ከጎንደር እስከ አርማጭሆ፤ የቅማንት ጉዳይ፣ የግጨው ግጭትና የኢትዮ ሱዳን ድንበር
ክፍል ፫
ወደ አርማጭሆ መንገድ ጀምረናል፡፡ የተሳፈርኩባት ሚኒ ባስ የገነት ተራራንና ወለቃን በሌሊት አልፋ ወደ ትክል ድንጋይ እየተንደረደረች ነው፡፡ በነገራችን ላይ የገነት ተራራ ‹‹ትግሬ መጯኺያ›› በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ በታሪክ ምሁራን ለዘመነ መሣፍንት መምጣትና ለጎንደር ነገሥታት ፍጻሜ ምክንያት ነው ተብሎ የሚታወቅ ራስ ሚካኤል ስሑል የሚባል ሰው ነበር፡፡ ራስ ሚካኤል ስሁል የትግራይ ተወላጅ ሲሆን ‹ንጉሥ ሠሪ› ወይም ደግሞ ‹አንጋሽ አፍላሽ› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም የሆነው እንዳይነግሥ የንግሥና ዘር የለውም፤ ስለዚህ የይስሙላ ንጉሥ ዙፋን ላይ አስቀምጦ ቤተ መንግሥቱን በቁጥጥር ሥር አደረገ፡፡ በዚህ ዘመን ነገሥታቱ ከጎንደር ራቅ ባሉ አካባቢዎች በግዛታቸው ሥር ያሉትን ሁሉ ማስተዳደርም ሕግን ማስፈንም ተሳናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ከርቀት ቦታዎች እየመጣ ፍትሕ የሚለምነው ሰው ቁጥር በረከተ፡፡
የተከዜ ወንዝንና በርሃን ተሻግረው ለቀናት ተጉዘው ጎንደር የሚደርሱት ትግሬዎች ጎንደር ከተማ ከደረሱ በኋላም ‹ብልኮ› እተባለው ሰፈር ላይ ኬላ ተጥሎ እንዳይገቡ ይከለከሉ ነበር፡፡ ይህም የነ ራስ ሚካኤል ፍትሕ ለማግኘት የትግሬ መጯኺያ የተባለው ተራራ ላይ በመውጣት የጎንደር ቤተ መንግሥትን ወደ ታች እየተመለከቱ ‹‹በሕግ አምላክ!›› እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡ በዚህም ያ ተራራ ‹‹ትግሬ መጯኺያ›› እንደተባለ እንዲጠራ ምክንያት ሆነ፡፡ ዞሮ ዞሮ ተራራው አሁን ገነት ተራራ ተብሎ ስሙ ተቀይሯል፡፡ ጎሃ ሆቴል የሚባል መዝናኛም በደርግ መንግሥት ተሠርቶበት ትግሬ ይዝናናበታል እንጅ አሁን ላይ አይጮኽበትም፡፡
ወለቃ ከጎንደር ከተማ ወደ ደባርቅና ወደ ኹመራ መስመር ላይ ያለች ትንሽ መንደር ነች፡፡ ወለቃ የምትታወቀው ቤተ እስራኤሎች (ፈላሻዎች) መንደር በመሆኗ ነው፡፡ እስራኤል በዘመቻ ሰሎሞን የጀመረችውን ፈላሾችን ወደ አገሯ የመውስድ ሥራ በቅርቡ አጠናቃ ጎንደር ያለውን ቆንሲል ከመዝጋቷ በፊት የፈላሾች መንደር ወለቃ ነበረች፡፡ በወለቃ አሁን ላይ የዳዊት ኮከብ በሰማያዊ ቀለምና በነጭ መደብ የተሳለባት አንዲት የጀበና ቡና ቤት ውጭ አንድም አይሁድ ወይም የአይሁዳዊነት ምልክት አይታይም፡፡ የአይሁዳውያን መንደር ነበረች በሚል ብቻ ትታወሳለች፡፡
ላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ እየደረስን ነው፡፡ ትክል ድንጋይ ከቅማንት ማንነት ጋር ችግር ከተፈጠረባቸው ቦታዎች አንዷ ናት፡፡ በነገራችን ላይ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዚህ አካባቢም እንደ ጭልጋው ሁሉ የከፋ ነገር ተከስቷል፡፡ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ድረስ በሰሜን ጎንደር ብዙ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ክሶች የፍች ጥያቄዎች ያዘሉ ነበሩ፡፡ በጥብቅና እና በዳኝነት ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ግለሰቦች እንዳረጋገጡልኝ በርካታ ጥንዶች ‹ሰይጣን› በመካከላቸው ገብቶ ትዳራቸውን ንዶታል፡፡ በአማርኛ እያወሩ በግእዝ የሚያስቀድሱ በሥርዓተ ተክሊል ጸሎት ተጋብተው ‹አይ ትዳር እንደነሱ ነውጅ!› እየተባሉ ሲነገርላቸው የነበሩ ጥንዶች ቤት በድንገት የሚፈርሰው ‹ሉሲፈር› በመካከላቸው ካልተገኘ በስተቀር እንዴት ሊሆን ይችላል? አባ የንስሀ ልጆቻቸውን እሁድ እሁድ ሰብስበው ‹ስለ ፍቅረ ቢጽ› ሲያስተምሩ ‹ትዳርና ፍቅር እንደ እነ እንትና ነው!› እያሉ በአርኣያነት ሲጠቅሷቸው የነበሩ ጥንዶች ቤት በሰዓታት ውስጥ የቤታቸው ዋልታና ማገር ፈርሷል፡፡ ሕጻናት ትምህርት ቤት ደርሰው ሲመለሱ የወላጆቻቸውን ፍቅርና እንክብካቤ ሲናፍቁ እንዳልነበር ከአባት ወይም ከእናት ጋር ማን እንደሚቀር የልጆች ክፍፍል ተመልሶ ለልጆች ሰቀቀን ሆነ፡፡ ቤተሰብ ይሉት ተቋም ተናደ፤ ፈረሰ፡፡ ልጆችም ተበተኑ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ትዳር ሲፈርስ እያዩ ምንም ማድረግ የማይችሉት ነገር ገጠማቸው፡፡ የአርባ አራቱ ታቦታት ጠበል ይህን የገባ ሰይጣን ፈውስ መስጠት ተሳነው፡፡ በቃ! ቅማንትና አማራ በሚል ሰበብ የስንት ሰው ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ? የቤተሰብ ፍቅር እንዲህ እንዳልነበር ሲሆን ማየት በጣም የሚያም ነገር ነው፡፡
ትዳር እንዴት ይፈርስ እንደነበር ለማስረጃ ይሆን ዘንድ የአንድ ሰው ታሪክ ከዚህ ላይ መናገር ፈለግኩ፡፡ ግለሰቡ ታሪኩን ያጫወተኝ በዚህ መልክ ነበር፡፡ ‹‹አስራ ሰባት ዓመታት ከሚስቴ ጋር አብረን ስንኖር ስለ እርሷ ማንነት የማዉቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ ሰዉነቷ ብቻ በቂዬ ነበር፡፡ እዉነቴን ነዉ የምልህ የጎንደር ልጅ ከመሆኗ ዉጭ የማዉቀው አልነበረኝም፡፡ በጋብቻችን ለአቻዎቻችን አርኣያ የምንሆን ሰዎች ነበርን፡፡ በትዳራችን 3 ልጆችን አፍርተናል፡፡ የመጀመሪያዋ ልጄ 16 ዓመቷ ነዉ፡፡ ባለፈዉ ዓመት የጥቅምት መድኃኒዓለም ሊደርስ አንድ ሳምንት ሲቀረው እናቷ ደወሉልኝና ‹ለመድኃኒዓልም ዝክር ዝግጅት ታግዘኝ ላካት› አሉኝ (አማትን አንቱ በማለት ነው የሚጠራው)፡፡ እኔም እናቷን እንድታግዝ መሔዷን በደስታ ተቀበልኩ፡፡ የጥቅምት መድኃኒዓለም አልፎ ግን ከነገ ዛሬ ትመጣለች እያልኩ ከልጆቼ ጋር ብናያት የዉሃ ሽታ ሆነች፡፡ ስልክ ስንደዉል ስልኳን ዘግታለች፡፡ መጨረሻ ቤተሰቦቿ ካሉበት ቦታ ትክል ድንጋይ ሰዉ ተላከ፡፡ የተላኩት ሰዎች ‹ልጃችን ‹አማራ› አግብታ አትኖርም!› የሚል መልስ ተነገራቸው፡፡ አንድ ዓመት ያልሞላዉን ሕጻን ልጅ እና ሌሎቹንም ልጆቿን ትታ ለመቅረት እንደወሰነች ሰማሁ፡፡ በቄስ በሽማግሌ አስጠየቅኳት፡፡ ፈቃደኛ ልትሆን አልቻለችም፡፡ የሚገርምህ ልጆቼ ሲያድጉ ሠራተኛ አያውቁም፡፡ ሠራተኛ በዘመድ አፈላልጌ ቢያንስ ምግብ እንድታዘጋጅልን አደረግኩ፡፡ ልጆቼ ግን ሌላ ሰው የሠራውን ተመግበው ስለማያውቁ አስቸገሩኝ፡፡ ስለዚህ ምጣድ ሁሉ ሳይቀር እየጋገርኩ ልጆቼን ለማሳደግ ሞከርኩ፡፡ በዚያ ላይ ሕጻኑ ልጅ ሌሊት ላይ እማዬ እያለ ጡት ለመጥባት ፈልጎ ሲያጣት ያለቅስብኛል፡፡ ቤታችን ሁሉ ነገር ምሉእ ነበር፡፡ ግን በዚህ ምክንያት የምወዳትን ሚስቴን አጣሁ፤ ቤተሰቤም ፈረሰ›› አለኝ፡፡ ይህ ግለሰብ የነገረኝ ብዙ የሚያም ነገር አለው፡፡ ቢሆንም የጠቀስኩት ለግንዛቤ በቂ ነው፡፡
ይህ የአንድ ሰው ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ሳይጠፋፉ በሰላም የተለያዩማ እድለኞች ነበሩ፡፡ በዚህ መካከል የሚያድጉ ሕጻናት በሕሊና ሊጎዱ የሚችሉትን ሳስብ አዝናለሁ፡፡ ሆኖም የደማውን ሕሊናየን የሚያክም ነገርም አገኘሁ፡፡ አሁን ላይ ‹በሁለቱም ወገን› ጎራ ከፍለው ሲናከሱ የነበሩ ሁሉ ትምህርት ወስደዋል፡፡ የችግሩ ምንጭ እነርሱ አለመሆናቸውን አምነዋል፡፡ ዛሬ ላይ የአድባር ዛፍ ሥር የተቀመጡ ነጭ ሸማ የለበሱ ሰዎችን ካያችሁ የፈረሰው ትዳር እንደገና ሲጠገን ነው፡፡ እንዳልነበር የሆነው ቤተሰብ ፍቅር በዛፉ አድባር ሲመለስ ነው፡፡ የገባው ሰይጣንም በአርባ አራቱ ታቦት ጸበል ተረጭቶ ሲወጣ ነው፡፡ አሁን ላይ ጎረቤታሞች ቡና እተጠራሩ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ እፎይታን ሰጥቶኛል፡፡ ከላይ የገለጽኩት ግለሰብም ከባለቤቱ ጋር ለመታረቅ ሙከራ ላይ እንዳለ ነግሮኛል፡፡ ትንሽ ቀናት ሰንብቼ ቢሆን ኖሮ የቤተሰቡን ፍቅር ሲታደስ አይቼ እንደምመጣ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
ከትክል ድንጋይ ወደ ታች አርማጭሆ ሳንጃ ጉዞ ቀጥያለሁ፡፡ በዚች ከተማ የማይረሳ ታሪክ አለኝ፡፡ ሳንጃ ከሁለት ዓመት በፊት አውቃታለሁ፡፡ አሁንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ያየኋት ሳንጃ ምንም የተቀየረችው ነገር የለም፡፡ ሙቀቷ ብቻ ትንሽ ሳያይል አልቀረም፡፡ በአካባቢው የነበረው ደንም የተመናመነ መሠለኝ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ለተመሳሳይ ሥራ አሽሬ፣ ዳንሻና ሶሮቃ ደርሰን ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንመለስ ሳንጃ ላይ መሸብን፡፡ ሳንጃ ቤርጎ ለመከራየት ስንዘዋወር አብሮኝ የነበረው ጓዴ ዩንቨርሲቲ አብሮት የተማረ የአርማጭሆ ጓደኛውን አገኘነው፡፡ ይህ የጓዴ ጓደኛ ‹‹እኛ ቤት ካልሔዳችሁ!›› ብሎ ገለገለን፡፡ ተከትለነው ሔድን፡፡ በእንግድነት ቤት እግራችን ታጥበን የሚበላውና የሚጠጣው በገፍ ቀረበልን፡፡ አልጋ ተለቆልን እንድንተኛ ቢነገረንም እንቅልፍ የማያስተኛ ነገር ገጠመን፡፡
በአርማጭሆ ደም የሚባል መጥፎ ነገር አለ፡፡ በእንግድነት የገባንበት ቤትም ደም የተቃቡ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኛ ቤት ከመድረሳችን አንድ ሳምንት ያክል ቀደም ብሎ የጓደኛችን አያት (የአባቱን እናት) ሰው ገደላት፡፡ እንደነገሩን ከሆን በአርማጭሆ ሴት መግደል ነውር ነው፡፡ ሆኖም ግን አልፎ አልፎ እንዲህ ዓይነት ነገር መከሰቱ አይቀርም፡፡ በአርማጭሆ ሰው የተገደለበት ወገን የገዳዩን ተመሳሳይ ወገን ካልገደለ አስከሬኑ አይቀበርም፡፡ ስለዚህ በሰው የተገደለ ሰው ካለ ሌላም እንደሚጨመር መገመቱ ቀላል ነው፡፡ የገዳይ ዘመዶች በተቻላቸው መጠን ከአካባቢው ርቀው ቢሸሹም ከመገደል አይድኑም፡፡ ደም ያልመለሰ ሰው ሁልጊዜም መሰደቢያ ይሆናል፡፡ ደም መመላለስን በተመለከተ ብዙ ገራሚ ነገሮች አሉ፡፡ ሚስቱን አስረግዞ የተገደለ አባት የተወለደው ልጅ አድጎ የአባቱን ደም የመለሰበት አጋጠሚም አለ፡፡ ወንድ ልጅ ቢጠፋ በአርማጭሆ ሴት ደሟን ትመልሳለች፡፡ የአባቱን ወይም የወንድሙን አሊያም የጓደኛውን ደም የመለሰ ሰው ደመላሽ ይሰኛል፡፡ ኮረዳዎች ይገጥሙለታል፤ የዘፍን ቅኔን ይቀኙለታል፡፡ አሊያ ግን በድፍን አርማጭሆ አንገቱን ደፍቶ መኖሩ ነው፡፡ ወደ ቀደመው ነገር ስመለስ የጓደኛችን አባት የገደለበትን ሰው እናት ሳንጃ ከተማ መግቢያው አካባቢ ወንዝ ውኃ ስትቀዳ አገኛትና እዚያው ከእነተሸከመችው እንስራ አሰናበታት፡፡ ሁለቱም እናቶች ተቀበሩ፡፡ ነገር ግን ደም አይደርቅምና ቀጣዩን ሟች ከየትኛው ወገን እንደሚሆን ስለማይታወቅ ከሁለቱም ወገን መፈላለግ ጀመሩ፡፡ እኛ በእንግድነት ባህል እግራችን ታጥበን በልተንና ጠጥተን የሚመች አልጋ ላይ ተኝተን አባትና ልጅ በየተራ መሣሪያ በር ላይ ደቅነው ይጠብቁ ጀመር፡፡ መሣሪያ የያዘ ሰው ከበር ላይ ተቀምጦ እኛ እንዴት እንቅልፍ ይውሰደን? የመከራ ሌሊት ረጅም ነው እንዲሉ እኛም እንቅልፍ በዓይናችን ሳይዞር አድረን አርማጭሆን ለቀን ወጥተናል፡፡
አሁንም ድጋሚ ሳንጃ ተከስቻለሁ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ያስተናገደንን የጓደኛየን ጓደኛ ሳንጃ ላይ አገኘሁት፡፡ ይህ መልካም ወዳጄ የቅማንት ቤተሰብ ልጅ መሆኑን በዚህ ዓመት ነገረኝ፡፡ በፊት ስለነበረው የደም መቀባባት ጉዳይ ሳነሳለት እያዘነ ‹‹ባለፉት ጊዜያት ደም ስትቃባ ጠብህ ከግለሰቦች ጋር ብቻ ነበር፤ አሁን ግን አንድ ሰው ከተገደለ ‹የገደለው እኮ እሱ አማራ ወይም ቅማንት ስለሆነ ነው› እየተባለ ወደ ቡድን ጠብ ይቀየራል፡፡ ብዙዎቹ ዘመዶቼ ወደ ትክል ድንጋይ ናቸው፡፡ ላይ አርማጭሆ የተያዘው ነገር እንዲህ ያለ ነው፡፡ ምን እንደሚሻል አላውቅም›› አለኝ፡፡ ወዳጄ በተፈጠረው ነገር ካዘኑ ሰዎች መካከል ነው፡፡ እርግጥ ነው ያላዘነ ሰው የለም፡፡ ነገሮች አሁንም በዚህ መልኩ መቀጠል አለመቀጠላቸውን ላነሳሁለት ጥያቄ ‹‹እርግጥ ነው አሁን መሻሻሎች አሉ፤ ብዙ ዘመዶቼ ላይ አርማጭሆ ስለሆኑ እሔዳለሁ፡፡ በጉዳዩ ላይ እንወያያለን፡፡ ይህ በሕወሓት የተፈጠረ ሴራ መድረቅ እንዳለበት ዘመዶቼ ሁሉ ያምናሉ›› የሚል መልስ ሰጠኝ፡፡
ይህ ወዳጄ በአካባቢው ያደረግኩትን ጥናት ቀና እንዲሆን ብዙ አግዞኛል፡፡ አንዳንዶቹ ነገሮች በአንድ ኢትዮጵያ በምንላት አገር እየኖርን መሆን አለመሆኑን እንድንጠይቅ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡ ባለፈው ዓመት በምዕራብ አርማጭሆ ግጨው በተባለው አካባቢ የቀለጠ ጦርነት ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡
ችግሩ ከተጠነሰሰ ስድት ዓመታት አልፈዋል፡፡ የሕወሓትን የተስፋፊነት እቅድ በአርማጭሆና ጠገዴ ከሚኖረው ሕዝብ የበለጠ የሚያውቀው የለም፡፡ ይህን የተገነዘቡ የጠገዴና የአርማጭሆ ባላባቶች በአርማጭሆ የተለያዩ አካባቢዎች የዛሬ ስድት አመት ገደማ ቀለም ይዘዉ ዛፎቹን እያቀለሙ ደንበር አበጁ፡፡ ክረምት አልፎ ክረምት ሲተካ ዛፎቹ ላይ የተቀባው ቀለምም እየጠፋ ድንበሩም እየፈረሰ ሔደ፡፡ የተወሰኑ የሕወሓት አራሾች በየዓመቱ ትንሽ ትንሽ እያለፉ ማረስ ጀመሩ፡፡ ለምን? ብለዉ የሚጠይቁ ሰዎች ሲበርክቱ የሁለቱ ክልል መንግሥታት ጣልቃ ገብተዉ ካርታ ሠሩ፡፡ በዚህ ካርታ መሠረት ግጨው በሰሜን ጎንደር ሥር አረፈ፡፡ ከዳንሻ ጀምሮ እስከ ግጨው የተዘረጋ ትልቅ የወያኔ እርሻ አለ፡፡ የትግራይ ልማት ማኅበር እርጎየ ላይ ትምህርት ቤት ሠራ፡፡ የልማት ማኅበሩ የሠራው ትምህርት ቤት ለምን እንደሆነ የተገዘበ ሰው አልነበረም፡፡ በአርማጭሆነና በጠገዴ ያሉ የብአዴን አመራር ካቢኔዎች ሆን ተብሎ ይሁን አሊያም ባጋጣሚ በእናታቸው ወይም ባባታቸው አሊያም ሙሉ በሙሉ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ይበዛሉ፡፡
በሰኔ 2006 ዓ.ም. የክረምት መግቢያ ላይ የሕወሓት የጦር ተመላሽ የሰሊጥ አምራቾች ግጨዉ ከተባለዉ ተራራ አልፈዉ መመንጠር ጀመሩ፡፡ የአርማጭሆና የጠገዴ ሕዝብ አይሆንም ብለዉ በኃይል አባረሯቸዉ፡፡ ከጠገዴ ወረዳ ፖሊስ ሊያጣራ አንድ ኮንስታብል ማዕረግ ያለው ሰው ተላከ፡፡ ለእርሻ የመጡትን ሰዎች የእነርሱ ቦታ አለመሆኑን ነገሮ የአካባቢውን ገበሬዎችም አረጋግቶ ተመለሰ፡፡ ወደዚህ ቦታ የተላከዉ ፖሊስ ግዳጁን ፈጽሞ ከተመለሰ በኋላ በምን እና ማን እንደገደለዉ ሳይታወቅ በአገር አማን በጥይት ተገድሎ ተገኘ፡፡
ሰሊጥ አምራቾቹ እንደገና ተመልሰዉ መጥተዉ ሰሊጥ ለመዝራት ሞከሩ፡፡ ገበሬዎችም እንደገና ለመዝራት ከመጡት ሰዎች ጋር ተጣሉ፡፡ ችገሩ እየተባባሰ በመጣበት ወቅት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ለዞንም ሆነ ለክልል እርዳታ ሳይጠይቅ አፍኖ ያዘው፡፡ የፖሊስ አዛዡ ችግር ወደተፈጠረበት የሚሔዱ ጓዶቹን በግጭቱ መካከል ገብተው እነርሱ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሁሉ ኃላፊነት እንደማይወስድ አስጠንቅቆ ላካቸው፤ በርቀት ቆመዉ እንዲታዘቡ እንጅ ገብተዉ እንዲገላግሉ የፈለገ አይመስልም፡፡
ችገሩ እየጠነከረ ሲሔድ የሚገደሉ ሰዎችም ቁጥር ጨመረ፡፡ የፖሊስ አዛዡ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በስልክ አሳወቀ፡፡ ግን ይፋ ጦርነቱ ተጀመሮ ነበር፡፡ የትግራይና የአማራ ተወላጆች በየጎራቸዉ ተሰለፉ፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን የአማራ አድማ በታኝ ፖሊስ ላከ፡፡ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና አድማ በታኝ ፖሊሶች የሲቪል ልብስ ለብሰው ግን ደግሞ እስከ አፍንጫቸዉ ታጥቀው ወደ ጦርነት ገቡ፡፡ በሲቪል ሰዎች መካከል የተደረገ ግጭት ለማስመሰል የታቀደ መሆኑ ነው፡፡ ግጨዉ ተራራ በአንድ ቀን ዉስጥ ወደ ጦር ሜዳነት ተቀየረች፡፡ ከሳንጃና ትክል ድንጋይ ብዙ ወጣቶች ወደ ግጭው ሲሔዱ መንገዱ ተዘጋ፡፡ ለቀናት ከጎንደር ኹመራ የመኪና መንገድ አገልግሎት መስጠት አቋረጠ፡፡ ምርኮ ሁሉ ነበረ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ በኋላ በሽምግልና ግጭቱ በረደ፡፡ ሕወሓት በወልቃይና በጠገዴ የተነሳውን እንቅስቃሴ ለማፈን እንዲያውም ግዛቴ ከዚህም የሰፋ ነው የሚል አስተሳሰብ ለመፍጠር ያደረገው ይመስላል፡፡
የፌደራል መንግሥት የሚያሠራው ከኹመራ ተነስቶ በማይካድራና አብደራፊ አልፎ መተማ የሚገባ መንገድ አለ፡፡ መንገዱን የያዘው ሱር የተባለ ኮንስትራክሽን ነው፡፡ በአቶ አባይ ወልዱ ትእዛዝ ከማይካድራ ቀጥታ ወደ ሱዳን ታጥፎ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ አቻቸው አቶ ገዱ ደግሞ የአቶ አባይን ትእዛዝ ጥሰው ወደ መተማ እንዲሠራ አደረጉት፡፡ አቶ ገዱ በምዕራብ አርማጭሆ የሚመረተውን ሰሊጥ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይሔድ አብራጂራ ላይ ኬላ ተክለው የኢትዮጵያ የእህል ንግድ ድርጅትም እዚያው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንዲከፍቱ በማስደረጋቸው በአካባቢው ስማቸውን ለመገንባት ጥረዋል፡፡ ብአዴን ለአማራው ሕዝብ የአህያ ባል እንደሆነ ማንም እያወቀ አካባቢው በአቶ ገዱ ላይ የጣለው እምነት ጉድ እንዳይሠራቸው እሰጋለሁ፡፡
ድንበር ጠባቂው ባሻ ጥጋቡ
በምዕራብ አርማጭሆ እጅግ ሰፊ የሆነና ለም መሬት በሱዳን መንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑን በተለያየ የአርማጭሆ አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ነግረውኛል፡፡ በዚህ አካባቢ የነበሩ ቦታዎች ሁሉ አረብኛ ትርጓሜም እየተሰጣቸው ነው፡፡ በእርግጥ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ቢሆን ብዙ ቦታዎች የአረብኛ ትርጓሜ ያላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ አብደራፈፊ የሚባለው ከተማ ስያሜ ‹አብደላ ፊ› ከሚል ከአረብኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‹አብደላ አለ› የሚል ነው፡፡ ያ ማለት ግን አካባቢው የሱዳን ነው ወይም ነበረ ማለት አይደለም፡፡ ሕዝቡ አረብኛን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ የሆነው ሆኖ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ከ2000 ዓ.ም. በፊት በእኛ ገበሬዎች እጅ የነበረ መሬት አሁን እዚህ የለም፡፡ ሕዝቡም በሥጋት ሌሎች የተረፉ ድንበር ላይ ያሉ አረብኛ ሥያሜ የነበራቸውን ቦታዎች ሁሉ ወደ አማርኛ እየቀየራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል ቀድሞ ‹ኮር ኹመር› ትባል የነበረችው ትንሽ መንደር አሁን ‹ጠፈረ ወርቅ› ተብላለች፡፡
አሁን የባሻ ጥጋቡን ጉዳይ እናንሳ፡፡ ባሻ ጥጋቡ በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት ስሙ የናኘ ነበር፡፡ ባሻ ጥጋቡ ለተበደለ ሰው የሚቆምና በኃይለኛነቱ የሚፈራ የራሱ ሚሊሻዎች የነበሩት አንድ ግለሰብ ነው፡፡ እንዲያውም ሱዳኖች ‹ባሻ ጥጋቡ ይቅር እንጅ መለስስ ይመጣ› ይሉ እንደነበር ይወራል፡፡ ድፍን አርማጭሆ ፍትሕ ሲጎድልበት የሚያመለክተው ለምዕራብ አርማጭሆ ፖሊስ አሊያም አስተዳደር ጽ/ቤት አልነበረም፤ ለባሻ ጥጋቡ እንጅ፡፡ ባሻ ጥጋቡ በደል ያደረሰውን ሰው ወዲያውኑ እንዲያስተካከል የፍትሕ ርትእትን ያስጠብቃል፡፡ የሱዳን መንግሥት ለም የሆነውን የአርማጭሆ መሬት በወሰደ ጊዜ የባሻ ጥጋቡን መሬት ማንም ሊደፍረው አልቻለም፡፡ እንደሚባለው የባሻን መሬት አልፈው ሱዳኖች ወደ መሐል ሲገቡ መካከል ላይ የባሻ መሬት ይገኛል፡፡ ሆኖም ሰው ሆኖ ከሞት የሚያመልጥ የለምና ይህ ጀግና በ2005 ዓ.ም. ታሞ ከዚህ ዓለም ተለየ (እርግጥ ነው ለሕክምና አዲስ አበባ በሔደበት ወቅት ሆን ተብሎ ተገድሏል የሚባል ሐሜትም አለ)፡፡
የባሻ ጥጋቡ ተዝካር እለት አንድም የአርማጭሆ ሰው አልተጠራም፤ ነገር ግን አንድም የአርማጭሆ ሰው የቀረ የለም፡፡ ሕዝቡ አዘነ፤ ተዝካሩን ተረባርቦ አወጣ፡፡ የባሻ ጥጋቡን መሞት የሰሙ ሱዳናውያን የባሻን የእርሻ መሬት ለመቀማት ካምፑን ወረሩት፡፡ በዚህ ጊዜ የሚገርም ነገር ተከሰተ፡፡ አንዲት መነኩሴ ቆቧን ጥላ ክለሽ አንግባ ‹‹ገና ለገና ባሻ ሞቷል ተብሎ ርስቱ ሊደፈር ነው?›› በማለት ለጦርነት ሔደች፡፡
አብራጂራ የነበረውን የመለስ ቢል ቦርድ የአርማጭሆ ሰው አውርዶ በምትኩ ‹‹ባሻ ጥጋቡ ሆይ ራዕይህን እናስቀጥላለን!› የሚል ጥቅስ ጽፎ ሰቀለበት፡፡ ይህ ተረት ተረት ሳይሆን ትናንት የተፈጸመ እውነታ ነው፡፡
ከአርማጭሆ ወደ ጎንደር እየተመለስኩ ነው፡፡
የሚቀጥል…