Gondaronline.com

እዚህ ገና ሳትናገር ሃሳብህን በረዶ የሚያደርጉ አፍጣጭና ገልማጮች…

By Alex Abreham
ከሰው ፊት የተፈጥሮ ፊት
(አሌክስ አብርሃም )ወዳጃችን Yona Bir እንዲህ ሲል መልእክቱን ልኮብናል
<<እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አልፈልግም፤ በዐልም አልወድም>> የሚል ሃበሻ እንኳን ቢኖር ዛሬ አገሩን መናፈቁ አይቀርም።ለምን መሰላቹ?

አየሩ!!!

ወይኔ አየሩ፤ ወይኔ ብርዱ፤ ወይኔ ቅዝቃዜው (በእናታቹ ሌላ ቃል ፈልጉልኝ)

ዛሬ አንዳንድ ቦታዎች ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ (-40 °C ወይም -40.0 °F ሁለቱም እኩል ናቸው) ደርሷል። -40 °C ሲባል ቁጥር ብቻ ስለሆነ ስሜቱን አትረዱት ይሆናል። ቆይ በሌላ ዘዴ ላስረዳቹ

ከብርዱ የተነሳ ኡ… ኡ…. ኡ… ብላችሁ መጮህ ያምራቹና ገና ኡ.. ለማለት አፋቹን ስትከፍቱ አፋችሁ ውስጥ ያለው ምራቅ ወደ በረዶነት ስለሚቀየር አፋችሁ እንደተከፈተ ይቀራል። በዚህ ምክኒያት ዛሬ ዎክ ማድረግ ተከልክሏል። ››
.
.
እንግዲህ በዚህ የገና ወቅት … አገር ውስጥ የምትኖሩ (በነሮዛ ቋንቋ ሎካሎች) ያንን ውብ አየር እየማጋችሁ ደስ ይበላችሁ!!

አሌክስ አብርሃም የቤት ክራይ በየቀኑ ማሻቀቡ አብሽቆህ ይሆናል። ግን በምድር ላይ (ከገነት ቀጥሎ) ምርጥ አየር ባላት አዱ ገነት ላይ ገናን በማክበርህ ደስ ይበልህ። ››

Yona Bir ያልከው ሁሉ ገብቶናል !! ግን አልተግባባንም ! ምክንያት ብትለኝ ….

እዚህም ኑሮ ቀዝቅዞ ከዜሮ በታች (-40 °C ወይም -40.0 °F ሁለቱም እኩል ናቸው) ደርሷል። እንዳይመስልህ ወዳጀ እናተስ ጋር ልትናገር አፍህን ስትከፍት ምራቅህ በረዶ ይሆናል እዚህ ገና ሳትናገር ሃሳብህን በረዶ የሚያደርጉ አፍጣጭና ገልማጮች ብዙ ናቸው ! ወዳጀ በእኔ ይሁንብህ ከሰው ፊት የተፈጥሮ ፊት ቢገለምጥህ ይሻላል ! አርፈህ ዶላሬህን ሰራ ሰራ አድርግና ደህና ማሞቂያ ሸምት !

የሰው ልጅ ንፁህ አየር ወደውስጥ በመሳብ ብቻ አይኖርም የተቃጠለውን አየርም ወደውጭ ሲተነፍስ እንጅ ! እና መተንፈስህ በሚደብራቸው ሰወች መሃል ከሆንክ እንኳን ከገነት ቀጥሎ ያለ አገር ገነትም ራሱ ከሲኦል እኩል ነው ፡፡ ዮኒ የቤት ኪራይ መጨመር አያምም ….የቤት ኪራይ ጨምር መባል ነው የሚያመመው …..አለመተንፈስ አያምም አትተንፍስ መባል ግን ያማል …..ስለነፃነት የሚያወሩህ ሰወች ምርኮኞች ናቸው ምርኮኛ ጋር ደግሞ ማራኪ አይጋጭም ! በሃሳብ የተለየ ግን ዎዮለት !

ያው እንዳየኸው በተያያዘ ዜናህ እንደታዘብከው …..እች አገር ሳትቀመጥ እግሯን እየዘረጋች መፈንገል ሆኗል እጣ ፋንታዋ ሃሳብ እየተገመደለ እና እየታፈነ ለአንዲት ፊደል ፊርማ ሰብስቡ ይሉናል ! ከደቡብ እስከሰሜን የተዘረጋ ችግር ሳይቆረቁራቸው ከጉሮሮ እስከምላስ ያለች ድምፅ የእግር እሳት የሆነችባቸው ወዳጆቻችን ዘመቻ ላይ ናቸው !

እና ልድገምልህ ከሰው ፊት የተፈጥሮ ፊት ቢገለምጥህ ይሻላል ! በረዶ ለዘላለም ይኑር ! በረዶ ላይ ገናን በማክበርህ ደስ ይበልህ ! እኛም ቃላችን ሳይሆን ምራቃችን በረዶ የሚሆንበት ዘመን ይናፍቀናል ንግግር የሚከለክል ሃሳብን በነፃነት እንዳትገልፅ የሚያግድ በረዶ በፀሃይ ይቀልጣልና !!

Exit mobile version