Gondaronline.com

የኢትዮ ሱዳን ድንበርን ለማጣራት ያደረግኩት ድካምና ውጤት

By Muluken Tesfaw

የኢትዮ ሱዳን ድንበርን ለማጣራት ያደረግኩት ድካምና ውጤት

ክፍል ፩

የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጎንደር ከተማ አደርኩ፡፡ እራት ላይ ‹ትእቢት› የሚባል ምግብ በልቼ ተሰቃይቻለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ናይል ሆቴል ከአንድ የቀዬ ወዳጄ ጋር ሒደን ራት ስናዝዝ ‹የቤቱ ምርጥ ዛሬ ምንድን ነው?›› አልናት አስተናጋጇን፡፡ ‹‹ትእቢት ይምጣላችሁ›› አለችን፡፡ በስሙ እየተገረምን ምግቡ ምን ዓይነት ይሆን ይሆን? እያለን የሚጠጣ አዘዝን፡፡ ‹ምኒልክ› በጎንደር የድራፍት መጠጫ ሆኖ አገኘሁት፡፡ የምኒልክ ብርጭቆ ስለተመቸን ነው መሠል ደጋግመን ተጎነጨን፡፡ የምር በምኒልክ ጃምቦ መጠጣት ደስ ይላል፡፡ ምግቡ መጣ፡፡ መመገብ ጀመርን፡፡ በአጭሩ ምግቡ የሚጣፍጥ ነገር ግን የሚያሰቃይ ነው፡፡ የተፈጨው ሥጋ በበርበሬ ተለውሶ ከዚያ ላይ ቃሪያ (ቄጦ) ታክሎበት የሚጣፍጥ ሆኖ ነው የቀረበ፡፡ እንዳንበላ ያቃጥላል፤ እንዳንተወው ይጣፍጣል፡፡ ደጋግሜ በጎርስኩ ቁጥር በፊቴ ላይ ላቨት መንቆርቆር ጀመረ፡፡ ምግቡ እልክ ያስይዛል፡፡ በላይ በላዩ በምሊክ ድራፍቱን ባንቆረቁርበትም ሊበርድ የሚችል አልሆነም፡፡ እንዳሉትም ትእቢት ያራግፋል፡፡ የሆነው ሆኖ እንዲህ ያለውን ምግብ የጤና ጥበቃ ቢከለክለው የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ የሆቴሉ ባለንብረቶች አንድ ቀን አንድ አቅመ ደካማ ሰው እንዳያሸልብባቸው እሰጋለሁ፡፡

የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ መተማ ማልጄ ወጣሁ፡፡ እግረ መንገዴን ባለፉት ወራት ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት አሰብኩና እያቆራረጥኩ መጓዝን መረጥኩ፡፡ ከጎንደር ጭልጋ፣ ሰራባ፣ ነጋዴ ባህር፣ ገንዳ ውኃና መተማ በየተራ እያረፍኩ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ በየቦታው የተወሰኑ ሰዎችን ለማነጋገር ሞክሬያለሁ፡፡ ሁሉም ግን የሚሰጡኝ መረጃ የተቀራረበ ነው፡፡ ከቅማንት የማንነት ደጋፊዎች ጋር ባደረግኩት ሁሉ አብዛኛዎቹ ብአዴን ሆን ብሎ ቅማንቶችን በወታደር አስጨፍጭፏል የሚል ቅሬታ ይቀርባል፡፡ የሚነግሩኝን ከመስማት ውጭ ምን ያክል እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡

ከመተማና ጭልጋ ወረዳዎች ያሉ አንዳንድ ሲቪል ሠራተኞች የነገሩኝ በጣም አስደንቆኛል፡፡ ከባድ ሆኖ ያገኘሁት ነገር ቢኖር ከሰው ጋር በቀላሉ ግንኙነት መመስረት ነው፡፡ ማንም ሰው ማንንም አያምንም፡፡ መንግሥትን ብታማም ብታሞግስም የወያኔ ሰላይ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንዲሁ ማኅበራዊ ነገሮችን ለማውራት ደግሞ ቶሎ ወደ ወቅታዊ ጉዳዮች ሊገባ የሚችል ሰው የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ጥናቴን አስቸጋሪ አድርጎብኝ ነበር፡፡ ከተጓዦች አሊያም ምግብና ካፌ ላይ ከሚጠቀሙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ለመመስረት አስቸጋሪ መሆኑን መግለጽ በቂ ነው፡፡

ባለፈው የቅማንት የማንነት ጥያቄን ምክንያት በማድረግ የብዙ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የሚያሳዝነው ጎረቤት ከጎረቤት ተገዳድለዋል፡፡ ባልና ሚስት በተኙበት በጩቤ ተወጋግተዋል፡፡ እያንዳንዱ የሆነው ነገር ሁሉ እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስተክዝም ነገር ነው፡፡ አንድ ቋንቋ እያወሩ፣ አንድ እምነት እየተከተሉ አብረው አድገው፣ ተዋልደውና ከብደው እርስ በእርስ ለመተራረድ ከመፈላለግ በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ብዙ ቤቶችና በአውድማ ላይ ያለ ምርት በቃጠሎ ወድሟል፡፡ ለሺህ ዓመታት አብሮ የኖረ ሕዝብ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ማንም እንግዳ ሰው ከዚያ አካባቢ ቢሔድ ያለውን ልዩነት ማሳዬት እንደማይችል በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ ለምን ይህ ሆነ? ብለን ስንጠይቅ ነዋሪውም ሆነ አመራሩ ተጠያቂ የሚያደርገው ሕወሓትን ነው፡፡ ሕወሓት በወልቃይትና ጠገዴ የተነሳውን ተቃውሞ ለማፈን የፈጠረው ብሎም የቅማንት ሕዝብ የአርማጭሆን፣ የቋራን፣ የደንቢያንና የወገራን በከፊልና ሙሉ አካባቢዎችን በመያዝ አዲስ ማንነት ከፈጠረ በወልቃይት የተጀመረው የመስፋት (ታላቅ የመሆን) ምኞት ለማስፈጸም እንደሆነ ሁሉም ሰው ይናገራል፡፡ ባለፉት ዓመታት የታችና ምዕራብ አርማጭሆን አካባቢዎች ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ሰሊጥ ለማምረት የመጡት የሕወሓት ሰዎች የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ጀምረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ጎንደር ላይ ትምህርት በትግርኛ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ሁሉ ከሕጻን እስከ አዋቂ የሚያውቀው ነው፡፡

ባለፉት ወራት በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት የተፈጠረው እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከላይ የገለጽኩት አዲስ ያልኩት መረጃ የሚከተለው ነው፡፡ ከብዙ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ብሎም ከአመራሮች ለማረጋገጥ ሞክሬያለሁ፡፡ የተባለውን እውነት ነው ለማለት ግን እኔ አላየሁትም፤ የተነገረኝ ግን ይህ ነው፡፡ ግጭቱ ሊፈጠር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከትግራይ ክልል በሽተኛን በሚያመላልስ አምቡላንስ መትረጊስ ተጭኖ ወደ ጭልጋ ገባ፡፡ መትረጊሱ በአምቡላንስ የመጣበት ምክንያትም አምቡላንስ ስለማይፈተሸ ነው፡፡ አንዲት የጀበና ቡና በማፍላት የምትተዳደር ሴት እጅግ በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ በጉንፏ (በልብሷ ደብቃ) ይዛ መግባቷን ሁሉ በድፍን ጎንደር ይወራል፡፡ የመጣው መትረጊስ በርካታ ዜጎችን መቅጠፉ ያሳዝናል፡፡ በተለይ ደግሞ የተጨራረሰው በአንድ ሕዝብ መካከል ልዩነት ለመፍጠር መሆኑን ማወቅ ለአእምሮ ሰላም አይሰጥም፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የተደረገው ጎንደሬን እርስ በእርሱ ለማጫረስ በሕወሓት የተሸረበ ሴራ መሆኑ ነው፡፡ ይህን መረጃ አንድ ሕጻን ልጅም፣ አዛውንትም፣ ተራ ተቀጣሪ ሠራተኛም፣ ካቢነውም የሚያወሩት ነው፡፡ አሁን ላይ ሕዝቡ ወደ ቀደመው አንድነቱ የተመለሰ ይመስላል፡፡ በሁለቱም ወገን ማን እያፋጃቸው እንደሆነ ግንዛቤ እንደወሰዱ ያወራሉ፡፡ ብስለት የሚመጣው ዘግይቶ ሆነና የሞቱት ሰዎችን ሕይወትና የጠፋውን ንብረት ማስመለስ አልተቻለም፡፡ ለወደፊትም ይህ እንዳይደገም ስምምነት መኖሩ የሚያስደስት ነው፡፡

ከጎንደር እስከ መተማ ድረስ በየቦታው የወዳደቁ መኪናዎች ይበዛሉ፡፡ ይደንቃል፤ በመኪና አደጋ የሚረግፈውን የአገሬ ዜጋ ሳስብ አዘንኩ፡፡ በአማካይ በየዐሥር ኪሎ ሜትር የተጋጩ መኪናዎችን ወይም መስመር ወጥቶ የተከሰከሰ ተሸከርካሪን ማዬት ይገርማል፡፡ ከጎን የተቀመጡትን ስጠይቅ ‹ይህ ትናንት ነው፤ ዐሥራ አምስት ወታደሮችን የጫነች ኦራል መኪና ከሚኒ ባስ ጋር ተጋጭታ ስትገለበጥ ሁሉም ወታደሮች አመድ ሆኑ፤ የሚኒባሱ ጋቢና ያሉት አልተረፉም፡፡ ይህ ደግሞ ከሱዳን መኪና ጋር ተላትሞ ነው፡፡ ሲኖማ ሲሔድ ጭኖ ሲመለስ ተጭኖ› የሚሉ ነገሮችን ትሰማላችሁ፡፡ ብዙ አደጋ የደረሰባቸውን ተሸከርካሪዎች ባየው ቁጥር ከጎኔ ያሉ ሰዎችን መጠየቅ ሰው ያሰለቻል ብየ ስለማስብ አንዳንዴ እኔም እየሰለቸኝ ዝም ብዬ እጓዛለሁ፡፡ የእኛ ሕይወትም ከእነዚህ እንደ አንዱ እንዳይሆን አሰጋለሁ፡፡

አካባቢው ሙቀቱ ከፍተኛ ነው፡፡ መንገዱ ዳርና ዳር በበርሃ ግራሮች የተሸፈነ ነው፡፡ በርቀት ግራሮቹን ሲያዩያቸው ነጫጭ ወፎች ያረፉባቸው ነው የሚመስሉት፡፡ ምንድን ነው? ብዬ ስጠይቅ ጥጥ የጫኑ መኪናዎች ሲመጡ ጥጡን ዛፎቹ ስለሚያስቀሩት ግራሮቹ በሙሉ ጥጥ አባዛች (ደዋሪ) ሆነዋል፡፡ መተማ ከተማ ወረድኩና ምሳ በላሁ፡፡ ወደ ጋላቫት እስከ ዐሥራ አንድ ሠዓት ድረስ መግባት ይቻላል፡፡ ጋላቫት ማለት ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚነግዱባት የሱዳን ከተማ ነች፡፡ መተማ ማለት ደግሞ ብዙ ሱዳናዉያን የሚሰክሩባት የኢትዮጵያ ከተማ ነች፡፡ ጋላቫት ብዙ የአገራችን ሴቶች በረንዳ ላይ ቡና እያፈሉ ገላቸውንም ጭምር የሚሸጡ አሉ፡፡ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በአካባቢው የበዛ በመሆኑ ብዙ ዓይነት ቋንቋ ተናጋሪ ሴተኛ አዳሪዎች አሉ፡፡ አዘዋዋሪ ደላላዎቹ ካርቱም አሊያም ሊቪያ እናደርሳችኋለን ወደ ኢጣሊያም በቀላሉ ትገባላችሁ እያሉ ገንዘባቸውን ከወሰዱባቸው በኋላ እንጣጥ ፍርጥ እያሉ ከአንዱም ሳይሆኑ ሴተኛ አዳሪ ብቻ ሆነው ይቀራሉ፡፡ የሱዳን ሲም ካርድ ይገዙና ቤተሰቦቻቸውን በሱዳን ሞቫይል በመደወል መተማ ተቀምጠው ካርቱም ነው ያለሁት እያሉ የሚደልሉ ሞኞችም ሞልተዋል፡፡
እንደሰማሁት ከሆነ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩ አንዳንድ ቱባ የመንግስት ባለሥልናትና የፌደራል ፓሊስ አባላት አሉበት፡፡ ደላላዎቹ ወደ ሱዳን ለመሻገር የመጣን ሰው በቀላሉ የሚለዩበት ክሕሎት የሚገርም ነው፡፡ የድንበር ከተማ ከመሆኑ አንጻር ብዙ አዳዲስ ሰዎች ማየት የሚደንቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን አዲስ መተማ ከሚደርሱ ሰዎች መካከል የትኛው ወደ ሱዳን እንደሚሰደድ አሊያም ለኮንትሮቫንድ ንግድ እንደመጣ ማወቅ ለደላላዎቹ ምንም ያክል አይከብድም፡፡ በደላላ እጅ የገባች ተሰዳጅ ደላላው በፈለገው ነገር ያሳምናታል፡፡ ለደላላዎች የእራሳቸውን ሽያጭ ዋጋ ከከፈሉ በኋላ ያሰቡበት ቦታ ሳይደርሱ ከኮሚሽን ተካፋይ ባልሆነ ወይም ቅሬታ በገባው የጸጥታ አካል ተይዘው መተማ ፖሊስ ጣቢያ ይታሰራሉ፡፡ እነዚህ እህቶች አንዳችም ነገር ሳያስቀሩ ለደላላው ሰጥተዋል፡፡ ደላላው ደግሞ ከዚህ በኋላ አይገኝም፡፡ ያላቸው ብቸኛው ተስፋ ራሳቸውን መሸጥ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሴተኛ አዳሪ ሆነው የቀሩ እህቶች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ የበርሃ ሰው የመጠጥና የሴት ነገር አይሆንለትም፡፡ የፍየል ግንባር በምታክል ከተማ ያን ያክል ሰው በዚህ መተዳደሩ ለዚህ ነው፡፡ በአናቱም ሱዳናዉያን ወደ መተማ የሚሻገሩት አንድም ቢራችንን አሊያም እህቶቻችንን ለመሸመት ነው፡፡ መጀመሪያ በገንዛ ብራቸው (ገንዘባቸው) ራሳቸውን ለደላላ የሸጡ ሴቶች ገላቸውን ቸርችረው አጠራቅመው ነገም ካርቱም አሊያም ጣሊያን ለመድረስ ተስፋን ይሰንቃሉ፡፡ የሰው ልጅ ምን ያክል ተስፈኛ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ወላጆቻቸውን በውሸት ካርቱም ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው ያለች አንዲት የጂማ ልጅ መተማ መቀመጧን ማንም እንደማያየት እርግጠኛ ስለሆነች ነው፡፡ በዚያ ላይ የሱዳን ሲም ከኢትዮ ቴሌኮም በተሻለ ኔትወርክ መሥራቱ ላይክስ አይበድል ነው፡፡ ገላቸውን ቸርችረው ትንሽ ገንዘብ ማጠራቀም የቻሉ ሴቶችም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ሰው አግኝቻለሁና ከጎንደር በባንክ ይልክላችኋል ብለው ለቤተሰቦቻቸው በመንገር በሌላ ሰው ስም መተማ ባሉ ባንኮች የሚልኩ አሉ፡፡

ሳስበው አገራችንን ጥለን ለመሔድ ራሳችንን ክደን ክብራችንን አውልቀን የጣልንበት ጉድጓድ ጥልቀት ይገርመኛል፡፡ በአገራችን ሰርተን መለወጥ እንዳንችል ያደረገን ነገር ምንድን ነው? ኢትዮጵያዊነታችን አውልቀን ለመጣል ያስገደደን ምክንያቱ ከቶ ምን ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች ሁልጊዜም አብረውኝ የሚጓዙ ናቸው፡፡ ገንዘብ እንዳንል አንዲት እህት ከተወለደችበት ተነስታ ጣሊያን ወይም የመን ለመድረስ በአማካይ ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ያስፈልጋታል፡፡ ይህንን ብርም ወላጅና አሳዳጊ ከየትም ከየትም ሰብስቦ ተሰድዳ ነገ ለምታሳልፍለት ልጁ ይሰጣል፡፡ ሴትነት በራሱ ፈተና ነው፡፡ በየመንገዱ እየተደፈሩ ከጋላቫት ገዳሪፍ ካርቱም ለመግባት ብቻ ቀናትን በበርሃ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ እንደገና የሱዳን ደላሎች የመንግሥት ጥበቃ ልል በሆነባቸው የግብጽና የቻድ በርሃዎችን አቆራርጠው ወደ ሊቪያ ይገባሉ፡፡ በበርሃ አካላቶቻቸው እየተበለቱም የሚሸጡባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ኩላሊትን የመሠለ አካል አንደኛው መገኛ ቦታው የግብጽ፣ የቻድና የሊቪያ በርሃ ነው፡፡ ከሊቪያ እንደገና ወደ ደቡባዊ ጣሊያን ለመሻገር የሜዲትራኒያን ባህርን ከሻርክ ጋር ታግለው ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፤ ሌላም ሌላም፡፡

ታዲያ የአገሬ ዜጎች በዚህ መልኩ ከሞት ጋር ግብግብ እየገጠሙ ስለምን ይሰደዳሉ? ያልን እንደሆነ መልሱ ነጻነትን ፍለጋ ነው፡፡ ነጻነትን ያጣው ፖለቲከኛ አሊያም ጋዜጠኛ ብቻ አይመስለኝም፡፡ ይህ ቢሆንማ ኖሮ ሁላችንም ጋዜጠኛነቱን አሊያም ፖለቲከኛነቱን ትተን ነጻነታችን ባወጀን ነበር፡፡ በእኛ ምድር ሰው በነጻነት መኖር፣ መስራት አይችልም፡፡ ይህም ብዙዎቻችንን ከሞት ጋር እንድንጋፈጥ አድርጎናል፡፡ መልኣከ ሞት ፊታችን ቆሞ እያየን ኢትዮጵያ ያለው ጭቆናና ባርነት ከፊታችን ከቆመው መልኣከ ሞት የበለጠ ስለሚሆንብን አገራችን ትተን እንሰደዳለን፡፡ ከንአንን የመሰለች አገር እያለችን በባዕዳን መሸጥን መምረጥ በእውነት መረገም ነው፡፡ እርገመቱስ መቼ ይሆን የሚለቀን?

ጋላቫት ከአበሻ ሴቶች ጋር ቡና በዐሥር ብር ገዛሁ፡፡ ከላይ የገለጥኩትን የስደተኞች ጉዳይ በዝርዝር ያጫወቱኝ እነዚሁ አንስቶች ናቸው፡፡ ቡና ለመጠጣት ቁጭ ባልኩበት ሰዓት እንኳ ከዳሚዋን ልጅ ስንት ሱዳን መጥቶ እንደወደቀባት ያየሁት ምስክር ነኝ፡፡ አንደኛው ሲያልፍ ይቆነጥጣታል፤ ሌላኛው ሲመጣ ጡቷ አካባቢ ሆን ብሎ ይነካታል፤ ሌላኛው መቀመጫዋ ላይ፡፡ እርሷ ለሁሉም ትስቃለች፡፡ ለሁሉም የፈላጊነት ስሜት ታሳያለች፡፡ የእኛ እህቶች ኑሮ ይህ ነው በመተማና በጋላቫት፡፡ ወደ ቋራ መሔድ ስለነበረብኝ ሒሳብ ከፍየ ተነሳሁ፡፡ ደረቴ ላይ በጣም የሚያቃጥል ስሜት ተሰማኝ፡፡ ለካስ አንገቴ ላይ ያለው ሐብል ግሎ በእሳት የተጠበሰ ብረት ሆኗል፡፡ በእጄ አነሳሁት አቃጠለኝ፡፡ የሚገርም ነው፡፡ በአካባቢው ጸሀይ ከአናት አንድ ሜትር ከፍታ ያላት ነው የሚመስለው፡፡ ብዙ ሰዎች ራቁታቸውን መሆን ይወዳሉ፡፡ ሽፍን ጫማና ጥቁር ቲሸርት በመልበሴ እንግዳ እንደሆንኩ በቀላሉ እለያለሁ፡፡ ፀሀይ ገና በማለዳ ይህን ያክል ኃይል ካለት ከተሲያት ምን እንደምትሆን ማሰብ ይቻላል፡፡

መተማ ዮሐንስ ገባሁ፡፡ ይህ ቦታ አጼ ዮሐንስ ከድርቡሾች ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፈበት ነው፡፡ በኒም (በብዛት ያለ ዛፍ) ዛፎች የተሸፈነውን የመተማ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሜ ከዛፎቹ ሥር ትንሽ ተቀመጥኩ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሮፌሰር መስፍንን በድንበር ጉዳይ ስጠይቃቸው ‹ስለምን አንድ ቁርጠኛ ሰው ጂፒኤስ ይዞ በመሔድ ትክክለኛ ካርታው የት ላይ እንደሚያርፍ አያረጋግጠም?› የሚል መልስ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ የእሳቸው መልስ ይህን እንድወስን ሳያደርገኝ አልቀረም፡፡ ጎግል ማፔን ከፍቼ የት ላይ እንዳለሁ ለማረጋገጥ ሙከራ አደረግኩ፡፡ ምንም እንኳ ያለኝ የካርታ እውቀት ውስን ቢሆንም ጎግል ያለሁበት ቦታ (ከረንት ሎኬሽን) ከሱዳን ድንበር ትንሽ ሜትሮችን ራቅ ብዬ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ቦታ አሁንም ድሮም የአገራችን ነው፡፡ ይህ ትክክል ከሆነ የት ቦታ ላይ ሊሆን ይችላል ወደ ሱዳን የተካለለ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ግድ ይለኝ ነበር፡፡ የጀበና ቡና እና ጫት ደባልቀው ወደሚጠቀሙ ወጣቶች ተደባልቄ ወሬ ጀመርኩ፡፡ ጥርጣሬ በማይፈጥር መልኩ የድንበርን ጉዳይ ለማንሳት ሞከርኩ፡፡ በአጭሩ በዚያ ማኅበር የተነሳው ሐሳብ የሚያስረዳው እንደመተማ ያሉ ታዋቂ ከተሞች ወደፊትም እንደማይነኩ ነገር ግን ሰው ያልሰፈረባቸው ጥቅጥ ጫካዎች በተለያየ ጊዜ ወደ ሱዳን እየተካለሉ እንደሆነ ፍንጭ ሰጡኝ፡፡ ስለዚህ ተወደድም ተጠላም ከመተማ ወደ ሰሜንና ደቡብ የቋራና የአርማጭሆ ጫካዎች መፈተሸ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡

ቋራ ለመሔድ ወደ ሸኽዲ ከተማ ተመለስኩ፡፡ ሸኽዲ ከተማ ከመተማ 30 ኪሎ ሜትሮችን ያክል ወደ ጎንደር መስመር ትገባለች፡፡ ከተማዋ መሐል አስፓልት ላይ ቆመው የሚያድሩ ወይም የሚውሉ መኪናዎች ብዙዎቹ ነዳጅ ጫኝ ናቸው፡፡ አንድ መኪና ላይ የእሳት አደጋ ቢከሰት ያ ሁሉ ነዳጅ የተሸከመ መኪና ብቻ ሳይሆን ከተማዋም እንዳለ ልትጠፋ ትችላለች፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የከተማዋ ነዋሪም ስጋት እንደሆነ ለማረጋገጥ ሞክሬያለሁ፡፡ የገንዳ ውሃን እንደተሻገርን አንድ ቦቲ ተቃጥሎ የመንደሯን አብዛኛዎቹን ቤቶች እሳቱ ላፍ አድርጓቸዋል፡፡ መኪና መንገዱም በመዘጋቱ በቅያሬ ነው የሔድነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላ የገረመኝ ነገር የኮንትሮ ባንድ ነጋዴዎች ጉዳይ ነው፡፡ ከጋላቫት በርካታ ነገሮች በእርካሽ ዋጋ ይገዛሉ፡፡ የልብስ ማጠቢያ ሳሙና (ኦሞ) በኪሎ ግራም፣ ጫማ፣ የመኝታ ልብሶች፣ ጥይትና ሌሎችም የደራ ገበያ አላቸው፡፡ መተማ ጉምሩክ ዘመድ ያላቸው ሰዎች በቀላሉ ያልፋሉ፡፡ ዘመድ የሌላቸው ደግሞ አንድም የመተማ ጉምሩክ ኬላን አሊያም የመተማ በርሃን አታለው ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱም ቀላል አይደሉምና ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ አስቀድመው በስልክ የሚሰጡትን ኮሚሽን (?) ተደራድረው ያለምንም ፍተሻ የሚያልፉት ብዙ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ሸኽዲ ከሚገኘው የመተማ ጉምሩክ ኬላ ላይ ንብረታቸውን ተቀምተው የሚያለቅሱ ሰዎች አይታጡም፡፡ ጉምሩክ ሠራተኞቹ አንዳንድ ጊዜ ከኮንትሮ ባንድ ነጋዴዎች ላይ ግማሹን ወስደው መካዝን ሳያስገቡ ያስቀምጡታል፡፡ ያ የግላቸው መሆኑ ነው፡፡ ወደ መካዘን ለምን አይገባምና ደረሰኝ አልትሰጠኝም ብሎ የሚከራከር ንብረቱ የተወሰደበት ግለሰብ ሙሉን ሊቀማ ይችላል፡፡ የሚፈትሸው ሰው እንደሚወስደው እያወቁ ሁሉንም ከማስዘረፍ ብለው ብዙዎች ይተዋሉ፡፡ አንዳንዶች ብልጥ ነጋዴዎች ደግሞ መኪና ውስጥ ላለው ሰው ያከፋፍሉና የእኔ ነው በሉ ይላሉ፡፡ ይህም አንድ ሰው አንድ ዓይነት እቃ በቁጥር ይዞ መንቀሳቀስ ስለሚችል ከመዘረፍ ይድናሉ፡፡

ጥይት ወደ ጎንደር የሚገባበት መንገድ አስገርሞኛል፡፡ የጠርሙሱ ስፕራይት ለስላሳ (ሱዳኖች እስቲም ይሉታል) ቀለሙ አረንጓዴ ነው፡፡ ስቲሙን የተወሰነ በመጠጣት አሊያም በመድፋት ካጎደሉት በኋላ ብዙ ጥይት ወደ ላስቲኩ ይጨመራል፡፡ ከዚያም ጥይት የሚነግደው ግለሰብ እስቲሙን የሚጠጣ በመምሰል ወደ አፉ እያስጠጋ ጥይቶቹን ከጉምሩክ በቀላሉ ያሳልፋል፡፡ እርግጥ ይህ ዘዴ አሁን ተነቅቶበታል፡፡ በዚህ ሁሉ ዘዴ ማሳለፍ የማይችል ከሆነ ግን ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ በጫካ ከበርሃና ከአራዊት ጋር ታግሎ ሸኸዲን ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሌላም አማራጭ አለ፡፡ ከሸኽዲ መሀል ከተማ ላይ ወደ ቋራ በመታጠፍ ቢሻው በቆላ ድባ አሊያም በአቸፈር አድርጎ ማምለጥ ይችላል፡፡ በቋራ በኩል ፍተሻው ጥብቅ አይደለም፡፡ ሸኽዲ ከተማ መካከል ላይ መውረድ ቢኖርብኝም ረስቼ የጉምሩክ ኬላ ላይ ስደርስ ከተማውን ማለፌን አረጋገጥኩ፡፡ በዚህ ከመጠን በላይ በሚሞቅ ጸሀይ እንደገና እየተቃጠልኩ ወደ ኋላ ተመለስኩ፡፡ የሚገርመው ከፍተኛ ንፋስ አለ፤ ነገር ግን ንፋሱ በራሱ ፊት ይጠብሳል፡፡ ንፋስ ብርድ ሲሆን እንጅ ሲያቃጥል ያየሁት መተማ ነው፡፡ ሙቀቱ ገና በረፋድ እንዲህ ከሆነ እኩለ ቀን ላይ ምን እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡

ከሸኽዲ ወደ ገለጎ ቋራ ለመሔድ መኪና ማፈላለግ ያዝኩ፡፡ የቋራና የሽንፋ ሰው በጭነት አይሱዚ እላይ ተጭኖ መሔድን ይመርጣል፡፡ ለምን እንደሆነ ስጠይቅ የመኪናው ውስጥ ሙቀት ከመጠን ያለፈ ስለሆነ ከጭነቱ እላይ መሆን የተሻለ እንደሆነ ለእኔ ለእንግዳው ነገሩኝ፡፡ እድለኛ ነኝ መሰል ወደ ቋራ ሒዳ እንደገና የምትመለስ ፒካ አገኘሁና በእርሷ ወደ ቋራ መንገድ ጀመርኩ፡፡ ሽንፋ ደርስን፡፡ ሽንፋ ከአንድ ወር በፊት ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ በእርስ በእርስ ግጭት የተጎዱ ተፈናቃዮች ሰፍረውበት ነበር፡፡ እዚህ አካባቢ ያለው ሙቀት መተማ ካለውም ያይላል፡፡ ንፋሱም አይንቀሳቀስም፡፡ በነገራችን ላይ መተማና ሽንፋ አካባቢ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በተኙበት ሊያሸልቡ ስለሚችሉ ሌሊት ላይ የአየር ሁኔታውን አይተው የፖሊስ አምቡላንስ መኪና ከእንቅልፍ ይቀሰቅሳሉ ብለውኛል፡፡ አሁን የምሔድበት አካባቢ ጫካ ብቻ ነው፡፡ የቋራ ወረዳ ኹለት ሦስተኛው የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን ጥቅጥቅ ጫካ ብቻ ነው፡፡ ፓርኩ እኛ ከምንሔድበት መንገድ ወደ ቀኝ ገባ ብሎ ነው፡፡ ከሰሞኑ የዓለማችን ሳይንቲስቶች ከኹለት መቶ በላይ አናብስቶችን በሳትላይት አይተናል ያሉት ከዚህ ነው፡፡ ፓርኩ በሱዳን ድንበር የተዋሰነ ነው፡፡

ገለጎ (ቋራ) ስንደርስ ዘጠኝ ሰዓት አልፎ ነበር፡፡ እንደማንኛውም የሙቀት አካባቢ ከተሞች ሰዎች ሁሉ በረንዳ ላይ ከገመድ በተሰራ ወንበር ወይም አልጋ ላይ ተቀምጠው ይመገባሉ፤ ይጠጣሉ፡፡ ምንም እንኳ የወረዳው ከተማ ብገኝም የሱዳን ድንበር ካለሁበት በጣም የሚርቅ ብቻም ሳይሆን መንገዱ የራሱን መኪና ላልያዘ ሰው የሚመች አይደለም፡፡ ስለሆነም ድንበሩን በተመከተ የማቀርበው ያየሁትን ሳይሆን በቅርብ የሰማሁትን ብሎም የተቻለኝን ያክል ለማረጋገጥ የሞከርኩትን ያክል እንደሆነ አንባቢ እንዲረዳ እሻለሁ፡፡ ቋራ ላይ የሰማሁት በኋላም ሸኽዲ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ያረጋገጡልኝ ነገር ቢኖር የሱዳን ወታደር ሽንፋ ወንዝ ተሻግሮ የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መስፈሩን ነው (ሽንፋ ወንዝ የመተማና የቋራ ወረዳዎችን እያካለለ ከሔደ በኋላ እንደገና ለሱዳንና ለኢትዮጵያ ድንበር ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሆኖ የአላጣሽ ፓርክን እየከለለ በመጨረሻም በበርሃ ሰርጎ ይቀራል እንጅ ከአባይ አይጨመርም አሊያም ሌላ ገባር የለውም፡፡ መተማና ቋራ ድንበር ያለችው ከተማ በወንዙ ስም ሽንፋ ትባላለች)፡፡ የሰፈሩበት አካባቢ ‹ሰልፈረዲ› ቀበሌ ቁጥር 3 በተባለ በርሃ ቦታ ነው፡፡ ቀድም ባሉት ጊዜያት የሱዳን ወታደሮች ቁጥር አምስት በተባለው ‹አንቶቭ ኮረብታ› ካምፕ ነበራቸው፡፡ ይህ ቦታ በአማርኛ ቁጥር 5 ተብሎ እየተጠራ የሱዳን ግዛት እንደሆነ ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ በዚህ አካባቢ ያሉ የሠፈራ ጣቢያዎች በቁጥር ይጠራሉ፡፡ አስቀድሞም የሱዳን ግዛት ከሆነ ቁጥር 5 ተብሎ መጠራት ላያስፈልገው ይችል ነበር፡፡ ከባዱ ነገር ከዚህ አካባቢ ሁሉም በኃይል እንጅ በሕግ የሚተዳደር ስለሌለ ቁጥር 5 ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያ እንደሆነች የምትታወቀው ቁጥር 3 በበርካታ ግጭቶችና የቋያ ቃጠሎ ምክንያት ሰው አልባ ናት፡፡ በዚህ ከብት የሚያረቡ ዘላኖች ብቻ ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ግን በቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው የሱዳን ወታደር ወደዚህች ቀበሌ የመጣው፡፡ በነገራችን ላይ የሰልፈረዲ ቀበሌ ስፋቱ ራሱን የቻለ አንድ ወረዳ ቢያንስ እንኳ ንዑስ ወረዳ ይሆናል፡፡ መተማ ወረዳን የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ለጉብኝት በሔደ ጊዜ የመተማና የቋራ ሕዝብ ተወካዮች ‹‹እነዚህ የሱዳን ወታደሮች ስለምን እኛ ድንበር ውስጥ ካምፕ ሠርተው መኖር ተፈቀደላቸው?›› የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የመጡት ኮሚቴዎች በትክክል መልስ አልሰጡም፡፡ በገደምዳሜ ‹‹በአካባቢው ያሉ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በጋራ ለመከላከል በእኛ ጥሪ ነው የመጡት ሆኖም የክልሉ መንግሥት እንዲወጡ እየተነጋገረ ነው›› በማለት መልሰዋል፡፡ በአካባቢው ያለን ጸረ ሰላም ኃይል ለመከላከል በሚል እኛ ድንበር ላይ የሱዳን ወታደሮች በቋራ መስፈራቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ የሚገርመው ነገር አንድ መንግሥት ስለ አገሩ ዳር ድንበር ዴንታ በሌለበት በዚህ ጊዜ እነዚህ ነዋሪዎች ግን የሱዳን ወታደር ተሻግሮ መጥቶ ቢራ ጠጥቶ ከመሔድ በዘለለ ካምፕ መሥራታቸው የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የሽንፋ ወንዝ እስኪሞላ ድረስ በተጠንቀቅ እየጠበቁ ነው፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ የሱዳን ወታደር የእኛ አገር ገበሬዎች በተኩስ ከገጠሙት እየዘለለ ወደ ውኃ በመግባት በወንዝ የመወሰድ እድል ብቻ ይኖረዋል፡፡ ቆሞ እንኳ ገበሬዎችን ለመከላከል አቅም እንደሌለው ነው ያወሩኝ፡፡ ነገሩን ጠቅለል ስናደርገው በዚህ አካባቢ የሱዳን ወታደሮች እኛ ክልል ውስጥ ሰፍረዋል፡፡ የሰፈሩበት ቦታ የተሰጣቸው ይሁን አሊያም እንደተባለው ለጊዜያዊነት ብቻ ማንም አያውቅም፡፡ ነገር ግን ቁጥር 5 የተባለው አካባቢ በትክክል በሱዳን የሚተዳደር ቦታ ነው፡፡ ቀድሞ የማን ቦታ ነበር ለሚለው ጥያቄ እኔ መልስ መስጠት አልችልም፡፡

የሚቀጥል…

Exit mobile version