Gondaronline.com

የቆምጬ አምባው ጨዋታዎች በ አፈንዲ ሙተቂ

ጓድ ቆምጬ አምባው በስማቸው የሚነገሩትን ጨዋታዎች በኔ ስም የተፈጠሩ ተረቶች ይሏቸዋል፡፡ ሰውዬውን በቅርበት የሚያውቁት ግን በርሳቸው ስም የተፈጠሩት ጨዋታዎች ከፊል እውነታ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ በርካታ ሰዎች ጨዋታዎቹን እያወሱ የሰውዬውን ጅልነት ሊያሳዩ እንደሚፈልጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ቆምጬ አምባው ነገር የገባቸው ብልጥ ነበሩ እንጂ በጭራሽ ጅል አይደሉም፡፡ ይህንን ለማሳየት እንዲቻለንም በርሳቸው ስም ከሚነገሩት ጨዋታዎች መካከል ጥቂቶቹን እንጽፍላችኋለን፡፡
*****
በደርግ ዘመን የመሰረት ትምህርት ፕሮግራም ተጀምሮ ነበር፡፡ ያ ፕሮግራም በግዴታ የሚከናወን በመሆኑ አብዛኛው ሰው ሰበብ እየፈጠረ ከትምህርቱ ይጠፋ ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱት ቆምጬ አምባው በወረዳው ላይ አንድ አዋጅ አሳወጁ፤ “መሰረተ ትምህርት የማይማር ቡዳ ነው” የሚል፡፡፡ በመሆኑም የሀገሬው ህዝብ “ቡዳ ነው” ላለመባል ትምህርቱን ቀጥ ብሎ መማር ጀመረ፡፡
*****
ጓድ ቆምጬ የዘመኑ ባለስልጣን ቢሆኑም ኮሚኒስት አልነበሩም፡፡ ከኮሚኒስቶች ጋር ሲውሉም ኮሚኒስቶች የሚተገብሯቸውን ድርጊቶች በውስጠ ወይራ መንገድ ይተርቧቸው ነበረ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ በዘመኑ ደንብ ስብሰባ የሚያሳርገው በመፈክር በመሆኑ ለሰብሰባው የተጋበዘው ቱባ ባለስልጣን በሰብሰባው ማብቂያ ላይ “ኢምፔሪያሊዝም ይውደም” የሚል መፈክር አወረደ፡፡ ጓድ ቆምጬም የቀኝ እጃቸውን በማንሳት “ይውደም!” አሉ፡፡ አጠገባቸው ቆሞ የነበረው ካድሬ “ጓድ ቆምጬ! በመፈክር ጊዜ የግራ እጅ ነው የሚወጣው እኮ!” ቢላቸው እሳቸውም “ወደዚያ ተው! በደንብ የሚያወድምልኝን እኔ ነኝ የማውቀው” የሚል መልስ ሰጡት ይባላል፡፡
*****
በሌላ ጊዜ ደግሞ የጎጃም ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ጓድ ካሳዬ አራጋው ወደ ደብረ ወርቅ ሄደው ነበር፡፡ ጓድ ካሳዬ ጉብኝታቸውን አብቅተው ሊመለሱ ሲሉ ጓድ ቆምጬ አምባው ወደ መድረኩ ወጥተው እንዲህ የሚል መፈክር አወረዱ!!
“እምዬ ማሪያም ጓድ ካሳዬ አራጋውን ወደ ሀገራቸው በሰላም ታግባ!!”
የጎጃም ህዝብም “ታግባ!” እያለ ተቀበላቸው፡፡
(ክርስቲያኑ ቆምጬ አምባው ህዝቡ የማያምንበትን መፈክር ለማውረድ አልፈለጉም)፡፡
*****
አንድ የአውራጃ ባለስልጣን በቆምጬ አምባው ስራዎች ተናዶ ኖሮ “እርስዎ መሃይም ነዎት፤ የመሃይም ስራ ነው የሚሰሩት” የሚል ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል፡፡ አይበገሬው ቆምጬ አምባውም ለሰውዬው እንዲህ የሚል መልስ ጻፉለት፡፡
“መሃይምስ አንተ ነህ! በእጅ መጻፍ አቅቶህ በታይፕ የምታስጽፍ!!”
*****
አንድ ጊዜ ደግሞ አመለ ክፉ የደርግ በለስልጣን የነበሩት ኮሎኔል ዘለቀ በየነ ደብረ ወርቅን ሊጎበኙ ይመጣሉ፡፡ ጓድ ቆምጬ በወቅቱ የወረዳውን ገበሬዎች የህብረት እርሻ እያሳረሱ ነበር፡፡ ኮሎኔሉ ወደ ስፍራው የመጡት ጉቦ ፍለጋ ለመሳሰሉት ልክስክስ ነገሮች እንደሆነ ገብቷቸዋል፡፡ በመሆኑም የእርሻውን ስራ ሳያቋርጡ ቀጠሉበት፡፡ ኮሎኔል ዘለቀ በሁኔታው ተናደው “እኛን አክብረህ መቀበል ሲገባህ በእርሻው ውስጥ ከገበሬዎች ጋራ ትጎለታለህ እንዴ?” የሚል መልዕክት እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፡፡ ጓድ ቆምጬ አምባውም መልዕክቱን ያመጣው ሰውዬ ወደ ኮሎኔሉ ተመልሶ እንዲህ የሚል መልዕክት እንዲነግራቸው አደረጉ!!
“ጓድ ኮሎኔል! ሌኒን “አብዮት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው” ብሎ የለም እንዴ?… አብዮታዊ እንቅስቃሴ ጀምሬ እንዴት ብዬ ነው የማቋርጠው?”
(ጠላትን በዘዴ ማባረር ይሉሃል ይህ ነው)::
*****
ከነዚህ ጨዋታዎች ለመረዳት እንደምትችሉት ሰውዬው ጅል እየመሰሉ በረቀቀ መንገድ ጠላቶቻቸውን ይሸውዷቸው ነበር፡፡ አካሄዳቸውን በደንብ ያስተዋለ ሰው ጅል ናቸው የሚያስብል ባህሪ እንዳልነበራቸው በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ሀገሩን ያስተዳደሩት የህዝቡን ስነ-ልቦና እና እምነት ባገናዘበ መንገድ ነው፡፡ “ስቴድየም በእበት ለቀለቁ”፤ “አብዮቱ ግቡን ሲመታ ለያንዳንዳችሁ አንድ ኳስ ይሰጣችኋል” ወዘተ… እየተባሉ የሚነገሩት ቀልዶች ግን በርሳቸው ጠላቶችና በምቀኞቻቸው የተፈጠሩ ወሬዎች በመሆናቸው እዚህ ውስጥ አንቀላቅላቸውም፡፡
በነገራችን ላይ ቆምጬ አምባው በጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም መሸለማቸውን ታውቁ ኖሯል?… ሽልማቱን እምቢ ማለታቸውንስ? አዎን! ሊቀመንበር መንግሥቱ የደብረ ወርቅ ወረዳን ጎብኝተው ሲያበቁ ባዩት ነገር በመርካታቸው ሽጉጣቸውን አውጥተው ጓድ ቆምጬን ሊሸልሟቸው ይንደረደራሉ፡፡ ጓድ ቆምጬ ግን “እኔ ሽጉጥ ምን ይሰራልኛል? ከሽፍታ ያስፈታሁት አስራ ዘጠኝ ሽጉጥ ስላለኝ እርሱን አልፈልግም፤ ይልቅ የወረዳዬ ህዝብ በውሃና በመብራት እጦት እየተቸገረ ስለሆነ መብራትና ውሃ እንዲያስገቡልን በአክብሮት እለምናለሁ” አሏቸው፡፡ ጓድ መንግሥቱም ውሃና መብራት እንዲገባላቸው ትዕዛዙን ለጠቅላይ ሚኒስትራቸው ለጓድ ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ አስተላለፉ፡፡ በስልሳ ቀናት ውስጥ ደብረ ወርቅ የውሃና የመብራት ተጠቃሚ ሆነች፡፡
——
አፈንዲ ሙተቂ

Exit mobile version