Gondaronline.com

የኢትዮ ሱዳን ድንበር ከአፄ ፋሲል እስከ ኢህአዴግ

29 March 14
Biruk Sisay

የአፄ ፋሲል ታሪከ ነገስታቸው በኢትዮጵያ ምዕራብ ዛሬ የሱዳን ግዛት በሆነው አገር ስናርን እና ኑብያን እንዳስተዳደሩ ይገልፃል። በኑብያም በርሳቸው ስር የሚተዳደር ጊዮርጊስ የሚባል የአካባቢ ንጉስ አንግሰው እስከ የግብፅ ወሰን የሆነው ጠረፍ ቦታ ድረስ እንዳስተዳደሩ እና የፈረሶቻቸውም መታሰሪያ እና መቀለቢያ ስናር ነበር በማለት ያትታል። አያይዞም ከአፄ ፋሲል በፊት የነበሩት ነገስታት ኑብያንና ስናርን እየዘመቱ ካስገበሩ በኋላ መመለስ እንጂ እንደርሳቸው በስርዐት አላስተዳደሩትም ነበር ብሎ በመግለፅ በእሳቸው ጊዜ አዝማሪ እንደሚከተለው እንደዘፈነ ይጠቅሳል፦ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ
ኑብያና ስናር ወርቁን ጫኑልህ
ሣሩን ተጠየፈ የፋሲል ፈረሱ
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለእሱአፄ እያሱ (አድያም ሰገድ) ወይም ታላቁ እያሱ በአያታቸው በአፄ ፋሲል እየተዳደረ ሲገብር የነበረውን እና በመሀል ያቆመውን ከከሰላ እስከ ስናር ያለውን ወረዳ ጭፍሮቻቸውን በመላክ እንዲያቀኑት በማስደረግ እና የአካባቢው መሳፍንቶች አቋርጠውት የነበረውን ግብር እንዲከፍሉ አሳምነዋል። የአፄ እያሱ (አድያም ሰገድ) የሰሜን ምዕራብ ግዛታቸው ወሰንም ከምዕራብ እስከ ስናር ከሰሜን የከረንን የሐባብን ሀገር ሁሉ ይዞ እስከ ላይኛው የባርካ ወንዝ ድረስ ያካተተ እንደነበር ታሪከ ነገስታቸው ያትታል።የአፄ በካፋ እና የቋረኛዋ እቴጌ ምንትዋብ ልጅ የሆኑት ቋረኛ እያሱ (ብርሀን ሰገድ) ዛሬ የሱዳን ግዛት በሆነው አገር ድረስ ግዛታቸውን በማስፋፋት እና አስተዳደራቸውን በመዘርጋት ግብር እንዳስገበሩ አሁንም የእሳቸው ታሪከ ነገስት ያስረዳል። ግዛታቸውም በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ እንደወሰን የሚታየውን አትባራን አልፎ ስናር የሚባለውን ከተማ ሁሉ ያካትት ነበር። በጊዜው የስናር ባላባት የነበረው ባዲ ኢብን ሻሉክ የሚባል ሰው ሲሆን እርሱም አልፎ አልፎ ለንጉሱ አልገብርም እያለ የሚያምፅ ቢሆንም ቋረኛው ንጉስ አፄ እያሱ በተደጋጋሚ ወታደሮችን እየላከ የሚቀጣውን እየቀጣ በማሳመን እና በማስገበር አካባቢውን አስተዳድሯል። ከዚያ በኋላ ዘመነ መሳፍንት ገባ እና ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ።

በዘመነ መሳፍንት ማብቂያ ገዳማ ደግሞ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በሽፍትነት ዘመናቸው ጭፍሮቻቸውን ይዘው ሲንቀሳቀሱበት የነበረው አካባቢ አሁን በሱዳን ይዞታ ውስጥ የሚገኘው ጋላባት እና ዙሪያውን ነበር። ቴዎድሮስም የዘመነ መሳፍንት የአካባቢ ገዢዎችን ተራ በተራ በመውጋት ሁሉንም አሸንፈው ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ እንዲባሉ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከተው ከዚሁ ከጋላባት እና ቋራ አካባቢ የተውጣጣው ሠራዊታቸው ነበር። ንጉሰ ነገሥት ከተሰኙ በኋላም አካባቢው በእሳቸው ቁጥጥር የነበረ ሲሆን እንዲያስተዳድር ያደረጉትም የአካባቢው ተወላጅ የሆነውን እና የሽፍትነት ጓደኛቸው እንዲሁም የልብ ወዳጃቸውን እንድሪሥን ነበር።

ከአፄ ዮሀንስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ገዳማ ጀምሮ ኢትዮጵያን በወሠን የሚያካልሏት እንዳሁኑ ያገር ተወላጆች የሚመሯቸው መንግስታት እነ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን ሳይሆኑ እነሱን ለመቀራመት እና ቅኝ ለማድረግ በበርሊኑ ኮንፈረንስ በስምምነት የተከፋፈሏቸው አውሮፓውያን አገሮች ናቸው። እነሱም እንግሊዝ፣ ጣልያን እና ፈረንሳይ ነበሩ። አፄ ምኒልክም ከአድዋ ድል በኋላ የወሰን ክልል የተዋዋሉት ከነዚሁ መንግስታት ጋር ነበር።

የእንግሊዝ መንግስት በሱዳን በኩል ስላለው የግዛቱ ወሰን ሌተና ኮለኔል ዢሀን ሐሪንግተን በእንግሊዝ ንጉሥ በኤድዋርድ ሰባተኛ ሥም፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አፄ ምኒልክ በራሳቸው ሥም እ. ኤ. አ. ግንቦት 15ቀን 1902 በአምስት አንቀፅ የተከፈለ ውል ተዋውለዋል። ይህ የአፄ ምኒልክ ውል አሁን መንግስት እንደሚያወራው መተማን፣ ቋራን፣ ከፊል ሁመራን፣ የቤንሻንጉል ጠረፍ አካባቢዎችን የሱዳን ያደረገ አይደለም። የድንበር አወሳሰኑ በካርታ ላይ እንጂ በመሬት ላይ የተከናወነ አልነበረም። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ በመሩት በኃይለ ሥላሴ ዘመንም የተካሄደ አንድም የድንበር ስምምነት የለም።

ምንም እንኳ ሀፍረት የለሹ የዘመኑ ጠቅላይ ሚኒስተር እኛ ለሱዳን የሰጠነው አንድም አዲስ መሬት የለም ነገር ግን የድንበር ማካለል ያደረግነው በምኒልክ፣ ኃይለሥላሴ እና በሶሻሊስቱ ደርግ ዘመን በሁለቱ መንግስታት የተደረጉ ውሎችን መሰረት በማድረግ ነው፤ ቢሉም በቅርቡ ሌ/ኮ መንግስቱ ሀይለ ማርያም በራሳቸው አንደበት ከሱዳን ጋር እሳቸውም ሆኑ ከእሳቸው በፊት የነበረው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ምንም አይነት የድንበር ውል እንዳላደረገ በመመስክር ድርጊቱን ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ዘመን ጀምሮ እያካሄደ ያለውን ጥንታዊት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሌላኛው ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን የሰሜን ምዕራብ የሱዳን አዋሳኝ መሬቶችን ያስደፈረው ኢህአዴግ ነው እንላለን! ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ሱዳን ላደረገችለት እርዳታ እንደውለታ በመቁጠር እንዲሁም ወደፊት ደግሞ የትጥቅ ትግል በማድረግ ኢህአዴግን እንቀብረዋለን ለሚሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዳትሠጥ እና መመሸጊያ እና መንቀሳቀሻ ቦታወችን እንዳትፈቅድ እንደ ማባበያ ለሙን የሰሜን ምዕራብ መሬት ለግሷታል። ተራ የሥልጣን ፍላጎትን ለማርካት የአገር ሉዐላዊ ደንበርን ለድርድር በማቅረብ እና ለባዕዳን አሳልፎ በመሥጠት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው አገዛዝ ኢህአዴግ ነው። ይህንን ደግሞ በአካልም በቁምም የሞቱት ሁለቱ ጠቅላዮቻችን በራሳቸው አንደበት ፓርላማ ላይ ደስኩረዋል በተግባርም አረጋግጠዋል (በተለይ መለስ ይሄን ሲናገር የሱዳን መሪ እንጂ የኢትዮጵያ መሪ አይመስልም ነበር)። የአካባቢው ነዋሪዎችም ወደ ጎንደር እና ሁመራ በመፈናቀል ላይ ናቸው። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው አልበሽር ወይም የሱዳን መንግስት ሳይሆን መለስ ዜናዊ እና የሙት ራዕይ የሚያስፈፅሙት ጠፍጥፎ የሰራቸው የሱ ተከታዮች ብቻ ናቸው አለቀ!!

Exit mobile version