Gondaronline.com

ዝቋላ ሀገሩ የት ነው?

በ ዳንኤል ክብረት

የዚህች ሀገር ባለቤቶች ሁላችንም ካልሆንን በቀር በተናጠል ማንም ባለ ግዛት ሊሆን አይችልም፡፡ ሉሲ አማራ ትሁን ኦሮሞ፣ አፋር ትሁን ሶማሌ፣ ጉሙዝ ትሆን ትግሬ፣ ወላይታ ትሁን ጋሞ የሚያውቅ የለም፡፡ በአኩስምና አካባቢው በተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ነገሥታቱ የሚገዙትን ሀገር ሕዝቦች ስም ይዘረዝራሉ፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካና የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የምንሻኮተው ብዙዎቹ ጎሳዎች/ነገዶች ስማችን የለም፡፡ ሁላችንም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከተለያየ ቦታ መጥተን የሠፈርንበት ላይ ረግተን ነው ዛሬ የምንገኘው፡፡ የሕዝብ የሥፍራ ንቅናቄ የታሪኳ አንዱ መገለጫ በሆነቺው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ሌላውን ሀገርህ አይደለም፣ ክልልህ አይደለም፣ መሬትህ አይደለም እንደማለት ያለ ታሪካዊ ኃጢአት የለም፡፡ ትንሽ በታሪክ ወደኋላ ስንጓዝ ዛሬ ክልልና መንደር በመሠረትንበት ቦታ ሌሎች ሲኖሩበት እናገኛለን፡፡ አሁን የያዝነው ቦታ ከምእተ ዓመታት በፊት የሁላችንም አልነበረም፡፡ ሁሉም ሠፋሪ ነው፡፡ ነባር መሬቱ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምታዋጣን የሁላችን እንድትሆን አድርገን ከሠራናት ነው፡፡ እንደ አጥር ሠሪ እንስሳት(territorial animals)  ከዚህ በመለስ ማንም አይገባብኝም፡፡ እኔን ያልመሰለውን በዚህ አካባቢ ላየው አልፈልግም የሚለው ሂደት መጨረሻው መበጣጠስ ነው፡፡ የልዩነትን ያህል ተመሳሳይነት ሰፊ አይደለም፡፡ ተመሳሳይነት እጅግ ጠባብ ነው፡፡ አንድ ነኝ ብሎ በሚያስብ ‹ብሔርም ሆነ ብሔረሰብ› ውስጥ አያሌ ልዩነቶች አሉ፡፡ የጎሳ፣ የቤተሰብ፣ የአካባቢ፣ የእምነት፣ የፍላጎት፣ የርእዮተ ዓለም፣ የጾታ፣ የሀብት ደረጃ፣ የሥልጣን፣ ምኑ ቅጡ፡፡ ሁሉም ተመሳሳዩን ፍለጋ ከሄደ መጨረሻው ግለሰብ ነው፡፡ በሰውነት ክፍላችን እንኳን ተመሳሳያቸውን ከሚያገኙት ይልቅ የማያገኙት ይበልጣሉ፡፡ ሰው እንኳን በግለ ሰብእነት ሕልው የሆነው ልዩነትን በአንድ ኑባሬ ውስጥ በማስተናገድ ችሎታ ነው፡፡ አንድን አካባቢ ‹በተመሳሳይነት ሚዛን› አንድነቱን ጠብቆ ማቆየት አይቻልም፡፡

ያማ ቢሆን ኖሮ ሶማልያን የመሰለ ጠንካራና የማይናወጥ መንግሥት አይኖርም ነበር፡፡በእምነትና በቋንቋ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሄ ተመሳሳይነታቸው ግን አንድነታቸውን ሊጠብቅላቸው አልቻለም፡፡ ትኩረታቸው ‹ተመሳሳዩን ብቻ ፍለጋ› በሚለው ላይ ስለነበር ወደ ነገድ፣ ወደ ጎሳ፣ ወደ ጎጥ፣ ወደ ቤተሰብ እየወረዱ ነው በጦርነት ሲታመሱ የኖሩት፡፡ ለሶማልያ ችግር መፍትሔው ተመሳሳይን መፈለግ አይደለም ልዩነትን ለማስተናገድ መቻል ነው፡፡ ተመሳሳይነት ጠባብ ነውና፡፡ ጠባብነት ከሚመነጭባቸው ምንጮች አንዱም ‹ተመሳሳይን ብቻ ፍለጋ› ነው፡፡

የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዛሬ በሚታወቅበት ቦታ ላይ ከተገደመ ከ700 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚያ አካባቢ አያሌ መንግሥታትና ሕዝቦች ተፈራርቀዋል፡፡ ገዳሙ ግን መከራ ሲገጥመው እየቀዘቀዘ፣ መከራውን አሸንፎ ደግሞ እንደ ፍግ እሳት እንደገና እየጋመ ከእኛ ዘመን ደርሷል፡፡ ወደዚያ ገዳም የሚገቡ መነኮሳት ሰማያዊቷን ሀገር የሚናፍቁ፣ ጾምና ጸሎትን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ የጻድቁን ቃል ኪዳን የሚጠብቁ ናቸው፡፡ የመነኩሴ ሀገር የለውም፡፡ መነኮሳት እንኳን ከእናትና አባታቸው በተወለዱበት ሀገር ቀርቶ ስማቸውና ታሪካቸው በማይታወቅበት ሀገርም ‹ሀገርህ የት ነው?› አይባሉም፡፡

ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ግብጽ ውስጥ ኖረዋል፣ ሊባኖስ ውስጥ ኖረዋል፣ ሶርያ ውስጥ ኖረዋል፤ ግሪክ ውስጥ ኖረዋል፣ ሮም ውስጥ ኖረዋል፡፡ አርመን ውስጥ ኖረዋል፡፡ ‹ሙሳ አል ሐበሽ› ሶርያ ውስጥ የታወቀ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ነው፡፡ የሶርያ ድርሳናት እንደሚነግሩን ሙሳ (ሙሴ) የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ ነው፡፡ ዛሬ ከኢትዮጵያ በላይ ሀገሩ ሶርያ ናት፡፡ በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያውያን መነኮሳት ገዳም በሊባኖስ ውስጥ በቁፋሮ ተገኝቷል፡፡ ቫቲካን ውስጥ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት ማረፊያ ለታሪክ ቆሞ ይታያል፡፡ አርመን ውስጥ ኤቺሚዚን የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ገዳም ዛሬም አለ፡፡

እንዲያውም ዛሬ የዝቋላ መነኮሳት እንደገጠማቸው ያለ ‹ሀገርህ አይደለም› የሚል ሰውነት ያልገባው ፈተና ሲገጥማቸው ራሱ ፈጣሪ ነበር ይገሥጽላቸው የነበረው፡፡ በተአምረ ማርያም ላይ የተጻፈውና ኢየሩሳሌም በጦርነት ምክንያት በተዘጋች ጊዜ በ13ኛው መክዘ አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘው ኢትዮጵያዊ ታሪክ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ይህ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች ሁሉ የታወቀውና ዛሬም ድረስ በጎልጎታ መግቢያ በር ላይ ምልክቱን ትቶ ያረፈው ታሪክ እንዲህ ነበር የተፈጸመው፡፡

ከዛሬ 700 ዓመታት በፊት አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዛል፡፡ ከአፍሪካ ምድር የሄደ ብቸኛ ሰው ነበር፡፡ የትንሣኤ በዓል ሲከበር የትንሣኤውን መብራት ከመቃብሩ የሚያወጡት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ ግን ብቻውን ስለነበር ማንም ከቁም ነገር አልቆጠረውም፡፡ እንዲያውም  በመልኩ ምክንያት ተንቆ ‹ያለ ሀገርህ ለምን መጣህ፣ ውጣ› ተባለ፡፡ እርሱም ወጥቶ መግቢያው በር ላይ ሲያለቅስ በላዩ ላይ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ታየ፡፡ ተሳላሚው ሁሉ እምነቱንና ታላቅነቱን አደነቀ፡፡ ብርሃኑ የወረደበት ቦታም ተሰንጥቆ እስከ ዛሬ ድረስ ይታያል፡፡ ወደ ጎልጎታ የሚገባም ሁሉ ይሳለመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን መነኮሳት በሌሎች ሀገሮች ሄደው በኪደተ እግራቸው የባረኩት ሁሉ ሀገራቸው ሆኖ መኖራቸው ብቻ አይደለም የሚገርመው፡፡ ከመላው ዓለም የመጡ መነኮሳትም በዚህች ሀገር ውስጥ ‹ከየት መጣችሁ? የማንስ ወገን ናችሁ?›› ተብለው ሳይጠየቁ እንደ ሀገሬው ዜጋ ኖረዋል፡፡ አባ መጣዕ(ሊባኖስ)፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ አርባ ሐራ፣ አምስቱ የመንዝ ቅዱሳን፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እጨጌ ዕንባቆም፣ ማኅበረ ጻድቃን፣ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ መጥተው ኖሩ፡፡ እዚህችም ሀገር ዐረፉ፡፡ ገዳማቸው ገዳማችን፣ ታሪካቸው ታሪካችን ሆነ፡፡

 

ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ ነው የዝቋላ ገዳም መነኮሳት ዝቋላ ‹ሀገራችሁ አይደለም›› የተባሉት፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን አይደሉምን? እዚህ ቦታኮ ከ700 ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ እዚህ አካባቢ ከ700 ዓመታት በፊት የነበሩ ዜጎች አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሲመጡ ‹ኦቦ› ብለው ተቀበሏቸው እንጂ ‹ሀገርዎ አይደለም ይውጡ› አላሏቸውም፡፡ ዛሬ በሥልጣን ላይ ካሉትና ገዳሙን በኢሬቻ መተካት ከሚፈልጉት ሰዎች ይልቅ ያኔ የነበሩት ሰዎች ልበ ሰፊዎች፣ አስተዋዮች፣ የሰውነት ክብር የገባቸው፣ የሀገርን ትርጉም የተረዱ፣ ከዘር ይልቅ ለሰውነት ታላቅ ቦታ የሚሰጡ፣ ሰውን በምግባሩ እንጂ በቋንቋውና በቀለሙ፣ በዘሩና በአጥንቱ የማይለኩ ነበሩ፡፡

የአንድ ክልል የቱሪዝም ቢሮ አንድን ገዳም ነጥቆ በገዳሙ ሥርዓት የማይፈቀድ ሌላ እምነትን ለመተካት ማነው ሥልጣን የሰጠው? በዚያ ገዳም ክልል ውስጥ ሊከበሩ የሚገባቸው ሃይማኖታዊ በዓላትንስ በምን ቀኖናዊ ሥልጣኑ ነው የሚወስነው? ለምንስ ነው እነዚህን መነኮሳት እየጠራ የሚያስፈራራው? ይኼ ገዳምኮ ዘመናትን ሁሉ ተሻግሮ እዚህ እንዲደርስ ያደረገው በእምነቱ ጽኑ የሆነው የአካባቢው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ሕዝቡ እዚያ ገዳም ለጸሎት የተጉ መነኮሳት እንደሚገኙ፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የቃል ኪዳን ቦታ እንደሆነ የሚያምን ነው፡፡ በየዓመቱ በጥቅምትና በመጋቢት 5 ወደ ቦታው በመሄድ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል ከሚያከብረው ሕዝብ አብዛኛው የአካባቢው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ ታድያ እነዚህ አካላት ይህንን አስተሳሰብ ከየት አመጡት?

ይኼ ተልዕኮ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ አይደለም፡፡ የጠብ ጫሪነት ተልዕኮ ነው፡፡ በሰላም የኖረውን ሕዝብ የማበጣበጥ ተልዕኮ ነው፡፡ መጋቢት 5 ቀን በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል ‹ኢሬቻን በጠበሉ ቦታ እናከብራለን፣ ሐውልት እናቆማለን› ብሎ በሕዝብ መገናኛ ማወጅ ጠብ ያለሽ በዳቦ እንደማለት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ያጸድቀኛል ብሎ ያሰበው እምነት ሊከተል ይችላል፡፡ ሁለት እምነቶች ግን በአንድ ቤተ መቅደስ ሊመለኩ አይችሉም፡፡ ሁሉም የየራሱን ነው መከተል ያለበት፡፡ ‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣልና አልጋሽን ልቀቂለት› የሚለው ብሂል ግን ዛሬ የሚያዋጣ አይመስልም፡፡ የሃያ አንደኛው መክዘ ኢትዮጵያንም በጤና አውሎ አያሳድራትም፡፡ በዝቋላ ገዳም ላይ የተጀመረው ርስትን የመንጠቅ ሥራም በዝቋላ የሚያበቃ አይሆንም፡፡ ‹መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም› ከተባለ መንግሥታዊ መዋቅሮች አንድን እምነት ደግፈው ሌላውን እምነት ለመጫን እንዴት ቻሉ?

ስለዚህም

  1. ቅዱስ ፓትርያርኩ ሁኔታውን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ድብዳቤ መጻፋቸው የሚገባ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ግን ይህንን ነገር በዕንቁላሉ ለመቅጨት መወሰንና መሥራት ያለበት ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ መነኮሳቱና ሀገረ ስብከቱ የጻፏቸው ደብዳቤዎች በገዳሙ ስለደረሰው መከራ ብዙ የሚናገሩት ነገር አለ፡፡ በስብሰባዎች የደረሰባቸው ጫና፣ በየጊዜውም የሚደርስባቸውን እንግልት ገልጠውታል፡፡ ሲኖዶሱ ገዳማትን ከመጠበቅ የሚቀድም ሌላ ኃላፊነት የለውም፡፡
  1. ምእመናንም ገዳሙን በንቃት መከታተልና በተለይም በመጋቢት 5 ቀን በክብረ በዓሉ በመገኘትና በዓሉን በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በማክበር ለቅዱሱ ሥፍራ ያለንን ፍቅር፣ ለመነኮሳቱ ያለንን የዓላማ አንድነት፣ ሁላችንንንም ለሚያቅፈው ኢትዮጵያዊነት ያለንንም ክቡር ሥፍራ ማሳየት አለብን

 

  1. መንግሥትም በጥባጭ ካለ ጥሩ ለመጠጣት አይቻልምና በሚዲያ የተሳተው በሚዲያ፣ በአሠራር የተበላሸውም በአሠራር እንዲታረም ማድረግ ይገባዋል፡፡
Exit mobile version