርጋቸው ተገልብጦ ስድብ እንዳይሆንበት ግን እሰጋለሁ። “አንዳርጋቸው ነኝ!” ለማለት
ቢያንስ አንዳርጋቸው የሞከረውን ለመሞከር ቁርጠኛነትን ማሳየት ይጠይቃል። “ሁላችንም አንዳርጋቸው ነን!”
የሚለው አባባል በአፍ ብቻ ተንጠልጥሎ ከቀረ፣ እንደተለመደው የአንድ ሰሞን የዳያስፖራ ጫጫታ ሆኖ እንደ
ቀዳሚዎቹ መፈክሮች ይህም ከተረሳ ለአንዳርጋቸው ስድብ እንጂ ክብር ሊሆነው አይችልም።
የቅዳሜ ማስታወሻ – December 12, 2014 – Tesfaye Gebreab (Gadaa) – Email: ttgebreab@gmail.com