የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ያዕ1፡2

ማኅበረ ቅዱሳን

image

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተዋጀችውና የተመሠረተችው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ፣ ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ ነው፡፡ ሐዋ.2ዐ፥28፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልጽም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ብሏል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ ሲዋጅ ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስን ድል ነስቶ፣ ምርኮውን መልሶ፣ ሞትን ደመስሶ በመሆኑ ዲያቢሎስ የድል ነሺውን ቤተ ክርስቲያንና ወደ ነጻነት የተመለሱትን ክርስቲያኖች ዘወትር ይፈትናቸዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው እግዚአብሔር ኃላፊያቱንና መጻእያቱን በገለጸለት ራዕይ ስለ ዲያቢሎስ ፈተና ሲጠቁም “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ ….ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና። ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።” ዮሐ. ራዕ. 12፥9-17፡፡

ታሪክና መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ጌታን የሰቀሉ አይሁድ ደቀመዛሙርቱን በእርሱ ስም እንዳያስተምሩ ለማድረግ በማስፈራራት ብዙ ጥረዋል፤ አስረዋቸዋል፣ ገርፈዋቸዋል፣ አሳደዋቸዋል፣ ገድለዋቸዋል፡፡ ሐዋ.ሥ 4፥17-21 ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በአለት ላይ የተመሠረተችና በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ስለሆነ ሥራዋ አልተቋረጠም፤ ተከታዮቿም አልጠፉም ዕለት ዕለት ይበዛሉ እንጂ፡፡ ማቴ. 16፥18

ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት፣ በዘመነ ሰማእታትና በዘመነ ሊቃውንት እንደጊዜው የተለያየ መከራና ፈተና አሳልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ጥንት በአይሁድ፣ በሮማዊያን ነገሥታት፣ በአህዛብ እያደረ፤ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው በመጽናታቸውና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገላቸው ሰውነታቸው በሰም ተነክሮ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ በቁርበት ተጠቅልለው ለአንበሳ እንዲሰጡ፣ በድንጋይ ተወግረው እንዲሞቱ፣ በስለት እንዲቀረደዱ፣ በሰይፍ እንዲቀሉ ያስደርግ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችም በእምነታቸው እየጸኑ ከሞት የተረፉት፤ በዋሻ በግበበ ምድር እየሆኑ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ጌታ “የሲዖል ደጆች አያናውጧትም” ያላት ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ዳርቻ እየሰፋች የመሰረታትን ጌታ እያመሰገነች ትኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ለማሳካትና የዲያቢሎስን ሽንገላ ለመቋቋም በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች ልጆቿን ታሰማራለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ሰጥታ ልጆቿን ለአገልግሎት ካሰማራችባቸው መንገዶች አንዱ የማኅበራት አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ የማኅበራት አገልግሎት የዲያቢሎስን ፈተናና ሽንገላ ተቋቁመው በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን እያበረከቱ ከሚገኙ ማኅበራት መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከ22 ዓመታት በፊት ቅርጽ ይዞ የተዋቀረና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎቱን የሚፈጽምበት ደንብና ሥርዓት የተበጀለት ማኅበር ነው፡፡ አባላቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የሆኑና በየአጥቢያቸው የልጅነት ግዴታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ሲሆኑ በቅናተ ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው ለቤተ ክርስቲያን እድገት የሚያግዙ የትሩፋት ሥራዎችን የሚሠሩ ናቸው፡፡

ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተለይቶ በተሰጠው ተግባር መሰረት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችን በየአጥቢያቸው አሰባስቦ፤ ከየሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ጋር በመተባበር ትምህርተ ሃይማኖትን የሚያስተምር፣ አባላቱንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ስብከተ ወንጌል በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም እንዲስፋፋ የሚያደርግ፣ አድባራትና ገዳማት በልማት ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደረግ፣ የቤ ተክርስቲያናችን ሀብት የሆነው የአብነት ትምህርት እንዲጠናከርና ሊቃውንቱም ወንበራቸውን እንዳያጥፉ በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ይህ መንፈሳዊ ተግባር በቤተ ክርስቲያን በመተግበሩ፤ ቤተ ክርቲያንን የማይወዱና ውድቀቷን እንጂ ጥንካሬዋን የማይሹ አካላት የማኅበሩን አገልግሎት አልወደዱትም፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ማኅበረ ቅዱሳንን ጠልፎ መጣል እንደ ዋነኛ ስልት አድርገው ቆርጠው መሥራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነዚህ አካላት ለዓላማቸው የሚጠቅም ሆኖ እስካገኙት ድረስ ማንኛውንም ነገር ይጠቀማሉ፡፡ በተለያየ ደረጃ ያሉ ሰዎችን በማሳሳት፣አሉባልታ በመንዛት፣የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጭምር በማሳሳት የሚፈልጉትን ተግባር ለመፈጸምና ለማስፈጸም ይተጋሉ፡፡ ማሩን በማምረር ወተቱን በማጥቆር- ደጋግመው እየወተወቱ ብዙ የዋሐንን የነርሱን የማደናቀፍ ተግባር ተባባሪ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡

በጎ ነገር ሲሠራ በጠላት ዲያብሎስ በኩል እንቅፋት እንደሚቀመጥ ሁልጊዜ የታወቀ ነው፡፡ ፈተናውን ማለፍ መሰናክሉን መቋቋም ግን የአንድ ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም እንደነዚህ ዓይነት ፈተናዎች ከቀድሞ ጀምሮ ሲያጋጥሙት ቢቆይም በአገልግሎቱ ምክንያት የመጡ መሆናቸውን በመገንዘብ በአባቶች ጸሎት፣ በእግዚአብሔር ኃይል አሸንፎ ላለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ ወደፊትም በእግዚአብሔር ፈቃድ ይቀጥላል፡፡

ከላይ በጠቀስናቸው አካላት አማካኝነት አንዳንድ ወገኖቻችን ስለማኅበሩ የተሳሳተ መረጃ ሲደርሳቸው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ መስሏቸው አገልግሎቱን የሚያደነቅፉና ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ የሚፈርጁትን አካላት ወግነው ሲቆሙ ይታያሉ፡፡ እነዚህ አካላት ትክክለኛውን መረጃ ቢያገኙ፣ ቢያውቁና ቢገነዘቡ ከማኅበሩ ጋር የዓላማ ልዩነት ስለሌላቸው፤ አብሮ በፍቅር ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ምንም የሚቸግራቸው ነገር የለም ብለን እናምናለን፡፡ ወደፊትም ከማኅበሩ ጋር አብረው ሊሠሩ የሚችሉ፣ የሚመክሩና የሚያስተካክሉ እንደሆኑ ማኅበሩ ያምናል፡፡ ካሁን ቀደምም እንዲህ ዓይኖቶቹን አካላት ባገኘ ጊዜ ሁሉ ማኅበሩ በማወያየቱና በማስረዳቱ የማኅበሩን አገልግሎት እየደገፉ የሚገኙ በርካታ ናቸው፡፡

ቤተ ከርስቲያንን በዓላማ የሚጠሉ ግን የማኅበሩን አገልግሎት ቢያውቁና ቢረዱትም የዓላማ ልዩነት ስላላቸው መቼም አገልግሎቱን በቀና አያዩትም፡፡ ዕለት ዕለት ለማደናቀፍ ይጥራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ሆነው ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ጠልፈው ለመጣል የሚታገሉ፣ እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን በአፍኣ ሆነው እጃቸውን ባስረዘሙ አንዳንድ አካላት ማኅበሩ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡

ለምሳሌም ያህል በአንዳንድ ሀገረ ስብከቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት በዋናነት የሚያስተባብረውን የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዳያስተምር ሲከለክሉና ሲያቋርጡ ይታያሉ፡፡ ማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ማእከላት ቢሮዎች የሚዘጉ አንዳንድ አጥቢያዎችም ይስተዋላሉ፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ አካላትም በሕዝብ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ሳይቀር የማኅበሩን ስም እያነሱ ተገቢ ያልሆነና ማኅበሩን በፍጹም የማይገልጹ ቅጽሎችን እየሰጡ ለማስረዳት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡

እነዚህ ለማሳያነት በተጠቀሱት የማኅበሩ ተግዳሮቶች መነሻነት በአንዳንድ ግለሰቦች አማካይነት መዋቅሮችን አላግባብ በመጠቀም የግለሰቦቹን ምኞት ከግብ ለማድረስ የሚሠሩና ጥንቃቄ ያልታከለባቸው እርምጃዎች እንጂ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመንግሥት ውሳኔ ነው ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆኑ ፈተና ስለማይለየው ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች በጸሎት፣ የሚመለከታቸው አካላት በማስረዳትና በመወያየት፣ እንዲሁም በመታገስ አልፎ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ያገለግላል፡፡

ማኅበሩ ፈተና ሲያጋጥመው መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት የሚሄድባቸው መንገዶች ሁልጊዜም የታወቁ ናቸው፡፡ ችግሮች ሲመጡ ጊዜያዊና በእግዚአብሔር ኃይል በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በመረዳት በጥበብና በትዕግስት ከሚመለከከታቸው አካላት ሁሉ ጋር እየተወያየ ይፈታል፡፡ የችግር አፈታቱ ሥርዓት መንፈሳዊነትን የተከተለ በመሆኑ ሥጋዊ አስተሳሰብን ሳይጨምር ሃይማኖታዊ ፈተና ሲመጣ ማሸነፊያው ሃይማኖታዊ ኃይል ነው ብሎ ያምናል፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በጾምና በጸሎት በትዕግስትና በጽናት፤ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ነው፡፡

በማርቆስ ወንጌል ላይ እንደምናገኘው፡- (ማር. 4፡37) “ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።” ይላል፡፡ በታንኳይቱ የተመሰለችው ቤተ ክርስቲያን በፈተና ልትናወጥ ትችላለች፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ በውስጧ ያለውን፣ ነገር ግን እኛ የድርሻችንን እስክንወጣ ድረስ የሚጠብቀውንና ዝም ያለ (የተኛ) የሚመስለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፈተናን ጸጥ የሚያደርግ አምላክ እንደምናመልክ ልንዘነጋ አይገባምና ፡፡

ማኅበሩ በቤተክርስቲያንም ሆነ በማኅበራችን ዙሪያ ስላሉ ነገሮች ማንኛውንም መረጃ የሚያስተላልፈው በራሱ ሚዲያና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሥርዓት ባለው መልኩ በሚመለከታቸው የማኅበሩ ኃላፊዎች በኩል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የሚተላለፍ ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ሀሳቦችን በመያዝ ማኅበሩን በተመለከተ የግል ሀሳብንና ተግባርን ማንጸባረቅ አግባብ አለመሆኑን ሁሉም አካላት ሊያውቀው ያስፈልጋል፡፡

ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማን ግብ ያለው በመሆኑ በጊዜው በሚታዩ ጥቅመኞችና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሁከት ሳንዘናጋ የወንጌል ተልእኳችንን በጥበብና በትዕግስት ከግብ ማድረስ ይገባናል እንላላን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ያዕቆብ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ ያዕ.1፡2 እንዳለ ስለ እምነታችንና ስለቤተ ክርስተያናችን የምናደርገውን አገልግሎት ፈታኙ ዲያብሎስ ሊያደናቅፍ ሠራዊቶቹን ቢያሰማራም እግዚአብሔር አምላካችንን ትዕግስትንና ጽናትን እንዲሰጠን ፈተናውንም እንዲያሳልፍልን በጽናት እንለምነው፡፡- እርሱ በሰው ዘንድ የማይቻለውን እንድንችል ማድረግ ያውቅበታልና፡፡ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔ