መረጃና ጥቅሙ

Achamyeleh Tamiru

የወያኔ ድርጅታዊና ስርዓታዊ ሞዴል ቁሳቁሳዊ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ጉልበት ማግኘት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ሞዴል እስከ ዛሬ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በነበሩት ስልጣኔዎች ሁሉ የሰራሞዴል ነው። የሞዴሉ ጽንስ ሀሳብ እንደሚከተለው ነው። ቁሳቁሱን የተቆጣጠረ አካል ሁኔታዎች ወዴት እንደሚያመሩ መቆጣጠር ይችላል የሚል መነሻን ያደርጋል። የቁጥጥሩ ስርዓት የሚከናወነው ደግሞ የመረጃ ስርጭትን በመቆጣጠር ሲሆን ይህንን ለማድረግ በቁጥጥር ስር ያለውን አካላዊ መሳሪያ ሁሉ ይጠቀማል። ይህ የተለመደ ሁኔታ ነው።

ዛሬ ላይ ግን መሳሪያ ብቻ ይረዳል ማለት ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ አይደለም። ምንም እንኳን ይቺን የአሁኗን ቅጽበት የሚቆጣጠረው ብረቱን የያዘው አካል ቢሆንም የምትቀጥለውን ደቂቃ ወይም ሰዓት ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ግን መረጃውን የሚቆጣጠረው አካል ነው።

እስከ አለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት ድረስ መሳሪያውን የያዘው የሚተላለፈውን መረጃ ይወስን ነበር። ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። ዛሬ መረጃን መቆጣጠር ማለት ተደማጭነት መኖር ማለት ነው። መረጃ ካለህ ሰው ሊሰማህ ይፈልጋል። መረጃ ከሌለህ የለህም። መረጃ ከሌለህ ማንም ሊሰማህ አይፈልግህም። ማንም ሊሰማህ ካልፈለገ ምንም መስራት አትችልም። ይህ ማለት እንግዲህ የአድማጭ መልካም ፈቃድ የሚገኘው በመረጃ ነው ማለት ነው። አንድ ሰው ሌላውን ለማዳመጥ መልካም ፈቃድ ከሌለው በመሳሪያ አስገድደህ ሙሉ ቀን ስብሰባ ላይ ብታውለው፤ ሙሉ ቀን በሬዲዮና በቴሎቭዥን ብትለፈልፍ ምንም የምታመጣው ለውጥ የለም። በርግጥ ሰውን ያለፍላጎቱ አግተህ ፖለቲካ በመጥመቅ ጊዜያዊ ግንዛቤ መፍጠር ይቻል ይሆናል። ይህ በሚሊዮን ብር የተገነባው ግንዛቤ ግን በአንድ የፌስቡክ መልዕክት ሊፈርስ ይቻላል።

ይህ እንዲሆን ትክክለኛ መረጃ ያስፈልጋል። ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ ከሁሉ አስቀድሞ ለራስ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ ራሱን ነጻ ለማውጣት የሚያስችል ፍላጎትና አቅም አለው። ሆኖም የያንዳንዱ ሰው ፍላጎትና አቅም ብቻውን ነጻነት አያመጣም። ፍላጎትና አቅም በመረጃ ታጅለው ጣምራ መሆን አለባቸው።

መረጃ ሲጠራቀምና ጣምራ ሲሆን አቅምና ፍላጎትን አቀጣጥሎ ወደተፈለገበት የሚያደርስ ነዳጅ ነው። ትክክለኛ መረጃ ወደነጻነት ሲያደርስ የተሳሳተ መረጃ ነጻነትን ያስነጥቃል። አንድ ሃላፊነት የሚሰማው ሰው ለቤተሰቡ፣ ለጎረቤቱ፣ ለማኅበረሰቡ፣ ለሃገሩ ሊያደርግ የሚችለው አነስተኛው ነገር፣ ያለውን ትክክለኛ መረጃ ለሁሉም ማካፈል ወይንም ለሁሉ ወደሚደርስበት የመረጃ ቋት መላክ ነው። በየትኛውም መንገድ መረጃ ያገኘ ሰው ለነጻነቱ የሚችለውን እንዲያደርግ የሰው ተፈጥሮ ያስገድደዋል። ባጭሩ በባርነት እየኖርን ያለነው ሁላችንም ተባብረን የጋራ የመረጃ ቋት ባለመፍጠራችን ወይንም ያወቅነውን ትክክለኛ ነገር ለሁሉም ባለማሳወቃችን ነው።

ያየውንና የሚያውቀውን ትክክለኛ መረጃ የሚደብቅ ሰው ሃላፊነት የማይሰማው ሰው ነው። እውነቱን የሚደብቅ ሰው ለሰው ጥሩ የሚያስብ ሰው አይደለም። አውቆም ሆነ ሳያውቅ የውሽት መረጃ የሚያጋራ ሰው ደግሞ የሰውን ጥፋት የሚሻ ተልኮለኛ ሰው ነው። የግራ ፖለቲካ ወደ አገራችን ከገባ ወዲህ እኛ አገር አንዱ ትልቁ ችግር የተንኮለኛና ሴረኛ ሰዎች መብዛት ነው። ያ ደዌ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የዛሬው ትውልድ በሽታም ሆኗል። ካለፉት አርባ አመታት ወዲህ ባዳበርነው የፖለቲካ ባህል መረጃን መደበቅ ወይም ስህተት የሆነን መረጃ ማስተላለፍ እንደባህል ሆኗል። ለዚያም ነው የግራ ፖለቲካ ባህል ወደ አገራችን ከገባ ጀምሮ አለመተማመን ባህላችን የሆነው። ይሄ የፖለቲካ ባህል እውነት ቢነገርም በጥርጣሬ ለማየት እንድንገደድ አድርጎናል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ችግራን ብዙ ሆኗል።

በሶማሌና በአፋር ባህል ውስጥ ግን የሚደነቅ የመረጃ ልውውጥ ባህል አለ። ለሶማሌና ለአፋር መረጃ የነፍስ ያህል ነው። እንደሚታወቀው የዘላን ህይወት ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ ነው። ዘላን ከአንዱ ቦታ ተነስቶ ወደሌላው ቤተሰቡን፣ ከብቱንና ባጠቃላይ በዚህች አለም ላይ ያለውን ሁሉ ይዞ በረሃውን አቋርጦ ሲሄድ ስለሚያጋጥመው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በመዳረሻ ቦታው ውሃው ደርቆ ከሆነ ሁለት ቀን ተጉዞ እዚያ ሲደርስ ጉድ ሊሆን ይችላል። ቤተሰቡ ሊያልቅበት ይችላል። በዚያ መንገድ ላይ ሽፍቶች ወይም ተቀናቃኝ ጎሳዎች ካሉ ካላወቀው ከነቤተሰቡ ያልቃል። ስለዚህ ምንም ሌላ የመገናኛ መሳሪያ በሌለበት አንድ አፋር ወይም ሶማሌ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ በየቀኑ በትክክል ማወቅ አለበት። የተሳሳተ መረጃ ካለው አለቀለት። የዚህ ችግር መፍትሄ በነዚህ ጎሳዎች ባሕል ውስጥ አለ። ይኸውም መረጃን በትክክል ለጎሳቸው አባል ለሆነ ሰው በትክክል ማስተላለፍ ነው።

ሁለት አፋሮች መንገድ ላይ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ሲሄዱ ከተገናኙ ይቆሙና፣ ዱላቸውን መሬት ላይ ተክለው ተደግፈው መረጃ ይለዋወጣሉ። የመረጃ ልውውጡ ስርዓት አለው። አንዱ ሲናገር ሌላኛው እህ! እህ! እህ! እህ! እያለ ከማዳምጥ በስተቀር አያቋርጠውም። መንገድ ላይ ያለውን አደጋ፣ የማን ቤተሰብ የት ጋ እንዳለ፣ የትኛው የውሃ ምንጭ እንደደረቀ፣ ሌላም ሌላም ነገር ይነግረዋል። ተራው ሲደርስ ያኛውም እንደዚያው ያደርጋል። ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ከሰጠ በሰውዬውና ቤተሰቡ ህይወት ላይ ፈረደ ማለት ነው። ስለዚህ በዛ እልም ያለ በረሃ ውስጥ እያንዳንዱ አፋር የሚሆነውን፣ የሚያጋጥመውን፣ የቱ ጋ ምን እንዳለ በደምብ ያውቃል ማለት ነው።

ይህንን ፈረንጆቹ situational awareness ይሉታል። አሁን አሁን ግን ከባድ የነበረውን የአፋሮና የሶማሌዎች ህይወት ሞባይል ስልክ የበለጠ አቃሎታል።
ትግራይ በነበርሁ ጊዜ «ዞን ሁለት» በሚባለው የአፋሮች አካባቢ ለመስክ ጥናት ሄጀ አርባ ግመል የሚጎትት የአብር አባወራ አርባውን ግመል ሰትሮ በሞባይል ስልኩ ሌላ ቦታ ላለው የጎሳው አባል መረጃ ሲያቀብልና situational awareness ሲሰጥ በአይኔ አይቻለሁ። ይህንን ለመገንዘብ የቻልሁት አፋርኛ የሚችለው ትግሬው ሾፌራችን አርባውን ግመል ሰትሮ ለረጅም ጊዜ በሞባይሉ ያወራ የነበረው አፋር ምን እያወራ እንደሆነ ጠይቄው ሌላ ቦታ ላለው የጎሳው አባል መረጃ እየሰጠ እንደሆነ ተርግሞ ነግሮኝ ነው። ሾፌራችን አጠገባችን የቆመው አፋር ወዲያ ማዶ ላለው የጎሳው አባል… በዚያ አትሂድ፣ በዚህ አቋርጥ፣ እዚያ ብትሄድ ይህ ይገጥምሀል፣ በዚህ ብትሄድ ይህንን ታገኛለህ፣ ወዘተ እንደሚለው ተርጉሞልኛል።

እስካሁን ወያኔ በህዝባችን ላይ ተነግሮ የማያልቅ ሰቆቃ ሲታደርስ ለምንድነው የረባ ራስን ነጻ የማውጣት የተባበረ እንቅስቃሴ ያልተደረገው ለሚለው መልሱ እዛ ጋ ያለ ይመስለኛል። ዘላኖቹ አፋሮችና ሶማሎዎች እንዳላቸው አይነት ትክክለኛ የሆነ የዳበረ የጋራ የሁኔታዎች ምልከታ (situational awareness) የለንም። ካለንም የተሳሳተ፣ የተዛባ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልሁት እውነት ቢሆንም አናምነውም፤ እንጠራጠራለን። የምንጠራጠረውን ከማረጋገጥ ይልቅ ይዘነው እንቀራለን። የማረጋገጥ ፍላጎቱ ካለ ግን ለማንጠር [refine ለማድረግ] ቀላል ነው። ቀላሉ ዘዴ ማመሳከር ነው፤ ከሌላው ጋር መለዋወጥ ነው። ሁሉም ሰው «ይህ በዛ ያ አነሰ» ሳይል ያለውን መረጃ ጠረጴዛው ላይ [ፌስቡኩ ላይ ማለቴ ነው] [ስጋት ያለበት ካለ ደግሞ በውስጥ መገናኛ መስመር ለሚያምነው ሰው ሊልክ ይችላል] ከዘረገፈው የዚህ ሁሉ ሰው አይን እውነቱን ከውሸቱ ለይቶ ያወጣል። ማመሳከር ማለት ያ ነው። አፋር ውስጥ የሰውን ስም ማጥፋት ከባድ ነው። ሲስተሙ እያመሳከረ እውነቱን ያወጣዋል። ለነፍስህ ስትል ሁሉንም ስለምታዳምጥ እውነቱ ወዲያው ይወጣል። ውሸታሙ ወዲያው ይጋለጣል። ውሸቱ ሲጋለጥ ህይወት ሊጠፋውም ይችላል።

በኛ አካባቢ እንደ አፋርና ሶማሌዎች እውነቱን እያመሳከረ የሚያወጣ ሲስተም ስለሌለ ሰው ጥይት መተኮስ አያስፈልገንም። አንዱን የማንፈልገውን ሰው ልናጠፋው ከፈክለግን ያልሆነ ወሬ አንስተን «ቱስ» ብንል የፈለገ ትልቅ ሰው፤ ደግ ፍጡር ቢሆን ደብዛውን ልናጠፋው እንችላለህ። ይህም የሚሆነው ውሸት ብናወራ ስለሚወራው ነገር ስለማናመሳክር ነው። እውነት በቀላል ይገኝ ይመስል ውሸት በቶሎ እንቀበልና ስለእውነት የሚገባውን ክብደት አንሰጥም።

ያለንበትን ጊዜ መጠቀም ከቻልን ይህንን ሁሉ ችግር ማስወገድ የምንችልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። የዘመኑ ቴክኖሎጂው ነገሮችን አቅሏቸዋል። ከኛ የሚጠበቀው ያለውን ሁሉ መረጃ በትክክል ማቅረብ ነው። ቴክኖሎጂውና የሰው ልጅ የእውቀት ደረጃ አንድን መረጃ እውነት እንኳ ባይሆን በቀላሉ ያጣራዋል። ቴክኖሎጂው የቀረበለትን መረጃ በተቻለ መጠን ማዛመድ፣ ማጣራት፣ ማመሳከር ይችላል።

ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂና እውቀት ከሌለን ግን የአፋሮችንና የሶማሌዎችን የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ብንከተል ብዙውን ችግራችንን ማቃለል እንችላለን። ስለዚህ እንደ አፋሮች የሰማኸውን ነገር ሁሉ ሰማሁ ብለህ አቅርብ፤ ያየከውንም አጋራ። የሰማኸውን አየሁ ካልህ፤ ያላየኸውን አይቻለሁ ካልክ መረጃውን በከልከው ማለው ነው። የተበከለ መረጃ ሰው ርግጠኛ ሳይሆን እንዲፈርድ ያደርገዋል።

በሰለጠኑት ፈረጅኖች ዘንድ ዛሬ የአንድን መረጃ ትክክል መሆን አለመሆን በሂሳብ ቀመር የሚፈትን ነጻ የኮምፒዩትር ፕሮግራም አለ። ይህ ምናልባትም ላይመስል ይችላል። በርግጥ ይህ ፕሮግራም የሁሉን ተሳትፎ ይጠይቃል። ፕሮግራሙ swiftriver ይባላል። እውነቱን ከውሸቱ አበጥሮ ያወጣል።

ፕሮግራሙ ስለራሱ እንዲህ ይላል… «SwiftRiver is a platform that helps people make sense of large amounts of information in a short amount of time. It’s also a mission to democratize access to the tools used to make sense of data – to discover information that is authentic.»

አንድ አይነት ራዕይ ያለን ሰዎች የራሳችን swiftriver መፍጠር እንችላለን። ታዲያ የኛው swiftriver የኮምፒዩተር ፕሮግራም አይደለም፤ መረጃ የምንልክለት የኛ የሆነ ሁነኛ ሰው እንጂ። ይህ የኛ swiftriver የመረጃ ማእከል ይሆንና አጠቃላይ የመረጃ ፍሰቱን ይቆጣጠራል። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በሚመለከት የመረጃ ፍሰቱን የሚቆጣጠረው ይህን አካል ካወቅን ወይንም ያን አካል እኛ ከፈጠርነው ወደፊት በማን ራዕይ እንደምንመራ ማወቅ እንችላለን ማለት ነው።

ስለዚህ በተለይ አገር ቤት ያላችሁ የመረጃ ትንሽ የለውምና በእጃችሁ ያለውን ስልክ ሳይቀር በመጠቀም መረጃ ሰብስቡ። የሰበሰባችሁትን መረጃ ደግሞ የኛ swiftriver ነው ብላችሁ ለምታስቡት ሰው ላኩ። ይህ ሰው የላካችሁትን መረጃ አደራጅቶ ፤ ትርጉም ሰጥቶ፤ሁኔታ አበጅቶ፤ መልክ አስቀምጦና ተንትኖ የዳበረ የጋራ የሁኔታዎች ምልከታ ይፈጠራል። ይህ የነጻነታችን ሞተር ነዳጅ ነው። ያየነውን፤ ያወቅነውን ወደ አንድ swiftriver የሆነ ሰው በመላክ ያለብንን ሃላፊነት በመወጣታችን ነጻ እንወጣለን።

ሁላችንም በኃላፊነት ስሜት ያለንን፣ ያየነውን፤ ያወቅነውን ሁሉ ወደ መረጃ ቋታችን ማለትም ወደኛው swiftriver መላክ ከቻልን በቀላሉ መጻኢ እድላችንን መቅረጽ እንችላለን፤ መረጃ ፍሰቱን የሚቆጣጠረው አካል የወደፊቱን ሁሉ ይቆጣጠራልና!

አክባሪያችሁ!

አቻምየለህ ነኝ!

Leave a Reply